Monday, August 10, 2015

ነኅሴ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በትግራይ እና በአማራ ክልል ገዢዎች መካከል ያለው አለመግባባት በተለያዩ አጋጣሚዎች ከፍ ዝቅ ሲል ቆይቶ ፣ ሰሞኑን ኢህአዴግ በአካሄደው ግምገማ ላይ እንደገና አገርሽቶበታል።

የትግራይ ክልል ገዢ አቶ አባይ ወልዱ የተወሰኑ የህወሃት ደጋፊዎችን በመያዝ በሁለቱ ክልሎች መካከል ስላለው አወዛጋቢ መሬት ፣ ከአማራ ክልል ገዢ ጋር በድንበር አካበባ ያደረጉት ውይይት፣ በዘለፋና በጸብ ከተቋጨ ከወራት በሁዋላ፣ በሰሞኑ የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የመሳሪያ ምዘገባን ተከትሎ እንደገና አገርሽቷል። በአቶ አባይ ወልዱ የሚመራው የህወሃት ቡድን፣ የአማራውን ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን " ክልሉን መሳሪያ አስታጥቀህ ራስክንም ጄኔራል አድርገህ ሾመሃል" የሚል ሂስ ሰንዝረውባቸዋል። አቶ ገዱ በበኩላቸው " አዎ ለክልሌ ጄኔራል ነኝ" የሚል ምላሽ ሰጥዋል። ህወሃቶች ይህን ትችት እንዲሰነዝሩ ያደረጋቸው " በአማራ ክልል ለድብቅ የጦር መሳሪያዎች ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቷል የሚል መከራከሪያ ይዘው ነው። የህወሃቱ የጽ/ቤት ሃላፊ ፣ "ከደህንነት መስሪያ ቤት ባገኘነው መረጃ የክልሉ ተወላጆች በድብቅ የያዙት 3 ሚሊዮን 500 ሺ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ፣ ከተደበቀበት ወጥቶ ህጋዊ እንዲሆንላቸው ተደርጓል። ገዱ ይህን እርምጃ የወሰደው የክልሉን ምክር ቤት ብቻ አማክሮ ነው። " ያሉ ሲሆን፣ ይህ እርምጃ የተወሰደው በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ያለው አለመግባባት በቀጠለበት ሰአት መሆኑ፣ አማራ የራሱን ጄኔራል መርጦ ጦር እያደራጀ ነው ያስብላል" በማለት አክለዋል። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሰጡት መልስ " አዎ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን መዝግበን ህጋዊ አድርገንላቸዋል። ከዚህ የሚልቅ ያልተመዘገበ መሳሪያ እንዳለ እናውቃለን። አርማጭሆ ላይ በመራሁት ስብሰባ 'በየቤታችን የጦር መሳሪያዎች አሉን። ድንበሩን የሚጠብቀው ያንተ ወታደር አይደለም፣ እኛ ነን፣ መሳሪያችንን ህጋዊ አድርግልን?' ብለው በጠየቁኝ መሰረት፣ መሳሪያውን ለመቆጣጠር ያመቸን ዘንድ ህጋዊ አድርገናል። ይህንን ከፌደራል መንግስት ይሁንታ ጠብቀን አይደለም የሰራነው፣ ይሄ የክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ስልጣን ነው።" ብለዋል። አቶ ገዱ አክለውም " ትግራይ ስንት ክላሽ ነው ለአማራ አዋሳኝ ወረዳዎች ያከፋፈለው? እኛ ቁጥሩን ለመናገር በህወሃት ላይ ሰላይ አላሰማራንም። ነገር ግን ይታወቃል።" ካሉ በሁዋላ " ጄኔራል ለመሆን የተባለውም ቢሆን፣ አዎ በክልሌ ጄኔራል እኔ ነኝ ። ሲሉ አክለዋል። የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ውዝግብ ባለመቋጨቱ ለቀጣዩ ዙር ውይይት በአጀንዳ ተይዟል። በህወሃትና በብአዴን መካከል ያለው ውዝግብ የቆየ መሆኑን የሚናገሩት ማስረጃዎች፣ ህወሃቶች ብአዴኖችን "ፈሪ" እያሉ ሲከሷቸው፣ ብአዴኖች ደግሞ ጠባብ እና ያልተማሩ እያሉ ይንቋቸዋል። የንቀቱ ደረጃ በላበት ሁኔታ፣ በሁለቱ ድንበሮች አካባቢ የሚገኘው አወዛጋቢ መሬት ለተለያዩ ግጭቶች መንስኤ ሲሆን ቆይቷል። የአማራ ክልል ባለስልጣናት የትግራይ ክልል እስካሁን ከወሰደው መሬት በላይ ተጨማሪ የጎንደር አካባቢ መሬት ሊወስድ ያስባል በማለት ቅሬታ የሚያሰሙት ፣ የድንበር አካባቢ ህዝብ የሚያሰማው ተቃውሞ ስጋት ላይ ስለጣላቸው መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ። የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት በአካል ተገናኝተው በመነጋገር መፍትሄ ለመፈለግ ሙከራ ቢያደርጉም፣ ተዘላልፈው ከመለያየት በስተቀር የረባ ነገር መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በብአዴን ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች የተወሰኑ የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት የያዙትን አቋም እየተቃወሙ እንደሚገኙ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
Source :http://ethsat.com/amharic/%e1%8b%a8%e1%88%81%e1%88%88%e1%89%b1-%e1%8a%ad%e1%88%8d%e1%88%8e%e1%89%bd-%e1%8c%88%e1%8b%a2%e1%8b%8e%e1%89%bd-%e1%8a%a5%e1%88%ad%e1%88%b5%e1%89%a0%e1%88%ad%e1%88%b3%e1%89%b8%e1%8b%8d-%e1%8a%a5/

No comments:

Post a Comment