Monday, September 28, 2015

ብሪታኒያ በደርዘን የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ልትልክ ነው።


መስከረም ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን እንዳስታወቁት ወታደሮቺ የሚላኩት አልሸባብን እየተዋጉ ላሉት የ አፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ልዑክ ድጋፍ ለመስጠት ነው።
በመሆኑም እስከ 70 የሚደርሱ የ እንግሊዝ ወታደሮች በቅርቡ የሰላም አስከባሪ ልኡኩን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብሪታኒያ ከዚህም በተጨማሪ እስከ 300 የሚደርሱ ወታደሮቿን በደቡብ ሱዳን እንደምታሰፍር የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
ውሳኔውን አስመልክቶ በመንግስታቱ ድርጅት ስብሰባ ላይ ድጋፍ እንደሚቸራቸው የተገመቱት ዴቪድ ካሜሩን ወታደሮቹ ወደ ስፍራው መንቀሳቀሳቸው ወደ አውሮፓ የሚደረግን ህገወጥ የስደተኞች ዝውውር ለመግታት እንደሚረዳም ተናግረዋል።
በስብሰባው ከዴቪድ ካሜሩን ጋር ፊት ለፊት ይነጋገራሉ ተብለው ከሚጠበቁት በርካታ የ ዓለማችን መሪዎች መካከል የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኪ መሀመድ አንዱ መሆናቸውም ተመልክቷል። አልሸባብ መላው ሶማሊያን ለመቆጣጠር ከሶማሊያ ጊዜያዊ መንግስት ጋር እየተዋጋ ያለ ጽንፈኛ ድርጅት መኾኑ ይታወቃል።
በቅርቡ ወደ ሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የብሪታንያ ጦር የስልጠና፣ የህክምና፣ የስንቅና የኢንጂነሪንግ ድጋፍ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ወደ ደቡብ ሱዳን የሚነሳቀሰውም እንዲሁ የስልጠና እና የኢንጂነሪንግ ድጋፍ በመስጠት አስፈላጊ መሰረተ-ልማቶች በሚጠናከሩበት ሁኔታ ድጋፍ እንደሚሰጥ የዜና አውታሩ ጠቁሟል።
በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ታማኞች እና በቀድሞ ምክትላቸው በሪክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ እስካሁን 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው እንደተሰደዱ ይነገራል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment