Monday, September 21, 2015

በአማራ ክልል በግንባታ ስራ የተሰማሩ ተቋራጮች በጤና ጥበቃ ቢሮው አሰራር መማረራቸውን ተናገሩ፡


መስከረም ፲ (አስር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ዓርብ መስከረም 7/2008 ዓ.ም በድንገት በጠራው የተቋራጮች ስብሰባ፣ በክልሉ የሚገነቡ የጤና ተቋማትን በመስራት ላይ ያሉ ተቋራጮች በሙሉ ሰብስቦ ፤የግንባታ ስራዎች በመጓተታቸው ምክንያት ከልዩ ልዩ ግብረ ሰናይ መንግስታት የተገኘ የዕርዳታ ገንዘብ በየጊዜው ተመላሽ መሆኑ ቢሮውን አሳስቦታ ብሏል። ተቋራጮች በተቻላቸው ፍጥነት ግንባታቸውን በማጠናቀቅ በዕርዳታ የተገኘውን ገንዘብ ከመመለስ እንዲያድኑት ጠይቋል፡፡
የክልሉ የጤና ጥበቃ ቢሮ የዘርፉ ሃላፊዎች ግንባታው እንዲፋጠን ቢጠይቁም፣ ከተቋራጮች የተገኘው ምላሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡በርካታ ተቋራጮች በለቅሶና በምሬት በጤና ቢሮው የደረሰባቸውን በደል በመግለጽ ለመጓተቱ ተጠያቂው ቢሮው መሆኑን ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡
የጤና ጥበቃ ቢሮው በአብዛኛው ‹‹ በጀት የለም!! ›› በማለት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ያመላለሳቸው ተቋራጮች በምሬት ሲናገሩ ፤ ጤና ጥበቃ ቢሮው የሰሩበትን ገንዘብ በወቅቱ ባለመክፈሉ በተያዘው ጊዜ ስራውን ጨርሰው ለማስረከብ አልቻሉም፡፡በዚህም ምክንያት በየፕሮጀክቱ ለሚሰሩ ሰራተኞችና ሙያተኞች ከተገቢው በላይ ክፍያ ለመፈጸም መገደዳቸውን ገልጸው፤ የሚከፍሉት በማጣት ንብረታቸውን እሰከ መሸጥ መድረሳቸውን በለቅሶ ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
በጤና ጥበቃ ቢሮው በየክፍሉ በኃላፊነት የተቀመጡት ግለሰቦች ስለሚመሩት ዘርፍ ምንም ዓይነት እውቀት የሌላቸው በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በቦታው የተቀመጡ መሆኑ ስራው በታሰበው መንገድ እንዳይጓዝ አንዱ እንቅፋት ሆኗል የሚሉት ተቋራጮች ፤ከአብዛኛው ስራ አፈጻጸም ጀርባ የሚገኙ የቢሮው ባለሙያዎችም የተቋራጩን እጅ በማየት የሚሰሩ፣ ከሙስና ያልጸዱ ያለ ጥቅማ ጥቅም መስራት ወንጀል አድርገው የሚመለከቱ መሆናቸውን በግልጽ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
ተቋራጮች ከስብሰባው በኋላ በሰጡት አስተያየት የጤና ጥበቃ ቢሮው የአሰራር ዲሲፕሊን የማይከተል ከመሆኑም በላይ ጨረታዎችን አጫርቶ አሸናፊዎች ከታወቁ በኋላ ‹‹ በጀት የለንም !! ›› በማለት ስራውን ማጓተት እየተለመደ የመጣ የዘወትር አሰራሩ መሆኑን ገልጸው፣ በገንዘብ የሚደራደሩ ተቋራጮችን በጎን በመጥራት ስራዎችን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ለሲፒኦ ማስያዘዣነት አቅርቡ የሚለውን ከሃምሳ ሽህ ብር በላይ የሚቆጠር ገንዘብ ለበርካታ ወራቶች ከያዘ በኋላ ጨረታውን ሰርዣለሁ በማለት ገንዘቡን የመመለስ አሰራር በተደጋጋሚ በመፈጸም ገንዘቡ ስራ እንዳይሰራ ማድረጉ እና በቅርቡ በተመሳሳይ መንገድ ፣ የአርባ ጤና ጣቢያዎችን ግልጽ ጨረታ በጋዜጣ አውጥቶ አሸናፊዎች ከተለዩ በኋላ በጀት የለንም በሚል ሰበብ ጨረታውን መሰረዙ የቢሮውን የአሰራር ህገወጥነት ያመላክታል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የአገሪቱ የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አሊ ሱሌይማን በሪፖርተር ጋዜጣ ” አገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና እየተንሰራፋ እየመጣ ነው፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ አነስተኛ ሙስና ወንጀል ላይ ያተኩራል፡፡ ከፍተኛ ሙስና የሚፈጸመው በከፍተኛ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች በመሆኑ ፍርኃት አለባችሁ? ለዚያ ነው ደፍራችሁ የማትገቡት?” በማለት ለጠየቃቸው ጥያቄ ” የምንፈራበትም፣ የማንፈራበትም ጉዳይ አለ፡፡ ትልቁ ነገር ግን ፍርኃቱ የግል ጉዳይ አይደለም፡፡ ልማት እንዳይደናቀፍ በመሥጋት ነው፡፡ ልማቱን ላለማደናቀፍ በማለት ትንሹን ነገር አስበን ትልቁ ነገር እንዳይሰናከል ከማድረግ አኳያ የምናደርገው ሊኖር ይችላል” በማለት ልማት እንዳይደናቀፍ ሲባል ከፍተኛ ባለስልጣናት ሙስና ውስጥ ሲገቡ እንደማይጠየቁና ህጉ በእነሱ ላይ የተለየ ተፈጻሚነት እንዳለው ገልጸዋል።
Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment