Thursday, August 13, 2015

የዲያስፖራ በዓል በታላቅ ፌሽታ ተጀመረ

ነኅሴ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰበት የዲስፖራ ክብረበዓል ትላንት በአዲስአበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በታላቅ ፌሽታ ተጀምሯል፡፡ ዝግጅቱ በተለያዩ ክንውኖች ለተከታታይ አምስት ቀናት ይቆያል ተብሎአል፡፡ ዲያስፖራ በልማት ለማሳተፍ በሚል ሽፋን የዲስፖራውን ህብረተሰብ ለመያዝ እንዲመች ታስቦ በተዘጋጀው በዚህ በዓል ላይ በግምት 2ሺ ገደማ የዲያስፖራ አባላትና በሀገር ውስጥ ስራ የጀመሩ የዲያስፖራ ባለሃብቶች የተገኙ ሲሆን በመንግስት ወጪ ውስኪ እንደውሃ የተንቆረቆረበት ምሽት በሸራተን ሆቴል አስተናጋጅነት ተከናውኖአል፡፡ በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለንዋያቸውን ያፈሰሱ ዲያስፖራዎች እንዲገኙና ምርትና አገልግሎታቸውን በኤግዚቢሽን መልክ እንዲያሳዩ በታዘዙት መሰረት መገኘታቸው ታውቆአል፡፡ አንድ በአገልግሎት ሰጪ ዘርፍ የተሰማራ ዲያስፖራ በሰጠው አስተያየት በኤግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፈው አንዳች ነገር ይመጣብኝ ይሆን በሚል ሰግቶ መሆኑን ገልጾ ፣ ቢሮክራሲው እጅግ የሚያስመርርና እና የገባንበትም እያለቀስን ባለንበት ሁኔታ ወንድምና እህቶቻችንን ከውጭ ሀገር የሞቀ ኑሮአችሁን ትታችሁ ግቡና ስሩ ለማለት ሞራሉ የለንም ብሎአል፡፡ እናም መንግስት በቅድሚያ የራሱን ከባድና ውስብስብ ውስጣዊ ችግር ሳይፈታ ኑልኝ እያለ ከበሮ መደለቁ ሀብትን ከማባከን ያለፈ ዋጋ የለውም ሲል አስተያየቱን ሰጥቶአል፡፡ ተጋብዘው ሰሞኑን ከውጭ ለገቡት የዲያስፖራ አባላት መንግስት የትራንስፖርት ወጪያቸውን የሸፈነ ሲሆን በየአገሩ በአስተባባሪነት የሰሩ አባላት የተሟላ ወጪያቸው እንደተሸፈላቸው ታውቆአል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ከወጭ ንግድ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ገደማ በዓመት ገቢ የምታገኝ ሲሆን ፣ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጽያዊ ወደሀገር ቤት የሚልከው ገንዘብ (ሪሚታንስ) ከዚሁ ገንዘብ ጋር የሚስተካከል፣ አንዳንዴም የሚልቅ በመሆኑ መንግስት ሳይወድ በግድ ፊቱን ወደዲያስፖራው እንዲያዞር መገደዱን ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በበዓሉ ላይ የተገኘው ዲስፖራ አባላት ቁጥር ወደ 2 ሚሊየን ተኩል ከሚገመተው አጠቃላይ ዲያስፖራ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ፣ ሁሉንም ዲስፖራ በሀገሩ ጉዳይ ለማሳተፍ መንግስት የብሔራዊ እርቅ መንገድን በመከተል የዴሞክራሲና የሰብኣዊ መብት እንዲሁም የህግ የበላይነት ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ ይኖርበታል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን በዘገባው ላይ አስፍሯል።
Source : http://ethsat.com/amharic/%e1%8b%a8%e1%8b%b2%e1%8b%ab%e1%88%b5%e1%8d%96%e1%88%ab-%e1%89%a0%e1%8b%93%e1%88%8d-%e1%89%a0%e1%89%b3%e1%88%8b%e1%89%85-%e1%8d%8c%e1%88%bd%e1%89%b3-%e1%89%b0%e1%8c%80%e1%88%98%e1%88%a8/

No comments:

Post a Comment