Wednesday, February 11, 2015

የኢትዮጵያ “የድብቅ ዕዳ” በድብቁ የዓለም ባንክ (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የወያኔ ወሮበላ ስብስብ ቡድን በቀፈቀፈው ድብቅ ዕዳ ምክንያት እንደ በረዶ ክምር የተቆለለባትን ዕዳ መክፈል የማትችለው ሉዓላዊቷ ኢትዮጵያ፣ ባለፈው ሳምንትEthiopia’s “Odious Debt” to the Odious World Bankየዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ “የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የቁማር ጨዋታ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት የሚከተለውን ድብቅ ዕኩይ ድርጊት ለማጋለጥ ሞክሪያለሁ፣ “…በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የዓለም ባንክ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለሚገኘው እና እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ ለሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 600 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ የወደፊት ትውልዶች ምንም ዓይነት ተጠቃሚ ባልሆኑበት ሁኔታ ይህንን የተቆለለ እና የሚኮመዝዝ ዕዳ እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ፡፡ ይህንን ፍትሀዊ ያልሆነ የወያኔ የሸፍጥ ዕዳ ለመክፈል በህግ ሊገደዱ ይችላሉን!?! እም!“ የወያኔ የወሮበላ ስብስብ ቡድን እንክት አድርጎ የበላውን እና የተቀራመተውን የብድር ገንዘብ የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም ዓይነት ተጠቃሚነት ያልሆነበትን የተቆለለ የዓለም ባንክ የድብቅ ዕዳ የመክፈል ኃላፊነት ሊኖርበት ይችላልን?
የተቆለለ “ድብቅ ዕዳ” በሚከተለው መልክ ሊገለጽ ይችላል፣ “ድብቅ ዕዳ የህዝቦችን ጥቅም በማያስጠብቅ ዓላማ ላይ የተመሰረተ እና በገዥው አካል የሚፈጸም ህገወጥ ብሄራዊ ዕዳ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ህገወጥ ብሄራዊ ዕዳ በሀገሪቱ ህዝቦች እንዲከፈል ግዴታ ሊጣልበት አይችልም፡፡“
የህዝቦች የመሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ ፕሮጀክት 3 (መአጥፕ 3)/Protection of Basic Services Project (PBS III) እየተባለ የሚጠራው እና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ለወያኔ የዘራፊ ቡድን በዓለም ባንክ በኩል የተሰጠው 600 ሚሊዮን ዶላር (እንዲሁም በሁለትዮሽ እና በብዙሀን ሀገሮች አማካይነት በሚደረግ ስምምነት መሰረት የሚሰጡ ሌሎች ብድሮች አያንዳንዱ ሁሉ አንድ በአንድ እየተነሱ የሚገመገሙት ህገወጥ ድብቅ ብድሮች ናቸው፡፡ ይህንን ስል በዓለም ባንክ፣ ባለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ በቻይና፣ በጃፓን እና በእንግሊዝ መንግስታት እንዲሁም በአፍሪካ ልማት ባንክ ወይም ደግሞ በሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገሮች የሚሰጡ ብድሮች በሙሉ አንድ በአንድ ተመርምረው ድብቅ አዳ መሆን ወይም አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈለጋል የሚል ሀሳብን ማራመዴ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛውን በሚባል መልኩ በርካታዎቹ ድብቅ ዕዳዎች ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ እምነቴ ሙሉ በሙሉ ትክክል ለመሆኑ የእያንዳንዱን የብድር ስምምነት ሁኔታ አንድ በአንድ መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡
አሁን በዚህ ትችት ላይ (መአጥፕ 3)/(PBS III) እየተባለ በሚጠራው የድብቅ የብድር ስምምነት ላይ ትኩረት በማድረግ የማሳመኛ የክርክ ጭብጦቸን አቀርባለሁ፣ ምክንያቱም ይህ 600 ሚሊዮን ዶላር ብድር በማያጠያይቅ መልኩ ድብቅ ዕዳ መሆኑን ተራራ የሚያህሉ ግልጽነት ያላቸው ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ስለሚገኙበት ነው፡፡
የኢትዮጵያ “ሉዓላዊ የድብቅ ብድር” የኢትዮጵያ ህዝብ ለልማቱ እና ለእድገቱ ያልተጠቀመበትን እና በህዝቡ ስም የወያኔ የወሮበላ ስብስብ ቡድን ገንዘቡን እየተቀበለ የቁማር ጨዋታ የተጫወተበትን የልማት እና የዕድገት ሳይሆን የቅርምት እና የመፈንጫ ገንዘብ ውርደትን ለተላበሰው ዓለም ባንክ እየተባለ ለሚጠራው መቅን የለሽ ድርጅት መከፈል እንዲችል በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የህግ ግዴታ ሊጫንበት ይችላልን? ሸፍጠኛው የዓለም ባንክ ለወያኔ የወሮበላ ስብስብ ቡድን እንደ ቅርጫ ስጋ እየተለተለ እና እንደ ጉሊት የችርቻሮ ቦታ እየመደበ ያንበሸበሸውን እና እንደ በረዶ ተራራ የተቆለለውን ብድር የወደፊቱ የኢትዮጵያ ትውልዶች የመክፈል ግዴታ ሊኖርባቸው ይችላልን?
በዚህ በአሁኑ ትችቴ ላይ (መአጥፕ 3)/(PBS III) እየተባለ የሚጠራው የይስሙላ የልማት ፕሮጀክትን የትግበራ ስራ ለማሳለጥ በሚል ሰበብ በሙስና የተዘፈቀው እና የበከተው፣ በማጭበርበር የተካነው እንዲሁም ምንም ዓይነት ምሁራዊ፣ ማህበራዊ ወይም ደግሞ የሞራል ስብዕና የሌለው የወያኔ የወሮበላ ስብስብ ቡድን እየተቀበለ ለተቀራመተው የብድር ገንዘብ ይህ በአሁኑ ጊዜ ያለው ወይም ደግሞ ለወደፊቱ የሚመጣው ትውልድ ይህንን ያልተጠቀመበትን ድበቅ ዕዳ የመክፈል ህጋዊ ግዴታ እንደሌለበት የክርክር ጭብጦቸን ዳህራ አቀርባለሁ፡፡
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ “ሉዓላዊ የድብቅ ብድር”፡ ሊጠየቁ የሚገባቸው ታላላቆቹ የህግ ጥያቄዎች፣
ከህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ ፕሮጀክት 3 (PBS III) ጋር በተያያዘ መልኩ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ወሰደች እየተባለ በሚነገረው ብድር ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እና ጉዳዮች በርካታ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በጣም ጥቂት በሆኑት ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፣
1ኛ) የዓለም ባንክ (መአጥፕ 3)/(PBS III) እየተባለ ለሚጠራው ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ሰጠ የተባለው ብድር ሙሉ በሙሉ ወይም ደግሞ በከፊል ለታለመለት ዓላማ አልዋለም ቢባል ወይም ደግሞ በስልጣን ላይ ባሉት ዘራፊ ወሮበሎች፣ በእነርሱ ግብረ አበሮች እና ተባባሪዎች ተዘርፏል፣ አላግባብ ለሌላ ተግባር ውሏል፣ ባክኗል፣ ተመዝብሯል፣ ተጭበርብሯል እናም በስልጣን ላይ ባሉት ዓይን ያወጡ ፈጣጣዎች በሙስና ተበልቷል ቢባል የኢትዮጵያ ህዝብ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ይህንን ድብቅ ዕዳ እና በምንም ዓይነት መልኩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ያልዋለ ዕዳ ለመክፈል ግዴታ ሊኖርበት ይችላልን?
2ኛ) በተራ ቁጥር 1 ላይ የተጠየቀው ጥያቄ ምላሹ አዎንታዊ ቢሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ድብቅ ዕዳ የመክፈል ግዴታ አለበት የሚል ቢሆን ይኸ ተሰጠ የተባለው ብድር ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር ዘረፋውን ያካሄዱት እና ከብድር ስምምነቱ በሙስና፣ በዘረፋ እና ማጭበርበር ተጠቃሚ የሆኑት የግል ወይም ደግሞ የወያኔ ወሮበላ ስብስብ ቡድን አመራሮች፣ የእነርሱ ግብረ አበሮች እና ተባባሪዎች የግል ብድር እና ዕዳ ነው የሚል የክርክር ጭብጥ ሊነሳበት ይችላልን?
3ኛ) በተራ ቁጥር 1 እና 2 የቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ አዎንታዊ ቢሆኑ የወያኔ የወሮበላ ስብስብ ቡድን አመራሮች፣ የእነርሱ ግብረ አበሮች እና ተባባሪዎች በጋራ እና በተናጠል ወይም በተጣማሪነት ለእነዚህ ዕዳዎች በግል ተጠያቂዎች ሊሆኑ ይችላሉን?
4ኛ) በተራ ቁጥር 1 ላይ ለቀረበው ጥያቄ ምላሹ አዎንታዊ ከሆነ የዓለም ባንክ የታወቀውን ገንዘብ ወይም ደግሞ እያወቀ ለወሮበላው የወያኔ ስብስብ ቡድን በመስጠት የሙስና መረቡን ዘርግቶ ወይም የማጭበርበር እና በተደራጀ መልኩ የማታለል ስልታዊ አካሄዱን አዘጋጅቶ ከህግ አግባብ ውጭ ከታለመለት ዓላማ አንጻር ሳይሆን በሙስና እንዲመዘበር በማድረጉ የኢትዮጵያ ህዝብ የዓለም ባንክን በህጋዊ መንገድ ወደ ህግ አካል አቅርቦ ህጋዊ እርምጃ ማስወሰድ ይችላልን?
5ኛ) የዓለም ባንክ ህጋዊነት ለሌለው ገዥ አካል (በምርጫ 99.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት በዝረራ አሸንፊያለሁ ለሚል ፈጣጣ) ገንዘብ በማበደር ይህንንም ብድር በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ተቀብሎ በዚሁ ገንዘብ ዘርፈ ብዙ የሆኑ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎችን እዲያካሂድ እንዲሁም ለዘመናት ከቀደምቶቻቸው ጀምሮ ሲኖሩበት ከኖሩበት ቀያቸው ህዝቦችን በግዴታ በማፈናቀል ወደሌላ እና ለጤንነት አዳጋች ወደ ሆነ አካባቢ እንዲሰፍሩ በማድረግ በሰው ልጆች ላይ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል እንዲፈጸም በማድረግ እና ተባባሪ በመሆን የዓለም ባንክ ከፍተኛ ወንጀል ሰርቷልን?
6ኛ) ለዘመናት በቋሚነት ይኖሩበት ከነበረው ቦታቸው (መአጥፕ 3)/(PBS III) እየተባለ በሚጠራው ፕሮጀክት ስም ብድር በመስጠት በጋምቤላ የአኟክ ማህበረሰብ በወያኔ የወሮበላ የስብስብ ቡድን ቀደምቶቻቸው ሲኖሩበት ከነበረው ቦታ በግዳጅ እንዲፈናቀሉ በማድረግ ለም ወዳልሆነ እና ምንም ዓይነት እህል ወደማያበቅል እና ለእርሻ ምቹ ወዳልሆነ ጠፍ መሬት እንዲጋዙ በማድረግ፣ እንዲሁም የህዝቦቹ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው ሊሟሉላቸው በማይችሉበት ሁኔታ እና ታላቅ ሰቆቃን፣ መከራን እየተቀበሉ እና የሞት ሰለባ እየሆኑ እንዲያልቁ በተወጠነው የሸፍጥ ስራ ላይ የዓለም ባንክ እንደ ተጨማሪ አበረታታች እና የዕኩይ ድርጊቱ ተባባሪ እና አጋዥ እንዲሁም የወያኔ ስብስብ ቡድን ህገወጥ ድርጊትን እንዲሰሩ እገዛ በማድረግ በኩል በሰው ልጆች ላይ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በማካሄድ ወንጀል ላይ ተጠያቂ ሊሆን ይችላልን?
7ኛ) ሆን ተብሎ በስምምነቱ መሰረት ተግባራዊ እንዳይደረግ በተተወ የብድር ስምምነት መሰረት ከታለመለት ዓላማ ውጭ ለተመዘበረ የዓለም ባንክ ብድር የኢትዮጵያ ህዝብ የመክፈል ተጠያቂነት ሊኖርበት ይችላልን?
8ኛ) የዓለም ባንክ የባንኩን ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች፣ የጸደቁትን የቢዝነስ ተሞክሮዎች እና የባንኩን ቀደምት የተመሰረቱ እና በስፋት ተቀባይነት ኖሯቸው በመተግበር ላይ ያሉትን ተሞክሮዎች ከምንም ባለመቁጠር በእንዝህላልነት እና የተንሰራፉ የሰብአዊ መብቶች ድፍጠጣ ተግባር በማከናወን ላይ የሚገኙትን ሰራተኞቹን አሰማርቶ ከስምምነቱ ውጭ እያሰራ ባለበት ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ተሰጠ ለተባለው ብድር ተጠያቂ ሊሆን ይችላልን?
9ኛ) በኢትዮጵያ ህግ እና ህገመንግስት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት የዓለም ባንክ ለሙስና እና ለወንጀል ድርጊቶች ማስፈጸሚያ ዓላማነት ከስምምነቱ ውጭ ለሚውል ለሰጠው የብድር ገንዘብ ክፍያ ዕዳ የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠያቂ ሊሆን ይችላልን?
10ኛ) በቀጣይነት የወያኔን የወሮበላ ዘራፊ የስብስብ ቡድን የሚተካው ዴሞክራሲያዊ መንግስት (መአጥፕ 3)/(PBS III) እየተባለ ለሚጠራው ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የመጣውን ብድር እና እየዋለ ያለው ግን ለሙስና እና ለሰብአዊ መብቶች ድፈፍጠጣ ለሆነ የገንዘብ ዕዳ ተጠያቂ ሊሆን ይችላልን?
በአጭሩ የኢትዮጵያ ህዝብ መአጥፕ 3/(PBS III) እየተባለ በሚጠራው ፕሮጀክት አማካይነት ከዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተሰጠ የተባለን የብድር ገንዘብ ከተደረገው ስምምነት ውጭ ለሙስና እና ለምዝበራ በመዋል እንዲሁም የወገኖቻችንን ሰብአዊ መብት በመደፍጠጥ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል በማለት በይፋ አለመቀበል እና ከዚህ ብድር ጋርም ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ማስወገድ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ሊኖረው ይችላልን?
በዚህ በአሁኑ ትችቴ ላይ እነዚህን ከላይ በዝርዝር የቀረቡትን ጥያቄዎች የመመለስ ዓላማ የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቸ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሳደርገው እንደቆየሁት ጥረት ሁሉ በህዝብ ስም እየተደረገ ያለውን ደባ በግልጽ ግንዛቤ እንዲወስዱበት እና በይፋ እንዲያውቁት ለማድረግ አጠቃላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በጣም ሙያዊ የሆኑ እና ቴክኒካዊ ትንታኔ የሚጠይቁትን ጉዳዮች ወደፊት በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ሲከበር፣ እና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሲገነባ እና ሲያብብ እንዲሁም አሁን በሀገሪቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለው አስቀያሚ የጥላቻ ከባቢ አየር እንደ ጉም ተገፍፎ ቆንጆ የሆነ ዘላቂነት ያለው የፍቅር እና የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ስሜት ወደሚሰፍንባት ኢትዮጵያ ስንሸጋገር እና ሰብአዊ መብቶቻችንን በአንድነት በጋራ በመቆም ማስከበር የምንችልበት ጊዜ ሲመጣ ለፍርድ ቤት ችሎት የሚቀርብ ይሆናል፡፡
የድብቅ ብድር የህግ መርህ፣
“የድብቅ ብድር” የሚለው የህግ መርህ ሀሳብ አንድ ሀገር በህዝብ ስም በማጭበርበር ገዥዎች ወይም የወሮበላ አምባገነን ገዥዎች በብድር ስም የመጣውን ገንዘብ በሙስና ለግል እና ለእራስ ጥቅም ለማዋል እየመነተፉ እና እየዘረፉ ወደ ቦርሳቸው እና ኪሳቸው እያጨቁ ባለበት ሁኔታ ህዝቦች እንደዚህ ያለውን ድብቅ ዕዳ በሀገር ስም የመክፈል ኃላፊነት የለባቸውም የሚል ነው፡፡ መሰረተ ሀሳቡ በመርህ ደረጃም ሆነ በተግባራዊ ይዞታው አንድ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ታዋቂ የሆነ ዘራፊ ሌባ ወይም ደግሞ አንድ የሙስና መዝባሪ ገንዘቡን እየዘረፈ ለግል ጥቅሙ ባዋለ ቁጥር የዚህ ሙስና ሰለባ የሆኑ ህዝቦች ለሚፈጠሩ የወንጀል ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸውን? ደግሞስ እነዚህን የግፍ ሰለባ የሆኑ ህዝቦችን ሁለት ጊዜ የችግሩ ሰለባ እንዲሆኑ ማሰብ እና ተግባራዊ ማድረግ ፍትሀዊ ነውን?
እንደዚሁም ደግሞ አንድ የህግ መሰረት የሌለው አገዛዝ በህዝቡ ስም ከፍተኛ የሆነ ዕዳ እንዲቆለል ቢያደርግ ሆኖም ግን ይህንን የህዝብ ዕዳ የሆነውን ገንዘብ የአገዛዙ አመራሮች እና የእነርሱ ግብረ አበሮች የግል መጠቀሚያ እና መጨፈሪያ ባደረጉት ቁጥር አንደኛ ባለስልጣኖቹ በብድር መልክ በመጣው ገንዘብ ከሚገኘው ልማት ተረጅው ህዝብ ተጠቃሚ እንዳይሆን በመከልከል እና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ህዝቡን እራሱን ከህግ አግባብ ውጭ የሰብአዊ መብቱን በመርገጥ እና በመጨቆን እያሰቃዩት ባለበት ሁኔታ የጥፋት ሰለባ የሆነው ህዝብ ሁለት ጊዜ የጉዳት ሰለባ መሆን ይኖርበታልን…? ህዝቡ በእራሱ ስም የመጣለትን የብድር ገንዘብ ለምንም ነገር ኃላፊነት የማይሰማው ገዥ አካል እያባከነ እና እየመዘበረ ባለበት ሁኔታ የጉዳቱ ሰለባ የሆነው ህዝብ ዕዳውን ለመክፈል የህግ ግዴታ ሊጣልበት ይችላልን?
ከታቀደለት ዓላማ ውጭ ህገወጥ በሆነ መልኩ ለዕኩይ ምግባር የዋለን ገንዘብ ድብቅ ብድር ዕዳ አከፋፈል የሚለው የህግ ተግዳሮት ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ ከ1898 የእስፓኝ እና የአሜሪካ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ነው፡፡ የድብቅ ብድር ዕዳ መርህ አሁን ያለውን ይዞታ ይዞ እንዲገኝ ያደረጉት በዓለም አቀፍ የገንዘብ ህግ ላይ ልዩ የሙያ ክህሎት እና እውቀት ባለቤት የሆኑት የሩሲያ የህግ ፕሮፌሰር የሆኑት አሌክሳንደር ናውሞቪች ዛክ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1927 ዛክ ስለዕዳ እና የገንዘብ ግዴታ አከፋፈል ሁኔታ የአመጽ አብዮትን ወይም ደግሞ ሰላማዊ የሆነ የመንግስት ለውጥን ተከትሎ ተኪ የሆኑ መንግስታት በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ስላለው ስምምነት የሚገልጽ ሰነድ አዘጋጅተዋል፡፡ ስምምነቶች መጠበቅ አለባቸው (pacta sunt servanda) የሚለው የዓለም አቀፍ ህግ አጠቃላይ መርህ ዕዳዎች ለአንድ ውሱን አገዛዝ፣ መሪ ወይም መንግስት ከመሆን ይልቅ የመንግስት ግዴታዎች (የፍትህ አካላቱ) ናቸው፡፡ እናም የመንግስት ለውጥ ቢደረግ ወይም በሌሎች ምክንያቶች መንግስት ቢወገድ እነዚህ ዕዳዎች የህዝብ ዕዳ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ይህ መርህ በርካታ የሆኑ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አሉት፡፡ አንድ መንግስት ተወግዶ ሌላ መንግስት በሚተካበት ጊዜ የቀደምቱን መንግስት ዕዳ አልከፍልም ብለው በማስወገድ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ መገበያየት እንዳይችሉ የንግድ ማዕቀብ ይጣልባቸዋል፡፡
ዛክ በመንግስት ፍላጎት ሳይሆን በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ዕዳ በሚኖርበት ጊዜ ከዋናው መርህ በተለየ መልኩ ሊስተናገዱ የሚችሉባቸው አሰራሮች ይኖራሉ በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አስቀምጠዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነቶችን የገንዘብ ዕዳዎች “dittes odieuses“ (“ድብቅ ብድር“) በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ ዛክ እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጣቸውን ያስቀምጣሉ፡
አንድ አምባገነን ለህዝቡ ፍላጎት ወይም ደግሞ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሳይሆን የእራሱን አምባገነናዊ አገዛዝ ለማጠናከር፣ እንደዚሁም የእርሱን አምባገነናዊ አገዛዝ በኃይል ለማስወገድ ጥረት የሚያደርጉትን ህዝቦች ጸጥ ለማድረግ ለሚያካሂደው ጭቆና፣ ወዘተ በማዋል የሚቆለለው እንደዚህ ዓይነቱ ዕዳ በህዝቡ ዘንድ ድብቅ ዕዳ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ዓይነቱን ዕዳ ህዝቡ እንዲከፍለው አይገደድም፣ ይልቁንም ይህ ዓይነቱ ዕዳ የአገዛዙ ዕዳ ነው፡፡ ይህ ዕዳ በመግዛት ላይ ላለው አምባገነን አካል የእራሱ የግሉ ዕዳ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ የአምባገነኑ ስርዓት ሲወድቅ አብሮ የሚወድቅ ዕዳ ነው…
ድብቅ ዕዳዎች ከህዝቡ ፍላጎት እና ጥቅም በተጻረረ መልኩ በተበዳሪዎች እውቀት ላይ ተመስርተው የሚፈጸሙ እና ለዚሁ ዓላማ የሚውሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉት ዕዳዎች ህዝቡ ጨቋኝ እና ሰብአዊ መብት ደፍጣጭ የሆነውን መንግስት ሲያስወግድ ለህዝቡ ጠቀሜታ እስካልዋሉ ድረስ አብረው የሚወገዱ ናቸው፡፡ ተበዳሪዎቹ ከህዝቡ ጋር ጥላቻ የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ያሳያሉ፣ አንድ ከአምባገነን አገዛዝ ነጻ የሆነ ህዝብ እነዚህ የአምባገነኑ አገዛዝ ድብቅ ዕዳዎች እንጅ የእራሴ ዕዳዎች አይደሉም ብሎ ላለመክፈል አሻፈረኝ ሊል እንደሚችል መገመት አይችሉም፡፡
ከዚም ሌላ አንድ አምባገነን ስርዓት በሌላ የጨቋኝነት መጠኑ ባነሰ ወይም ደግሞ በበለጠ አምባገነን ስርዓት ሲተካ እንኳ እነዚህ ድብቅ ዕዳዎች ቀደም ሲል ሲገዛ የነበረው አምባገነን አገዛዝ ድብቅ ዕዳዎች ለአዲሱ አገዛዝ ድብቅ ዕዳ ሆነው እንዲከፍል ግዳጅ ሊጣልበት አይችልም… ከዚህም ሌላ ከመንግስት ጋር ቀረቤታ ባላቸው በአንድ መንግስት አባላት ወይም ደግሞ በግለሰቦች ወይም በቡድኖች አማካይነት በህዝቦች ስም የሚገኘውን ብድር ከህዝቦች ጥቅም ጋር በማይገናኝ መልኩ ለእራሳቸው ጥቅም እና ፍላጎት ብቻ የሚያውሉት ከሆነ እንደዚህ ያለውን ዕዳ በዚህ ድብቅ ዕዳ በሚለው የዕዳ አመዳደብ ክፍል ውስጥ መመደብ ይቻላል፡፡
የዛክ ንድፈ ሀሳብ ወይም ህልዮት ነጻነታቸውን በተቀዳጁት የአፍሪካ ሀገሮች ላይ እና በድህረ ነጻነት ጊዜ በወታደራዊ አገዛዝ መዳፍ ስር ሲተዳደሩ በነበሩ ወይም የሲቪል አምባገነን ሀገሮች ላይ ከፍተኛ እንደምታን ሊያሳይ በሚችል መልኩ ሲተገበሩ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ነጻነታቸውን ተቀዳጅተው የሚኖሩ የአፍሪካ ሀገሮች ቀደም ሲል በቅኝ ግዛት ዘመን በቅኝ ገዥ አለቆቻቸው አማካይነት ሲቆለሉ የቆዩትን ዕዳዎች የመክፈል ኃላፊነት ሊጣልባቸው ይችላልን? አዲሶቹ የነጻነት ታጋይ መንግስታት ቀደም ሲል በመራራው ትግላቸው ቅኝ ገዥ የነበሩትን ሀገሮች አገዛዝ አሽቀንጥረው ጥለው የእራሳቸውን አዲስ አስተዳደር በመመስረት ህዝቦቻቸውን ማስተዳደር በሚጀምሩበት ጊዜ ቀደም ሲል የቅኝ ግዛት አለቆቻቸው ሲያከማቹት የነበሩትን ዕዳ እንዲከፍሉ ዓለም አቀፋዊ ህግ ግዴታ ሊጥልባቸው ይችላልን? በድህረ ቅኝ አገዛዝ ጊዜ በአፍሪካ በአንድ በተወሰነ ሀገር በወታደራዊ ወይም ደግሞ በሲቪል አምባገነናዊ አገዛዞች (ከህዝቡ ፈቃድ ውጭ) በአምባገነናዊነት ኃይልን በመጠቀም በህዝቡ ስም ያገኙትን እና የተበደሩትን ገንዘብ ለእራሳቸው የድሎት ቸበርቻቻ ህይወት እንዲሁም ህዝቡ ለመብቱ እንዳይታገል እና የስልጣኑ ባለቤት እንዳይሆን ለመጨቆኛነት እና ለማሰቃያነት ወይም ደግሞ በብድር የተገኘውን ገንዘብ በዘመዶቻቸው ወይም ደግሞ በግብረ አበሮቻቸው ስም በቀጥታ ውጭ ሀገር ላለ የሂሳብ አካውንታቸው ገቢ እንዲደረግ ቢልኩት እና ለግል ጥቅማቸው ቢያውሉት ህዝቡ ይህንን የብድር ዕዳ እንዲከፍል ግዴታ ሊጣልበት ይችላልን? በአንድ በአፍሪካ አህጉር ባለች ሀገር ላይ ያለ ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት እርሱ የተካውን አምባገነናዊ መንግስት ዕዳ እውቅና እንዲሰጥ ወይም ደግሞ እንዲከፍል የህግ ግዴታ ሊጣልበት ይችላልን?
አንድ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ያለች ሀገር “ድብቅ እዳን” አልከፍልም የሚል ጥያቄ ብታነሳ እና እንዲያውም ያንን ዕዳ አላውቅም ብላ ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆን ለማስወገድ ብትነሳ ማን ነው ያንን ዕዳ ቀደም ሲል አግባብ በሆነ መልኩ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል የባከነ እና ለተቀባዩ ሀገር ህዝብም ምንም ዓይነት ጠቀሜታ ያላደረገ ነው ብሎ ያለውን እውቀት በመጠቀም ወይም ደግሞ ተበዳሪው በጥፋተኝነት ሳይጠየቅ ያለ ስለሆነ እንዲጠየቅ የሚል ሀሳብን ሊሸከም የሚችል ኃላፊነት ያለው? አበዳሪ ሀገሮች ወይም ተቋሞች ኃላፊነታቸውን በመወጣት ሂደት ላይ ሲባል ያበደሩት ገንዘብ በስምምነቱ መሰረት ለታለመለት ዓላማ የዋለ እና ያልዋለ መሆኑን ሊያረጋግጡ የሚችሉበት የህግ አግባብ ሊኖር ይችላልን? በአምባገነኖች መዳፍ ስር በጭቆና ላይ ያሉ ህዝቦችን ፍላጎት እና ጥቅም ከግንዛቤ ባላስገባ መልኩ አምባገነኖቹ ገዥዎች በህዝቡ ስም ያገኙትን የብድር ገንዘብ የህዝቡን ፍላጎት እና ጥቅም ወደ ጎን ትተው ለሰብአዊ መብት ረገጣ እና ጭቆና ተግባራት ላዋሉት ገንዘብ ህዝቡ በዕዳ ሊጠየቅ ይችላልን?
ይህ “የድብቅ ዕዳ” ጉዳይ ለኢትዮጵያ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሚሆን ነገር ነው ምክንያቱም ኢትዮጵያ በዕዳ አዘቅት ውስጥ ተዘፍቃ በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጭ ጣዕረሞት ላይ የምትንጠራወዝ ምስኪን ሀገር ናት፡፡ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2014 ያወጣው ዘገባ (አይኤምኤፍ ሀገራዊ ዘገባ ቁጥር 14/303) የሚከተለውን ያስነብበናል፡
የመንግስት ዋና ዋና ዘርፎች ተካትተው በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ መጠን እ.ኤ.አ በ2013/14 የመጀመሪያዎቹ ወራት 12.2 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2012/13 መጨረሻ አካባቢ ደግሞ 11.2 ቢሊዮን ዶላር በመሆን ከዚህም በተጨማሪ ሌላ የብዙሀን ሀገሮች የብድር ስምምነቶችን የሚያንጸባርቅ መሆኑን የሚያመላክት ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012/13 እና በ2013/14 የመጨረሻዎቹ ወራት አካባቢ ከተለቀቀው የብድር ገንዘብ ውስጥ (ወደ 2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው የኢትዮጵያን አየር መንገድ ጨምሮ)፣ አንድ ሶስተኛው ለትራንስፖርት አገልግሎት እና መገናኛ ክፍለ ኢኮኖሚ ዘርፍ፣ 18 በመቶ የሚሆነው ለኤሌክትሪክ ኃይል እና ተዛማጅ ፕሮጀክቶች እንዲሁም 12 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለአውራ ጎዳናዎች የተመደበ ነበር፡፡ የዕዳ ቅነሳ ክፍያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመሩ መጥተዋል ሆኖም ግን ምቹ የሆኑት የዕዳ ክፍያዎች ሁኔታ የዕዳ ክፍያው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርገውታል፡፡ (“የዕዳ ክፍያዎች ሁኔታ” ማለት በቀላል አነጋገር ዝቅተኛ የወለድ መጣኔ፣ ረዥም የመክፈያ ጊዜ፣ የቴክኒክ ዕገዛ፣ ወዘተ ማለት ነው፡፡ በእኔ የተጠራጣሪነት አስተሳሰብ አዳ ማቃለል ማለት ኢትዮጵያ በዕዳ መሃል ውቅያኖስ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እስከምትሰምጥ ድረስ ቆሞ ማየት ነው፡፡)
እንደ የዓለም ባንክ ዘገባ እ.ኤ.አ ከ2010 – 2014 የነበረው የኢትዮጵያ ዕዳ 12.6 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ እንደ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዘገባ እ.ኤ.አ የ2013 የኢትዮጵያ የመንግስት የተጣራ ዕዳ (ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት መቶኛ) 20.165 መቶኛ ነበር፡፡ ይህ አጠቃላይ የሆነ የመለኪያ መስፈርት ሊሳሳት ይችላል፣ እናም ትክክለኛ የዕዳ መጠኑን ዝቅ አድርጎ ሊያሳይ ይችላል፡፡ ዕዳን ከገቢ ግብር ጋር ማነጻጸሩ ደግሞ የእያንዳንዱን ሀገር የመንግስት ገንዘብ ዕዳ ሸክም እውነተኛነት የበለጠ ሊገልጸው ይችላል፡፡
ዛክ የዕዳ ሸክሙን የመቋቋም ችሎታ ያበደሯቸው ብድሮች በብድሩ ወቅት ከነበሩ ስምምነቶች የዕዳ ክፍያ ግዴታ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ እና በአበዳሪዎች ላይ የሚወድቅ እንዲሁም ህጋዊ የሆነ የህዝብን ዓላማ ላለማሳካት የሚውል ስለሆነ የዕዳ ሸክሙ በአበዳሪዎች ትከሻ ላይ የሚወድቅ ይሆናል በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፡፡ እነዚህ አበዳሪዎች ያለባቸውን የዕዳ ሸክም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ፊት ቆመው ማስረዳት ካልቻሉ ዕዳው ግዴታ የሚገባበት ብቻ አይደለም የሚሆነው ሆኖም ግን ከዚህም በላይ በመሄድ ባዶ እና ተፈጻሚነት የማይኖረው ሆኖ ውድቅ ይደረጋል፡፡
በአሁኑ ዘመን ያሉ በርካታ የህግ ምሁራን ዕዳዎች ምንም ዓይነት የህዝብን ፍላጎት እና ጥቅም የማያካትቱ ሆነው ከተገኙ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ድብቅ ዕዳዎች ተብለው ውድቅ እንዲደረጉ በማድረግ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም በማለት ትምህርት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ፓትሪሲያ አዳምስ ፕሮቤ ድብቅ ብድር፡ “ጥብቅ የሆነ ስምምነት የሌለበት ብድር፣ ሙስና እና የሶስተኛው ዓለም የአካባቢ ስነምህዳር ውርስ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሀፋቸው ላይ የሶስተኛው ዓለም ዕዳ ህጋዊነት የድብቅ ዕዳ እና የህግ የበላይነት መከበር ከሚለው መርሆ አንጻር መመርመር ይኖርበታል በማለት በሚያሳምን መልኩ የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፡፡ ለድብቅ ዕዳ እንዲህ የሚል ቀላል የመመርመሪያ ዘዴ አስቀምጠዋል፡ “ማን፣ ምንድን እና ለማን አበደረ፣ ገንዘቡ የት ነው የሄደው፣ እዚያ ምን ያደርጋል እና በአሁኑ ጊዜ የት ነው ያለው?“
ስለድብቅ ዕዳ የማመልከቻ መርሆ እና ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር ያለው አንጻራዊ ጠቀሜታ፣
የድብቅ ዕዳ ጽንሰ ሀሳብ የሳዳም ሁሴንን ድብቅ ዕዳ በአዲሱ የኢራቅ መንግስት መከፈል እንደሌለባቸው እ.ኤ.አ በ2003 በማንም ሳይሆን አስደናቂ በሆነ መንገድ በዩኤስ የግምጃ ቤት ሚንስተር እና በሌሎች የዩኤስ ታላላቅ ባለስልጣኖች አጫሪ የሆኑ ሀሳቦችን አፍልቀው ነበር፡፡ ያ ድብቅ አዳ ሀሳብ በዩናይትድ ስቴትስ መንግስት መነሳቱ አጅግ በጣም የሚያስገርም ነገር ነበር፡፡
በእርግጠኝነት ዩናይትድ ስቴትስ በድብቅ ዕዳ እንቅስቃሴ ታላቅ የሆነ ፈጠራን ተጎናጽፋለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1898 የእስፓኝ እና የአሜሪካንን ጦርነት ፍጻሜ ተከትሎ ተደርጎ በነበረው የሰላም ስምምነት የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ስኬታማ በሆነ መልኩ ኩባን ቅኝ ግዛት አድርጋ እና ከኩባ ህዝብ ስምምነት ውጭ በሆነ መልኩ ስትገዛ እና የሰብአዊ መብት ረገጣ በማካሄድ የኩባን ህዝብ ደህንነት ስታቃውስ በቆየችው በእስፓኝ አማካይነት ሲቆለል ለቆየው የኩባ ዕዳ ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች ኩባ ተጠያቂዎች ሊሆኑ አይችሉም ብላ ተከራከረች ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ያ ዕዳ የኩባን ህዝብ ጥቅም በማያስጠብቅ መልኩ እና እንዲያውም ለኩባ ህዝብ ጠላት በሆነ ኃይል የኩባ ህዝብ መብቱን ለማስጠበቅ የአመጽ እንቅስቃሴዎችን እያካሄደ ባለበት ጊዜ ያንን አመጽ ለማስቆም እና ለማዳፈን ይወጣ የነበረ ዕዳ በመሆኑ ምክንያት ለኩባ ህዝብ ጥቅም ያልዋለ ስለሆነ የኩባ ህዝብ ለዚህ ዕዳ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም በማለት የክርክር ጭብጧን አቅርባለች፡፡ እስፓኝ በፓሪስ ስምምነት መሰረት የኩባን ዕዳ እየመረራትም ቢሆን ሳትወድ በግድ ለመቀበል ተገድዳለች፡፡
ሌሎች መንግስታትም የዩናይትድ ስቴትስን አመክንዮ እና መርሆዎች አቋም በመያዝ ከድብቅ ዕዳ የጥፋተኝነት ተጠያቂነት ነጻ ሊያደርግ የማያስችል አቋምን በመያዝ በዋናነት በስራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1917 ቄሳር ኒኮላስ ሁለተኛ በእራሳቸው ፈቃድ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ በአሌክሳንደር ከርነስኪ መሪነት የተቋቋመው የሩሲያ ጊዚያዊ መንግስት የቄሳሮቺን ዕዳ አክብሮ ተቀበለ፡፡ በዚያው ዓመት በኦክቶበር የከርነስኪ መንግስት በኃይል እንዲወገድ ሆኖ በቦልሸቪኮች (በኮሚኒስቶች) መንግስት ተተካ፡፡ እ.ኤ.አ በ1918 የቦልሸቪክ (ሶቪዬት) መንግስት በዛክ የድብቅ ዕዳ ጽንሰ ሀሳብ ላይ እምነትን በማሳደር እንዲህ የሚል አዋጅ አወጀ፡ “ሁሉም የውጭ ብድሮች ከዚህ በኋላ ያለምንም ማቅማማት ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ነገር ቢሆንም እንኳ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡“ እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጦቻቸውን አጠናክረዋል፡ “በአብዮት የሚከሰቱ መንግስታት እና ስርዓቶች የወደቁ መንግስታትን ህጎች የመጠበቅ እና የማክበር ግዴታዎችን ለመፈጸም አይገደዱም፡፡“ ሶቪየቶች የቄሳሩ መንግስት ዕዳዎች የቄሳሩ እና የአገዛዙ የግል ዕዳዎች ናቸው እናም ወደ አዲሱ የሶቪዬት መንግስት ሊሸጋገሩ አይችሉም ብለው ነበር፡፡
ስለ ድብቅ ዕዳ አብዛኛውን ጊዜ እንደ ህግ ሆኖ የሚቀርበው በኮስታሪካ እና በታላቋ ብሪታንያ መካከል የነበረውን ውዝግብ እንዲሰረዝ ያደረገው ስምምነት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1917 የኮስታሪካ የወታደራዊ አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ቁንጮ የነበሩት ጆሴ ፌዴሪኮ ቲኖኮ ግራናዶስ (ቲኖኮ) እና የእርሳቸው ወንድም ወታደራዊ አምባገነንነትን አቋቋሙ፡፡ ቲኖኮ በሁለቱም የኮስታሪካ የህግ አውጭ ምክር ቤቶች ህገመንግስታዊ መስፈርትን ሳያሟሉ እና አስፈላጊውን ድርጊት ሳይፈጽሙ በሰከባ ለጥቅም በመሮጥ ከአንድ ትርፋማ ከሆነ ከእንግሊዝ የዘይት ኩባንያ ጋር የስምምነት ውል ፈጸሙ፡፡ ቲኖኮ በእራሳቸው ፊርማ እና በአንድ ህግ አውጭ ምክር ቤት በማጸደቅ ለኩባንያው ስምምነት ሰጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1919 የእርሳቸው ወንድም ከተገደሉ ጥቂት ወራት በኋላ ቲኖኮ ስልጣናቸውን በእራሳቸው ፈቃድ ለቀቁ፡፡ እርሳቸውን የተኩት ጁአን ባውቲስታ ኩይሮ ያለፈው መንግስት የኮንትራት ውሉን በሚፈርምበት ጊዜ ከተሰጠው ህጋዊ ስልጣን በላይ ተጠቅሟል በማለት ሰረዙት፡፡ የኩይሮ መንግስት የኮስታሪካንን ህጎች የሚሽሩ ስምምንነቶች የሚሽር ህጎች አረቀቀ፣ እናም ቀደም ሲል ቲኖኮ ከካናዳ ሮያል ባንክ ጋር ያደረገውን ስምምነት እና ዕዳ በሚመለከት መመርመር እና ተግባራዊ እንዳይሆን ጥረቱን ቀጠለ፡፡
የዩኤስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሃል ዳኛ ታፍት በዳኘነት በተሰየሙበት ችሎት የኮስታሪካው ጉዳይ ከቀረበ በህዋላ ብይን ሰጡ” “… ሁሉም ዓይነት ነገሮች በዚህ ላይ የተደረጉ የስምምነት ውሎች እና ድርጊቶች ህጸጽ የሞላባቸው እና እንከን በእንከን ላይ የተደራረቡ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ከሮያል ባንኩ ጋር በተዘዋዋሪነት የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ማስቀመጥን በተመለከተ የሚፈቅድ የህግ ስልጣን የለም፡፡ ይህንን ገንዘብ ጡረታ የወጡት ቲኖኮ ለጥገኝነት ወደሌላ ሀገር ከተሰደዱ በኋላ ለግል ህይወታቸው መደጎሚያ እንደሚጠቀሙበት ባንኩ በሚገባ ተገነዘበ፡፡ ለዚህ ጉዳይ ጥገኝነትን ጠይቀው በሌላ ሀገር ለሚኖሩት የቀድሞ መሪ ገንዘቡ እንዲከፈላቸው ያደረገውን መንግስት ተጠያቂ እንዲሆን አልተደረገም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለወንድማቸው የተከፈለውም ገንዘብ ጉዳይ አንድ ዓይነት ነው… ሁሉም አጋጣሚዎች እና የምርመራ ውጤቶች እንደሚያመላክቱት የሮያል ባንክ ገንዘቡን የሰጠው ለህጋዊ የመንግስት ዓላማ ማስፈጸሚያ ሳይሆን ለግሰቦች መጠቀሚያ እና መዝናኛ መሆኑን ዳኘተዋል።
የኮስታሪካ መንግስት ገንዘቡን ህጋዊ ለሆኑ ዓላማዎች ማዋል እንደነበረበት በመግለጽ የሮያል ባንክ የዚህን የኃላፊነት ሸክም መውሰድ እንዳለበት ዳኛው ወሰነዋል፡፡ የሮያል ባንኩ በዚህ መሰረት ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም ነበር፣ ስለሆነም የታላቋን ብሪታንያ በካናዳ የሮያል ባንክ ስም የያዘችውን የይገባኛል መብት ውድቅ አድርጓል ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የተፈጸመው ውል ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መንገድ እና ስልጣኑን የኮስታሪካ ህገመንግስት ባልሰጠበት ሁኔታ ዝም ብሎ ኃይልን በመጠቀም የተደረገ ስለነበረ ነው፡፡
ለድብቅ ዕዳ ጉዳይ የበለጠ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተፈጸመው ዋና አሳዛኝ ምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ያደረገውን በምሳሌነት ማየት የበለጠ ጠቃሚነት አለው፡፡ በበርካታ መሪዎች እና ድርጅቶች የኬፕታውንን ጳጳስ እና የእውነት እና የእርቅ አፈላላጊ ከሚሽንን ጥሪ እና ዘመቻ ጨምሮ በአፓርታይድ የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ ጊዜ የተፈጸሙ ድብቅ ዕዳዎች ጉዳይ እንዲታይ ተደጋጋሚ የሆነ ጥቆማ ቢደረግም አሁን ያለው የደቡብ አፍሪካ መንግስት አንድም እርምጃ ሳይወስድ ሁሉንም ነገር ዝም በማለት አልፎታል፡፡ በአፓርታይድ ጊዜ የተፈጸሙት ድብቅ ዕዳዎች ምንም ዓይነት የህግ አግባብ የሌላቸው ስለነበሩ የጥቂት ነጮች መንግስት ለጥቂት ነጮች የሰጣቸው ብድሮች እንዲሁም በእነዚህ ህገወጥ ድርጊቶች በመጠቀም ጥቁር ህዝቦችን ሲጨቁኑ እና የምጣኔ ሀብታቸውን ሲበዘብዙ ስለነበር እነዚህ ድብቅ ዕዳዎች እንዲሰረዙ እና እንዲወገዱ በማለት የክርክር ጭብጦቻቸውን ያቀርቡ ነበር፡፡ በአፓርታይድ ገዥ አካል ድብቅ ዕዳ ብሎ ከተሰጠው ገንዘብ የበለጠ ህገወጥ ስራ የለም ግን አሁን ያለው መንግስት ለመከታተል ፈቃደኛ አይደለም፡፡
የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (አብኮ) የደቡብ አፍሪካ መንግስት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች በሚደረግበት ተጽዕኖ ምክንያት ወደፊት የውጭ መዋዕለ ንዋይ በመሳብ ረገድ ችግር ይፈጥርብኛል በሚል እሳቤ እና ፍርሀት በመመርኮዝ ሁሉንም ጥሪዎች በሙሉ ባለመቀበል ውድቅ አደረጋቸው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ግን በድህረ አፓርታይድ የደቡብ አፍሪካ ዘመን እንዲህ የሚሉ አሳማኝ የሆኑ ትንታኔዎች ተሰጥተው ነበር፡
“የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት እጅግ በጣም አናሳ ነው – በአፓርታይድ መንግስት መዋዕለ ንዋይ ከሚያፈስሱ ኩባንያዎች ሁለት ሶስተኛው ትርፍ ብቻ ወደ ውጭ ፈሰስ ይደረጋሉ፡፡ እናም አዲሱ ብድር ከክፍያ ጋር የተገናዘበ አይደለም- በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ደቡብ አፍሪካ ወደ ሀገር ውስጥ ከምታስገባው ገቢ የበለጠ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጭ አስወጥታለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ዘመን መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ትርፍ ከሀገር ውስጥ እንዳይወጣ ለመገደብ እና በቀላሉ የአፓርታይድን ድብቅ ዕዳ ለማስወገድ እና ለመሰረዝ ወይም ደግሞ የ10 ዓመታት የማዘግየት ጥያቄ ቢቀርብም እንኳ በ10 ቢሊዮን ዶላር የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የውጭ እርዳታ 1.1 ቢሎዮን ዶለር ብቻ ነበር፡፡ እርዳታ ቢቀንስም እንኳ ደቡብ አፍሪካ 8.9 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ታገኝ ነበር፡፡“
እ.ኤ.አ መጋቢት 2014 ፎርብስ የተባለው መጽሄት እንዲህ የሚል ዘገባ አቀረበ፣ “የደቡብ አፍሪካ ጠቅላላ የውጭ ዕዳ ወይም ደግሞ በውጭ አበዳሪዎች ያለ ዕዳ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በ250 በመቶ እንዲሁም ከ2008 ጀምሮ ደግሞ በ87 በመቶ ጨመረ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ዕዳ በጠቅላላው 136.6 ቢሊዮን ወይም ደግሞ የሀገሪቱን የሀገር ውስጥ ምርት 38.2 በመቶ ይይዛል…“
የድብቅ ዕዳን ጽንሰ ሀሳብ ከግንዛቤ በማስገባት በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስኬታማ የሆኑ ተመሳሳይ የክርክር ጭብጦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንድ አስገራሚ የሆነ ጉዳይ እ.ኤ.አ በ1947 በጣሊያን ሀገር የተደረገውን የሰላም ስምምነት ያካትታል፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት የፍራንኮ – ጣሊያን የዕርቅ ኮሚሽን እንዲህ የሚል ሕጋዊ ዉሳኔ አድርገው ነበር ። “ለጦርነት ጉዳዮች ወይም ደግሞ በመጀመሪያ ጊዜ ወረራ የተፈጸመባትን ሀገር ግዛት ለማስፋፋት እና ወዲያው ነጻነቷን የተቀዳጀቸን ሀገር በሚመለከት ከወደቀው መንግስት ጋር የሚደረግ የዕዳ ስምምነት የሚተካውን ወይም ደግሞ የተሻሻለውን መንግስት ዕዳውን እንዲከፍል አይገደድም፡፡ አገዛዙ በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ከተደረገው የኢጣሊያን ወረራ ጋር ጎን ለጎን ሊሄድ የሚችል ኢጠሊያን በኢትዮጵያ ላይ የነበራትን የበላይነት ለማረጋገጥ ስትል ስታወጣው የነበረውን ዕዳ ከነጻነት በኋላ ኢትዮጵያ መክፈል አለባት ተብሎ ሊታሰብ የሚችል አይሆንም፡፡“
ስለድብቁ ህወሀት ድብቅ ዕዳ ምን መደረግ አለበት?
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ስለሰጠው ብድር የነጻ እና ገለልተኛ የሆነ የዕዳ ምርመራ አስፈላጊነት፣
ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ በተበደረችው ግዙፍ የሆነ የዕዳ ገንዘብ ላይ ምርመራ/audit ማድረግ ለሚችል ነጻ ለሆነ የመርማሪ አካል ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ (ይህንን ስል አንባቢዎቸ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይዙ አሳስባለሁ፡ የዓለም ባንክ ብድሮች ላይ ነጻ የሆነ ምርመራ ለሚያደርግ አካል ጥሪ በማስተላልፍበት ጊዜ መስማት የማይፈልገው የዓለም ባንክ ድምጽ አልባው አዳራሽ ጉዳዩን አዳምጦ ተግባራዊ ያደርገዋል የሚል እምነት ኖሮኝ አይደለም፡፡ ደንቆሮዎች እንደሆኑ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ (ምንም መስማት ለማይፈልገው አካል ንግግር እያደረግሁ መሆኔ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ለነገሩ ላለፉት ስምንት ዓመታት ለድንጋይ ስትናገር ጊዜ አሳልሃል የሚሉ አይጠፉም፡፡) ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ለጉልበተኛው የዓለም ባንክ መናገሬን አላቆምም፡፡ አሁንም ቢሆን ከሁሉም በላይ የዓለም ባንክ ላለፉት የመጨረሻዎቹ ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ለኢትዮጵያ የሰጠውን ብድር ነጻ የሆነ ምርመራ የሚያደርግ አካል አጥብቄ በድጋሜ እጠይቃለሁ፡፡ በነጻው የምርመራ አካል ትኩረት ተደርጎ ሊታዩ የሚገባቸው ከብዙዎቹ ጥቂቶች የሚከተሉት ናቸው፡
1ኛ) የብድሮቹ የመጀመሪያዎቹ ስምምነቶች ሰነዶች፣
2ኛ) የተከፈለው የወለድ መጠን፣
3ኛ) በብድር የተገኘው ገንዘብ ለምን ዓላማ እንደዋለ፣
4ኛ) ደረጃውን በጠበቀ ዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ አካውንቲንግ ስርዓት እና በዓለም ባንክ በእራሱ የአካውንቲንግ የአሰራር ስርዓት በምርመራ ስራው ውስጥ ሊካተት የማይችለው ጠቅላላ ገንዘብ፣
5ኛ) በብድሮች ላይ ትዕዛዝ የሰጡ እና ስምምነቶችን የፈረሙ እንዲሁም በዕዳዎች ላይ ስምምነት ያደረጉ ሰዎች ማንነት፣
6ኛ) የዓለም ባንክ ስምምነቶቹ በሚፈረሙበት ጊዜ የነበረው ሚና እና የሁሉም ስምምነቶች ምንነት፣
7ኛ) የዓለም ባንክ ባለስልጣኖች እና ሰራተኞች ብድሮችን ለማስተዳደር ይጠቀሙባቸው የነበሩ የብድር ስምምነቶች፣ ፖሊሲዎች፣ ደንቦች እና ተሞክሮዎች፣
8ኛ) የዓለም ባንክ የገንዘብ፣ እና የብድር ሰነዶች እና መዝገቦች ትክክለኛነት፣ አስተማማኝነት እና ምሉዕነት፣
9ኛ) የሀሰት ሰነዶች አንዳይኖሩ፣ የማቴሪያል ቆጠራ ስህተትነት ወይም በዓለም ባንክ ሰነዶች እና መዝገቦች ላይ ጉልህ የሆኑ ስህተቶች በቅርቡ ተቋቁሞ የምርመራ ስራውን ሲያከናውን በነበረው የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን (Inspection Panel) የምርመራ ውጤት ላይ በጉልህ ተንጸባርቀዋል፣ (የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን የምርመራ ውጤት በዳመና የተሸፈነ ተራራ ጋራ ጫፍ ይሆን?
10ኛ) የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ለሰጠው ብድር የውስጥ የገንዘብ እና አስተዳደራዊ ቁጥጥር አሰራሮች ውጤታማነት፣ እና ሆን ተብለው ወይም ደግሞ በእንዝላልነት የሚታለፉትን (ያፈጠጡ እና ያገጠጡ ውሸቶች) አሰራሮች፣ ፖሊሲዎች እና የአሰራር ሂደቶች በስራ ላይ ስለመዋል አለመዋላቸው፣ ለማስረጃ ያህልም የዓለም ባንክ ሸፍጥን እና ቅሌትን በተላበሰ መልኩ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአማካይ በየዓመቱ የ10.7 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግባለች የሚለው የቅጥፈት ዘገባ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
የዓለም ባንክ! መአጥፕ 3/PBSIII የተባለው ፕሮጀከት ብድር (እንዲሁም ሌሎች ብድሮች) ሁሉ ድብቅ ብድሮች መሆናቸውን ዕወቅ፣
የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሰጣቸው ብድሮች ወደፊት በትክክለኛው ቦታ እና ጊዜ ተመርምረው እና ተጣርተው ውጤቶቻቸው ድብቅ ብድሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ የባንኩ ባለስልጣኖች የእኔን በተስፋ የተሞላ እና ድፍረት የተቀላቀለበት ሀሳብን ተመልክተው በሳቅ በመንከትከት ከወንበሮቻቸው ተስፈንጥረው ሊወድቁ ይችላሉ፡፡
ኢትዮጵያ “የንግድ አዳራሽ” እድትሆን አበርትተው ሲሰሩ የቆዩት “ገንዘብ ለዋጮች” በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየሳቁ ወደ ባንካቸው ይሂዱ፡፡ እኛ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመከራ በዳረገው እና አጥንቱ እስኪቀር ድረስ በመጋጥ የተቆለለበትን ያልተጠቀመበትን ዕዳ ደም ለመበቀል፣ ያፈሰሰውን ላብ እና እንባ ለማበስ ለእውነት እና ለፍትህ ስንል ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንሄዳለን፡፡
የዓለም ባንክ የድብቅ ብድር እንዲሰረዝ እና ደብዛው እንዲጠፋ ማድረግ የኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ ፋይዳዎች ብቻ ሳይሆን የሞራል ጥያቄም ጭምር ነው፣
የዓለም ባንክ እራሱን ህወሀት እያለ የሚጠራው የወያኔ የወሮበላ ሰብስብ ቡድን ስልጣንን በህዝብ ድምጽ በምርጫ ካርድ ሳይሆን በጠብመንጃ ኃይል እንደተቆጣጠረ እና ከዚያም በኋላ ሸፍጥ በተቀላቀለበት መልኩ የህዝብ ድምጽን በምርጫ ሰበብ እየዘረፈ እና እያጭበረበረ፣ ንጹሀን ዜጎችን እያፈነ፣ ወደ ማጎሪያ አስር ቤቶች እያጋዘ፣ እያሰቃዬ እና አየገደለ ከህዝቦች ፍላጎት ውጭ እንደ መዥገር በስልጣን ላይ ተጣብቆ መኖሩን አሳምሮ እያወቀ ባንኩ ለወሮበላው ቡድን መአጥፕ 3/PBSIII እየተባለ ለሚጠራው ፕሮጀክት ብድር ብሎ የሰጠውን ገንዘብ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማያውቀው እና ዕዳውም እንዳልሆነ በቂ እና አሳማኝ የሆኑ መረጃዎችን ለዓለም አቀፍ የፍትህ አካላት ማቅረብ እንችላለን፡፡(ለመሆኑ በምንኖርባት መሬት በምትባለው ፕላኔት ላይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በየትኛው ሀገር ውስጥ ነው 99.6 በመቶ ድምጽ በማምጣት ገዥ ፓርቲ ሆኖ ሀገርን የሚመራው? ሌላ የትም ሳይሆን ኢትዮጵያ በምትባል ጉደኛ ሀገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የዚምባብዌው የ91 ዓመቱ የዣዡ አምባገነን መሪ ሮበርት ሙጋቤም እንኳ ቢሆኑ የመጨረሻውን ምርጫ አካሂደው አሸነፍኩ ያሉት በ61 በመቶ የድምጽ ውጤት ነበር፡፡)
የዓለም ባንክ መአጥፕ 3/PBSIII እየተባለ በሚጠራው ፕሮጀክት ስም ለወያኔ የወሮበላ ስብስብ ቡድን የሰጠውን የብድር ገንዘብ እና አሁንም ገንዘቡ ህገወጥ በሆነ መልኩ እየባከነ እና እየተመዘበረ ባለበት ሁኔታ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን ህግ እና የባንኩን የእራሱን ፖሊሲዎችን በመጣስ መጠነ ሰፊ የሆነ ህዝቦችን የማፈናቀል፣ የማጋዝ እና የግዳጅ የሰፈራ ፕሮግራሞችን የማካሄድ፣ ከህግ አግብባ ውጭ የዜጎችን ንብረቶች የመንጠቅ እና በጋምቤላ አካባቢ ለበርካታ ዓመታት በቋሚነት ሲኖሩ ለነበሩት ህዝቦች ሞት መንስኤ በመሆን እኩይ ድርጊቶችን በማከናወን ላይ እንደሆነ እየቀጠለበት ያለውን ሁኔታ ለህግ ለማቅረብ ከበቂ በላይ ማስረጃ እና አሳማኝ ነገሮች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን እራሱ ባንኩም በሚገባ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ (እራሱ የዓለም ባንክ እራሱ ያቋቋመው የምርመራ ቡድን/Inspection Panel “ኢትዮጵያ፡ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ 3ኛ ዙር ፕሮጀክት (P128891)/Ethiopia: Promoting Basic Services Phase III Project (P128891)“ በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የምርመራ ዘገባ የመጀመሪያ ደረጃ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል እና በጋምቤላ የገንዘብ ብድሩ ትክክለኛ ላልሆኑ ህገወጥ ድርጊቶች እየዋለ ያለ መሆኑን ሊያስገነዝብ የሚችል ጠቃሚ ሰነድ ነው፡፡)
የዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ ያለው የባንኩ ተወካይ እንዲሁም በባንኩ ዋና ጽ/ቤት ያሉት የባንኩ ፖሊሲ አውጭዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ያበደሩት ገንዘብ የእራሳቸውን የባንኩን ፖሊሲዎች በሚጻረር መልኩ የህዝቦችን ደህንነት የሚጎዱ በርካታ ጉዳቶች ሲከሰቱ እየተመለከቱ በእንዝህላልነት ዝም የማለታቸውን ሁኔታ የሚያስረዱ በቂ እና አሳማኝ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ፡፡ (የዓለም ባንክ የምርመራ ቡድን ዘገባ ሆን ተብሎ እና እያወቁ የባንኩን ፖሊሲዎች፣ ደንቦች እና ተሞክሮዎች ወደ ጎን በመጣል በገንዘቡ ብክነት እና በህዝቦች ላይ እየተፈጸሙ ላሉት የሰብአዊ መብቶች ረገጣ የመጀመሪያ ማስረጃዎች ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡)
የዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ ያለው የባንኩ ተወካይ (በዓለም ባንክ ዋና ጽ/ቤት ያሉት ፖሊሲ አውጭዎች በትክክል እያወቁ ወይም ደግሞ ጥፋተኛ ላለመባል) መአጥፕ 3/PBSIII እየተባለ የሚጠራው ፕሮጀከት በጋምቤላ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአኟክ ማህበረሰብ ላይ በተከታታይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ እየታወቀ ባንኩም በፕሮጀክቱ ዙሪያ ሶስት የጋራ የምክክር ውይይቶችን እና የአፈጻጸም ድጋፍ ተልዕኮዎችን ሲያካሂድ የባንኩ ድክመቶች እና እንዝህላልነት እንዳይታወቅ ለማድረግ በሚል ዕኩይ ምግባር በህዝቡ ላይ ስለደረሱት እና እየደረሱ ስላሉት ጉዳቶች አንድም ነገር እንዳትነሳ እና መረጃ እንዳይሰጥ እንዲሁም እውነታው ታፍኖ እንዲቀር በሚል በድብቅ እንዲያዝ ማድረጋቸውን ሊያስረዳ የሚችል አስተማማኝ እና በቂ የሆነ ማስረጃ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጋራ የምክክር ጉባኤው ቀጥተኛ የሆነ ግድፈት ለመፈጸሙ እና ለመጣሱ ባንኩ ክትትል እና ቁጥጥር በሚያደርግበት የአሰራር ስልቱ በባንኩ የብድር ፖሊሲ (OP/BP 10.00) ላይ በግልጽ የተመለከተ በመሆኑ ይህም በቂ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡
የዓለም ባንክ መአጥፕ 3/PBSIII እየተባለ የሚጠራውን ፕሮጀክት ተግባራዊ በሚያድርግበት ጊዜ የፕሮጀክቱን የብድር አስተዳደር የባንኩን ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች፣ የስነምግባር እና የባለሙያነት መስፈርቶችን እንዲሁም ድርጅታዊ ተሞክሮዎችን ሆን ብሎ በመተው እና እንዝህላል በመሆን ምንም ዓይነት ጥንቃቄ እና ትኩረት ያለመደረጉን ሊያስረዱ የሚችሉ በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡
የዓለም ባንክ እራሱን ህወሀት እያለ የሚጠራው የዘራፊ ወሮበላ ስብስብ ቡድን እጅግ በጣም ሙሰኛ የሆነ ስብስብ መሆኑን ወይም ደግሞ ከዓለም እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ የሙስና ማዕበል ውስጥ ተዘፍቆ ያለ አገዛዝ መሆኑን ከጥርጣሬ በላይ አሳምሮ እያወቀ ይህንን ግዙፍ ገንዘብ ለዘራፊ እና ለወሮበላ የበተነው መሆኑን የሚያውቅ ስለሆነ ይህንንም ሊያስረዱ የሚችሉ በቂ እና አሳማኝ ማስረጃዎች አሉ፡፡ የዓለም ባንክ “በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር” በሚል ርዕስ ባለ417 ገጽ ዘገባ አዘጋጅቶ ያቀረበባት ብቸኛዋ ሀገር ናት፡፡ (በዚያ እ.ኤ.አ በ2012 በተዘጋጀው ዘገባ የዓለም ባንክ በጤና፣ በትምህርት፣ በገጠር የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በፍትህ፣ በግንባታ/ኮንስትራክሽን፣ በመሬት እና በመገናኛ/ቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች መጠነ ሰፊ የሆነ ሙስና መፈጸሙን ይፋ አድርጓል፡፡ እንደዚሁም በእ.ኤ.አ በ2012 የዓለም ባንክ መአጥፕ 3/PBSIII እየተባለ የሚጠራ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በሚል 600 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነትን ለዘራፊው ለወያኔ አጽድቋል፡፡) እንግዲህ እራሱ ባንኩ በየክፍላተ ኢኮኖሚ ዘርፉ ባደረገው ጥናት መሰረት ወያኔ እስከ አፍንጫው ድረስ በሙስና ተዘፍቆ በመንቦጫረቅ ላይ መሆኑን ሌላው ቢቀር እራሱ ባቋቋመው የምርመራ ቡድን ዘገባ ውጤት መሰረት መቶ በመቶ እያወቀ ይህንን ያህል ግዙፍ ገንዘብ ለዘራፊ ሙሰኛ ወዲያውኑ ያውም በዚያው ዘገባው በተለቀቀበት ዓመት መስጠት ማለት እንዲበላው እና እንዲያበላ መፍቀድን በተጨባጭ ማመላከት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
የህጉ ዋና መሰረት የሚሆነው የዓለም ባንክ መአጥፕ 3/PBSIII እየተባለ የሚጠራውን የፕሮጀክት የብድር ገንዘብ ጨካኝ አምባገነን፣ እና ህጋዊ እውቅና ለሌለው እንዲሁም በረዥም ጊዜ ታሪኩ የግድያ ባለሙያ እንጅ የዕውቀት አቅመ ቢስነት የተጠናወተው ደንቆሮ ስብስብ፣ ነውጠኛ፣ ጽንፈኛ፣ አሸባሪ፣ ቀማኛ እና የሰብአዊ መብቶችን በመደፍጠጥ ታዋቂ ለሆነ የዘራፊ ቡድን የመስጠቱ ጉዳይ ነው፡፡ የዓለም ባንክ የብድር ገንዘቡ የአኟክን ህዝብ የጉዳት ሰለባ የሚያደርግ መሆኑን አሳምሮ እያወቀ ይህንን ዕኩይ ድርጊት ለመደበቅ እና እውነታውን ለማዛባት እንዲቻል በቀረበው ግምገማዊ ዘገባው አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳይል ለመደበቅ ሙከራ አድርጓል፡፡
የዓለም ባንክ ሆን ብሎ እያወቀ እና የወያኔ ወሮበላ ስብስብ ቡድንን ለማጠናከር በሚል ሽባ አስተሳሰብ የመአጥፕ 3/PBSIIIን ገንዘብ እንካችሁ ብሎ ገጸ በረከት አድርጎለታል፡፡ እራሱ ባደረገው መጠነ ሰፊ የሙስና ጥናት የዓለም ባንክ በሙስና ለተዘፈቁ ሙሰኛ አገዛዞች ባለስልጣኖቻቸው በመንግስት ላይ መንግስት በማቋቋም በማታለል እና በማጭበርበር በህዝብ ስም የመጣን ገንዘብ ለታላላቅ ባለስልጣኖች እና ግብረ አበሮቻቸው የግል መጠቀሚያ ሆኖ ሲቀራመቱ እና ሲያባክኑ የደረሰበት ከሆነ ባንኩ የተረፈውን የእርዳታ ብድር ገንዘብ የማዘግየት እና የማስተላለፍ ስልጣን እንዳለው አሳምሮ ያውቃል፡፡
“የዘረፋ ዕዳ” ግዴታን በማያስገቡ የወሮበላ ዕዳዎች እና በአፍሪካ የማጭበርበር ተግባራት የዩስ ፖሊሲ ላይ የእራሴ የግል ሀሳብ፣
አንባቢዎቼ አንደምያውቁት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ አዳዲስ ቃላት በየጊዜው አበርክቻለሁ። አሁን ደግሞ የተጣመረ ቃል “የዘረፋ ዕዳ”/thug-debts የሚል ይሆናል፡፡ የእኔ የዘረፋ ዕዳ ግንዛቤ ከድብቅ ዕዳ የተለየ ነው፡፡ የእራሴን የዘረፋ ዕዳ ህልዮት ወይም ጽንሰ ሀሳብ በሌላ ጊዜ አብራራለሁ፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ ግንቦት 2011 “የአረብ ብረት መጨፍለቂአዎች ፣ የጠበቁ ቡጢዎች እና የተዘጉ ግድግዳዎች (ክፍል 4)/Steel Vises; Clenched Fists and Closing Walls; (Part IV)“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ እንደ ወያኔ የወሮበላ ስብስብ ያሉ ድርጅቶች ስልጣንን የሚቆጣጠሩት ወንጀለኛ የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን ለማስፋፋት እና የሀገሪቱን የገንዘብ ግምጃ ቤት ለመዝረፍ እንዲሁም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር የሚገኙ ሀብቶችን ለማባከን ነው የሚል የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡
የኦባማ አስተዳደር ካደረጋቸው በርካታ ከንቱ ጥረቶች መካከል አንዱ በዘረፋ የተወሰደን ሀብት የማስመለስ ተነሳሽነት (ዘሀማተ)/Kleptocracy Asset Recovery Initiative (KARI) በዩኤስ የፍትህ መምሪያ ስር በማቋቋም ዘራፊዎች እና የእነርሱ የወንጀል ተባባሪዎች ከዜጎቻቸው የዘረፉትን እና የሰረቁትን ገንዘብ በማስመለስ ገንዘቡ ቀደም ሲል ታቅዶለት ለነበረው ዓላማ እንዲውል ማድረግ ነው፡፡ የዩኤስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት ኤሪክ ሆልደር እ.ኤ.አ ሀምሌ 2010 ወደ ካምፓላ በመሄድ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገኝተው ይህ ፕሮግራም (ዘሀማተ) የተጀመረ መሆኑን አሳውቀው ነበር፡፡ እንደዚሁም ለአፍሪካ መሪዎች እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፡
በዩኤስ አሜሪካ የፍትህ መምሪያ ስር በዘረፋ የተወሰደን ሀብት የማስመለስ ተነሳሽነት (ዘሀማተ)/Kleptocracy Asset Recovery Initiative (KARI) አዲስ ድርጅት ተቋቁሞ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ይፋ የሆነ ሙስና ለማስመለስ እና የተመለሰውም ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እና ተገቢነት ላለው የህዝቦቻችን ጥቅም እንዲውል በማድረግ ትግሉን ለማካሄድ ስራውን የጀመረ መሆኑን ሳበስራችሁ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ለዚህ ተግባር ብቻ ሊሰሩ የሚችሉ የህግ ባለሙያዎችን መርጠን በአንድ ቡድን እንዲሰባሰቡ በማድረግ ሙስናን ለመግታት እስከ አሁን ድረስ የተደረጉት ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ አጥፊዎችም በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርዓት በማመቻቸት የህዝብ ሀብት እንዲጠበቅ ይደረጋል፡፡
ያ ክስተት እጅግ በጣም አስደናቂ እና ለማመን የሚያስቸግር ሁኔታ የተፈጠረበት ጊዜ ነበር፡፡ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሆልደር መገኘታቸው በአሜሪካ የማፊያ (ወንጀለኞች) ቤተሰቦች ከኒዮርክ ከተማ፣ ከችጋጎ፣ ዴትሮይት፣ ሚያሚ፣ አትላንቲክ ከተማ፣ ላስ ቤጋስ፣ ሴንት ሌውስ፣ ሎስ አንጀለስ እና ከፊላዴልፊያ ግዛቶች እና ከተሞች በተሰባሰቡ የማፊያ ወንጀለኞች ጉባኤ ላይ ቀርቦ ጦርነት አንደማወጅ ያህል ነበር። ኤሪክ ሆልደር በካምፓላ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በመገኘት ስለሀብት ዘረፋ ለአፍሪካ ተመሳሳይ ዘራፊዎች ማስታወቂያ እየተናገሩ በነበሩበት ጊዜ የእነዚህ የማፍያ ክርስትና አባት ምስሎችን እነ ቦናኖ፣ ኮሉምቦ፣ ጋምቢኖ፣ ጀኖቬስ እና ሉቸስ የተባሉት የአሜሪካ የማፊያ ኮምሲዮን ጋር አንደመደራደር ነበር። ይህ ዕለት እና ክስተት ታላቅ የሆነ ስሜታዊነት የተንጸባረቀበት ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንደሌሎች የኦባማ አስተዳደር የአፍሪካ የተነሳሽነት ጥረቶች ሁሉ ዘሀማተም እንደዚሁ በባዶ ዲስኩር ከመታጀብ ባለፈ ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡
በአሜሪካ በተደራጀ መልኩ የወንጀል ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩም የወያኔ የወሮበላ ስብስብ ቡድንም አጭበርባሪ፣ አታላይ ማፍያዊ እና በሙስና የተዘፈቀ ድርጅት መሆኑን በትንታኔዬ ላይ ለማቅረብ ሞክሬ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2013 ዶ/ር ሄለን ኤፕስተን በኒው ዮርክ የግምገማ መጽሐፍት ውስጥ እንደሚከተለው አቅርበው ነበር፡
እንደ ዓለም ባንክ ዘገባ ከሆነ በግምት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እራሱን ኢህዴግ እያለ ከሚጠራው የወሮበላ ስብስብ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት ባላቸው ማህበረ ረዴኤት ትግራይ (ማረት)/Endowment Fund for the Rehabilitation of Tigray (EFFORT) እየተባለ በሚጠራው የንግድ ተቋም የተያዘ ነው፡፡ የማረት የደረቅ ጭንት ማመላለሻ ትራንስፖርት፣ ኮንስትራክሽን፣ ፋርማሴውቲካል እና የስሚንቶ ማምረቻ ድርጅቶች በጣም ትርፋማ የሆኑ የውጭ እርዳታ የኮንትራት ስምምነቶችን እንዲሁም ከመንግስት ባንኮች ብድር በቀላሉ ለማግኘት እንዲችል ለማረት ተስማሚ የሆኑ የብድር ስምምነቶችን ይዋዋላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የተለመደው የአፍሪካ የዘረፋ ተምሳሌት ሀገር አይደለችም፣ እናም መለስ እራሱ ከእነዚህ የንግድ ድርጅቶች ተጠቃሚ ለመሆኑ ሊያስረዳ የሚችል ማስረጃ የለም፡፡ የተለየና እና ከሚታወቀው የማጭበርበር ዘዴ ባፈነገጠ መልኩ የተወሳሰቡ እና ማንም በቀላሉ ሊደርስባቸው በማይችል መልኩ በማጨበርበር የተካኑ በመሆናቸው ጉዳቸውን አዝረክርኮ ለማውጣት እጅግ በጣም የተለየ ምርመራን ይጠይቃል፡፡ ይልቁንም እነዚህ የንግድ ድርጅቶች በጣም ጥብቅ በሆነ የቁጥጥር ስርዓት የተያዙ እና የዕርዳታ ሰጭ ድርጅት ባለስልጣኖችም መለስ የምዕራቡን ዓለም የነጻ ገበያ ስርዓት እንደሚከተል እና እንደሚደግፍ በማስመሰል እያታለለ እና እያጭበረበረ ዕኩይ ምግባሩን ሲያካሂድ የቆየ መሆኑን አሁን በቅርቡ ነው የተገነዘቡት፡፡
ወሮበላው የወያኔ ስብስብ ቡድን በማረት ጥላ ስር የተካተቱትን ኩባንያዎች ከፊል ስም ዝርዝሮች ከተቃዋሚው ጎራ አንዱ የሆነው የግንቦት 7 ለፍትህ፣ ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ በድረ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡ ማንም ቢሆን የወያኔን የወሮበላ ስብስብ ቡድን በሙስና የበከተ እና የዘቀጠ መሆኑን እና የማጭበርበር እና የማታለል ክህሎት ያለው መሆኑን አንድ በሙያው ጥልቀት ያለው የጥናት ባለሙያ ወይም ደግሞ የተቃዋሚ ድርጅቶች ጥናቶች እና ትንታኔዎች ላይ መወሰን አይጠበቅባቸውም፡፡ አንድ የቀድሞ የህወሀት አመራር እና የማረት ባለስልጣን እንደሰጡት መግለጫ ከሆነ በዊኪሊክስ የተለቀቀው ሰነድ ማረት በጣም ውስብስብ የሆነ ባህሪ ያለው ወንጀለኛ የንግድ ድርጅት መሆኑን አሳይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የወሮበላ ዕዳዎችን መክፈል አይጠበቅበትም ምክንያቱም ክፍያው በየትኛውም መለኪያ ቢሆን ፍትሀዊ አይደለምና፡፡ የዓለም ባንክ ከእውነታው እና ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር ቆሞ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን ጉዳይ ንጹህ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
የማይቀረው የድብቅ ዕዳ የምጸዓት ቀን በአፍሪካ፡ አስቸኳይ ጥሪ ለአፍሪካ የህግ ባለሙያዎች በያላችሁበት!
እንደ የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት የአፍሪካ ጉደዮች ልዩ አማካሪ/United Nations Office of the Special Advisor on Africa (OSSA) እና የአፍሪካ በይነ መንግስታት የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ተነሳሽነት ዘገባ “እ.ኤ.አ በ2009 ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ለነበረው የአፍሪካ ዕዳ የአፍሪካ ሀገሮች ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን ወደ ውጭ ልከው ካገኙት ገቢ ውስጥ 16 በመቶ የሚሆነውን የአህጉሪቱን የውጭ ምንዛሬ ለውጭ ዕዳ ክፍያ አውለውታል፡፡“
ከ30 ዓመታት በፊት ፕሮፌሰር ሄንሪ ኤፍ ጃክሰን እንዲህ የሚል ሀሳብ አቅርበው ነበር፣ “ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የአፍሪካ ሀገሮች የውጭ ዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመምጣት በአህጉሪቱ ውስጥ ታላቅ ቀውስ እያንዣበበ እንደሆነ የአፍሪካ ትልቁ ችግር በድርቅ ምክንያት የሚመጣው ምስቅልቅ እና ቀውስ ሳይሆን ይልቁንም ትልቁ አደጋ በዕዳ መቆለል ምክንያት የሚከሰተው ቀውስ ነው“ በማለት ግልጽ አድርገዋል፡፡
ይህ ነው አንግዲህ ወደፊት አየተራመዱ ወደህዋላ መንሸራተት!
ለሁሉም የአፍሪካ የህግ ባለሙያዎች በያላችሁበት እንድትነሱ እና በአፍሪካ ላይ እየመጣ ያለውን የድብቅ ዕዳ የምጸዓት ቀን እንድትከላከሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ!!!
(ይቀጥላል…)
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የካቲት 3 ቀን 2007 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment