Wednesday, September 16, 2015

ይህን መንግሥት እንዳትነኩት ይወድቃል!


ኢህአዴግ በየሁለት ዓመቱ የጠቅላላ ጉባኤውን ያካሂዳል። በዚህ ጉባኤ የድርጅቱን ዋናና ም/ሊቃነመናብርት ይመርጣል። ድርጅቱ የሚጓዝበትን
ሁሉን አቀፍ የፖሊስ ሰንድም ያዘጋጃል። ያለፈውንም ዓመት መርምሮ ያጸድቃል። እነዚህ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ድርጅቱ እክል በገጠመው ወይም በድርጅቱ
አባላት መካከል መቃቃር የተፈጠረ በመሰለው ጊዜ ግን፣ ጉባኤን ራስን እንደ መፈወሻ ስፍራ (ፎርም) በመፍጠር፣ ግምገማና ሹም ሽሮችን በማድረግ ተሐድሶ ያደርጋል። አሁን አሁን ያን መሳይ ነገር ብዙ አይታይም። ምክንያቱም ጉባኤው ያን መሳይ አቅም እንዲኖረው ድርጅታዊ ሥራ የሚሠራና የሚመራ ጠናካራ አመራርና መሪ ይፈልጋል። ኢህዴግ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ያን መሳይ መሪ ማጣቱ መነገር ከጀመረ ሰንብቷል። ግምገማዎች የሚደርጉ ቢሆን ግምገማዎቹ ለውጦች የሚካሄዱባቸው ወይም ሥር ነቀል ሹም ሽሮች የሚታዩባቸው አይደሉም። ምክንያቱም የሚሻር የሚሽር ሰው የለም። እንኳን ድርጅቱ እንዲህ የአመራር ንቅዘትና ድክመት ሞልቶት ቀርቶ፣ ደህና እየሠራን ነው ተብሎ በሚፎከርበት ዘመን እንኳ፣ አቶ መለስ ዜናዊ፣ የውሸታቸውን በስብሰናል ገምተናል እያሉ፣ የሚያስቸግሯቸውን ሰዎች የሚያባርሩበት፣ የፈለጓቸውን እሚሾሙ እሚሽሩበት ሁኔታ ነበር። በዘንድሮ የኢህአዴግም ሆነ የአባልድ ድርጅቶቹ ጉባኤ ላይ ግን ይህ አልታየም። ብዙዎቹ ባሉበት ሲጸኑ ብዙ ችግር አለበት በተባለበት ህወሓት ዘንድ ብቻ መጠነኛ ለውጥ ታይቷል። ያ ም ቢሆን የአራቱም ድርጅቶች ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበሮቻቸው በድጋሚ ተመርጠዋል።

ያም ሆኖ የድርጅቶቹ ሁሉ አስኳልና የሥልጣን ማዕከል በሆነው፣ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕውሓት) ውስጥ ግን፣ አንጻራዊም ቢሆን ግብ ግቦችና መጠነኛ ለውጦች ታይተዋል። በዚህ ስብሰባ ልክ አቶ መለስ እንደሚያደርጉት ቢያንስ እንደ ልቡ መናገር የቻለና ሁሉም ላይ ቁጣና ተግሳጹን ማስፈን የቻለ አንድ ሰው ታይቷል። በህወሓቱ ጉባኤ የሥራ አስፈጻሚነቱን ሥፍራ የተረከበውና የአገሪቱ ቁልፍ ቦታ የሆነውን የደህንነት መ/ቤት የተቆጣጠረው ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አሰፋ አዳራሹን በሙሉ እንደ ልባቸው ሲወርዱበትና አመራሮችን በሰላ ወቀሳና ክስ ከፍ ዝቅ ሲያደርጓቸው መዋላቸው ተሰምቷል። የአመራር ጉድለትና ሙስፍና መንሰራፋቱን፣ በአመራር አባላቱ ዘንድ ዝሙትና መጠጥ ያለ ቅጥ መበራክታቸውን፣ የማስተዳደር አቅምና ችሎታ መጥፋቱን ሁሉ በማንሳት የሰላ ትችት አቅርበዋል። አቶ ጌታቸው አመራሩ የትግራይን ህዝብ የበደለ መሆኑን ሁሉ በማንሳት፣ ይቅርታ መጠየቅ የሚያስፈልግበትን አግባብ ሁሉ መመሪያ ቢጤ መስጠታቸውና አስተያየታቸውን በቁጣ መግለጣቸው ተሰምቷል። ከአቶ መለስ ሞት በኋላ እንደዚያ ባለ ኃይለ ቃል ህወሓቶችን የተቆጣ የህወሓት ሰው መኖሩን እንጃ!

ያም ሆኖ ግን የአዲስ አበባውና የትግራዩ ቡድን እየተባለ ለሁለት መከፈሉ የሚነገርለት ህወሓት፣ አንዳች ለውጥ ሳያታይበት የውድቅትና የድክመት ምንጭ ናቸው የተባሉትን አቶ አባይ ወልዱን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ እንደገና መርጧቸዋል። በአቶ ስብሐት ነጋ በአቶ አርከበና ደጋፊዎቻቸው አማካይነት በትግራይ ባለው አመራር ላይ ሲዘንብ የሰነበተው ፕሮፖጋንዳ፣ ምንም ለውጥ ሳይስገኝ፣ አቶ ጌታቸውን ብቻ በሥራ አስፈጻሚነት አስመርጦ፣ የተቀረውን በሙሉ ለባለድሎቹ መቀሌዎች አስረክቦ ተመልሷል። ያ ማለት ግን ጉዳዩ አልቆለታል ማለት አይደለም። ምክንያቱም በፓርቲው አባላት መካከል የተፈጠረው መናናቅና መረን የተለቀቀው ሙስና ይበልጥ መንሰራፋቱ አስግቷል። ያ ሁሉ ኃጢአት ተወርቶ፣ ከፓርቲው አመመራ አባላት ይመለከተዋልና እምርጃ ይወሰድበት መባሉ ቀርቶ፣ በትህትና እስኪ ይቺን ሂስህን በዚች ውሃ ዋጣት የተባለ ባለሥልጣን አንድም የለም። በአጉል የመተካካት ጨዋታ እንኳ የተሰናበቱትም ቢሆን በክብር ተሸኙ ተባል እንጂ በድክመት ተባረሩ አልተባለም። በአቅም ማነሰ የተገመገሙ ሰዎች ያቺኑ አቅማቸውን እንደያዙ ቀጥለዋል።

የተባለውማ ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ከአባይ ወልዱ ይልቅ እሳቸውን ፈልጓል በሚል ወከባ፣ ወደ ፓርቲው አመራር ተመልሰው እንዲመጡ ታሰበው የነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ ነበሩ። ግን ምን ያደርጋል እንኳን ሊመረጡ በእጩነት እንኳ ሊቀርቡ የሚችሉበት አግባባ ባለመፈቀዱ የመቀሌው አንጃ ባዶአቸውን እንዲመለሱ አድርጓቸዋል። ለመቀሌዎቹ ይብላኝላቸው እንጂ አርከበ እንደሆነ ፕላን ቢ አላቸው። እንዲያውም ትክክለኛውና ጥቅም የሚያስገኘው ሥልጣን፣ በፓርቲ ሳይሆን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እየሆነ በመምጣቱ፣ ፓርቲውን ጥርስ አልባ በማድረግ የመንግሥት ተቋማትን ለመቆጣጠር ሀሳብ መኖሩ ተሰምቷል። ለምሳሌ አቶ አርከበ ከአማካሪነት ይልቅ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በሚኒስቴር ደረጃ የሚቋቋም የራሳቸው መዋቅር ሠርተው፣ በሚኒስትር ማዕረግ፣ የኢንደስትሪ ፓርኮች ኃላፊ ለመሆን መዘጋጀታቸው ተነግሯል። ይህ ከፍተኛ ገንዘብና ጥሪት ሊያንቀሳቅስ የሚችል ተቋም ለብቻው ወጥቶ የሚደራጅበት ምክንያት ምንድነው? ከሆነስ ለምን በኢንደስትሪ ሚኒስትር ስር አይጠቃለልም ይህስ ከጥቅማ ጥቅም ሙስና ወደ መዋቅር ወደ መዘርጋት ሙስና መሸጋገሩ አይደለም ወይ? የመሳሰሉ ጥያቄዎች ተነስተው ግብግብ መኖሩም እየተሰማ ነው። በፓርቲው መስመር የሹመት ቦታ ያጡት አቶ አርከበ የራሳቸውን መዋቅር አስጠንተውና ሚኒስቴር መ/ቤት ዘርግተው ለዚህ ድፍረት መብቃታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን አቶ ኃ/ማርያምን ንቀው ነው ብሎ የሚከሷቸውም አሉ። ኃይለማርያም ተንቀዋል ብሎ ክስ እንኳ እንዲያው ስራ መፍታት ነው።

ለማንኛውም አቶ አርከበ፣ ሲሆን ሲሆን ህዝቡ ጠይቋቸዋል በሚል ሰበብ፣ መቀሌ ወርደው፣ ከወ/ሮ አዜብ ላይ የኤፈርት ድርጅቶችን አስለቅቀው፣ ድርጅታዊ ሥራ እየተሰጣቸው፣ ድምጾቻቸውን የሚሸጡ ካድሬዎችን በቁጥጥር ሥር በማድረግ፣ አላግባብ ተባረናል የሚሉትን እነ ስዩም መስፍንና ስብሐት ነጋን ወደ ፓርቲው መዋቀር መመለስ ት የሚቻልበትን የምርጫ መስመር መክፈት፣ ሲመከርበት የሰነበተ ዘዴ ነበር። ያ ሳይሆን ቀርቶ ከባለቤታቸው የተማሩትን ዘዴ የተጠቀሙት ወ/ሮ አዜብ ሁሉም እስኪደነግጡ ድረስ ከደብረጽዮን በቀር፣ ከሁሉም የላቀ ድምጽ አግኘተው፣ በሥራ አስፈጻሚነት እንደገና ሊመረጡ ችለዋል። እነ አርከበ፣ አባይ ፀሐዬ፣ ስብሐትና ስዩም መስፍን እንኳን ሊመረጡ የምርጫ ጨዋታ ውስጥ እንኳ መግባት አልቻሉም። ለነገሩማ ወደጉባኤ አዳራሾችም እንዲገቡ የተፈቀደላቸው የኢራኑ ኑዩክሌር ድርድር ያህል ጊዜ ፈጅቶ ነው ይባላል።

ሌላው የሥልጣን ማማ ናቸው የሚባሉት የሠራዊቱ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ሳሞራ የኑስ፣ እነ ወ/ሮ አዜብን የሚደግፉ ሲሆኑ፣ በዘንድሮ የጉባኤ ስብሰብዎችም ላይ፣ ሲቭል ለብሰው ሲንጎራደዱ ከርመዋል።

በህገመንግሥቱና በይስሙላው ልማድ መሠረት፣ የሠራዊቱ አባላት ተጠሪነታቸው ለሕገመንግሥቱ ብቻ ነው ስለሚባል፣ፖለቲካ ወገንተኝነት በሚያሳየው የፓርቲ ስብሰባ ላይ መገኘት አይኖርባቸውም። ድሮም አቶ የነበሩት ጄኔራል ሳሞራ ግን አቶ ሆነው ሰንብተዋል። ለዚህም ምክንያት ሳይኖራቸው አይቀርም።

በአገሪቱ ዛሬ የላቀውንና ተቀራራቢ የሆነውን ሥልጣን ያላቸው ጄኔራል ሳሞራና የደህንነት ሹሙ አቶ ጌታቸው አሰፋ መሆናቸው ይታመናል። አቶ ጌታቸው ወደ ፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ በመግባት ራሳቸውን በማስመረጣቸው አንዲት እርከን ወደላይ ከፍ ማለታቸው ለሳሞራ ሳይገባቸው አልቀረም። አቶ ጌታቸውም የሥራ አስፈጻሚነቱን ቦታ የሞሉት የሳሞራ ሰዎች በስብሰባቸው ላይ ምን እንደሚያወሩ፣ ምን እንደሚወስኑ ለማወቅ ቀረብ ብለው መመልከቱን ካስፈለገም በወሳኝነት መሳተፉን ሳይፈልጉ አልቀረም። ይህ ከሆነ ደግሞ ምንም ነገር ሊደረግ በሚችልባት አገር፣ ወታደሩ ሳሞራ ድንገት ብድግ ብለው፣ ከዛሬ ጀምሮ በፓርቲዎቹ የሥራ አስፈጻሚ እ ስብሰባዎችም ላይ መገኘት አለብኝ እንዳይሉ መስጋቱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም። ጌታቸውንም ሆነ ሳሞራን ከሥልጣን ላይ ሊያነሳቸው የሚችል አንዳች ኃይል ቢኖር ሊሆን የሚችለው ፓርቲው ብቻ ስለሚሆን ፓርቲውን ጥርስ እንዲኖረው ወይም ወላቃ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጉ ከማንም በላይ በሁለቱ ባለሥልጣናት ላይ የወደቀ ኃላፊነት መሆኑን ሁለቱም ሳይረዱት አልቀሩም።

በሌላ በኩልም ቀደም ባለው መዋቅር፣ የደህንነት ሚኒስትሩ በፓርቲው አንጻር ተጠሪነታቸው ለሥራ አስፈጻሚው ለዶ/ር ለደህንነቱ አማካሪ ለአለቃ ጸጋዬ የነበረ ሲሆን፣ ከአሁን በኋላ ግን፣ ደብረጽዮንም ሆኑ ጌታቸው እኩል ሥራ አስፈጻሚዎች ስለሚሆኑ አለቃ ፀጋይም ስለተሸኙ፣ ጌታቸው ለማንም ሳይጠሩ ሥልጣናቸውን ሊሠሩ ይችላሉ። መቸም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኃ/ማርያም ሪፖርት ያደርጋሉ ተብሎ መጃጃል አይኖርም።

በቀር ማለት ነው። ጨዋታውን አጓጊ የሚያደርገው ግን ካሁን በኋላ ጀኔራል ሳሞራ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰቡ ላይ ሲሆን፣ ስብሐትን የተመረኮዙት አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ሳሞራን ጥለው ጀነራል ሰዓረን ለማምጣት እየዶለቱ መሆኑ ከተሰማ ሰንብቷል።

ለማንኛውም ካሁን በኋላ ከትግራይ የመጣ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር አይሆንም እየተባለ መነገሩ፣ ቦታውን ለሌሎች ብሄረሰቦች ከመልቀቅ ቸርነት ሳይሆን፣ ያ ጠቅላይ ሚኒስትር እውነተኛ ባለሥልጣን ሊሆን ስለሚችል የመጀመሪያ ተጎጂዎች የሚሆኑት ደህንነቱና ኤታማዦር ሹሙ ናቸው። በዚያች አገር ቀርቶ በየትኛውም አገር ላይ፣ አንድ መሪ ሥልጣን ጨበጠ የሚባለው ቢያንስ እነዚህን ሁለት ነገሮች መሾምና መሻር ሲችል ብቻ ነው። ለማንኛውም ካሁን በኋላ ከትግራይ የመጣ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር አይሆንም እየተባለ መነገሩ፣ ቦታውን ለሌሎች ብሄረሰቦች ከመልቀቅ ቸርነት ሳይሆን፣ ያ ጠቅላይ ሚኒስትር እውነተኛ ባለሥልጣን ሊሆን ስለሚችል የመጀመሪያ ተጎጂዎች የሚሆኑት ደህንነቱና ኤታማዦር ሹሙ ናቸው። በዚያች አገር ቀርቶ በየትኛውም አገር ላይ፣ አንድ መሪ ሥልጣን ጨበጠ የሚባለው ቢያንስ እነዚህን ሁለት ነገሮች መሾምና መሻር ሲችል ብቻ ነው።

በዚህ የሥልጣን ሽኩቻና ፍትጊያ መካከል፣ እየተላተመ ያለው ሕወሓት/ኢህአዴግ፣ በዚያ ላይ እንደ አቶ በረከት ሰምዖን ያሉትን ሰዎቹን አጥቶ፣ ምን ያህል እድሜ ሊኖረው
እንደሚችል ማየቱ የሚያጓጓ ነገር ነው። የዘንድሮውን የህወሓት ጉባኤ ያዳነውም አንዱ ይሄ እባካችሁ ይሄን ድርጅት በጣም አትነካኩት ሊወድቅ የሚችል ተሰባሪ ነገር ነው የሚል መራራት መኖሩ ነው። ሌላኛው ደግሞ የኢህአዴግ ጉባኤ ከህወሃት ጉባኤ በኋላ የሚካሄድና ቀን ተቆርጦለት በዚያ ላይ እዚያው መቀሌ ላይ ሊደረግ እንግዶች ተጠርተው አገር እየጠበቀው ያለ ነገር በመሆኑ ነው። ያም ሆኖ እንኳ መግባባት እየጠፋ እረባካችሁ ቶሎቶሎ በሉ እየተባለ ገመናን አሳልፎ ላለመስጠት ውጥረት ቀብሮ በውጥረት ስር የተካሄደ ጉባኤ ነው። ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን የተባለ!

የሆኖ ሆኖ የመቀሌውም ይሁን የአዲስ አበባው ወገን አሸነፈም ተሸነፈም ሁለቱም ህወሓትን ከመጠጋገን የተረፈ ሌላ ጥቅም አይኖራቸውም። የጀመርኳትን ቤት እስክጨርስ ወይም አዲስ አበባ ደርሼ እስክመጣ ኢህአዴግን አትነካኩብኝ ይወድቅብኛል የሚሏት ጨዋታም ሌላዋ ጥቅም ናት። የባለ ሥልጣኑን እድሜን ያረዘመች ጥቅም!

Source:: Zehabesha

No comments:

Post a Comment