Tuesday, August 11, 2015

በኦሮምያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በኖኖ አሎ ቀበሌ የሚገኙ ባለስልጣናት እና የጸጥታ ሃላፊዎች

ነኅሴ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን በኖኖ አሎ ቀበሌ የሚገኙ ባለስልጣናት እና የጸጥታ ሃላፊዎች ' እናንተ የዚህ አካባቢ ተወላጆች ሳትሆኑ ሀብት እያፈራችሁ የአካባቢው ተወላጆች ግን ከናንተ ያነሰ ገቢ ነው ያላቸው...ይህን ገቢ ያገኛችሁት በኛ መሬት ነው፤ ስለዚህ የክልሉ ተወላጆች ባለመሆናችሁ ክልሉን ለቃችሁ ውጡ' በማለት ቤታቸውን በማቃጠልና ንብረታቸውን በመንጠቅ ያፈናቀሉዋቸው የአማራ ተወላጆች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ሲል የቀድመው ኢሰመጉ የአሁኑ ሰመጉ በፎቶ ግራፍ አስደግፎ ያወጣው 136ኛ ልዩ መግለጫ አስረድቷል። የሰብአዊ መብት ጉባኤው እንደሚለው መጋቢት 27፣ 2007 ኣም አቶ ዘመዱ እንዳለ የተባለ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ መገደሉን ተከትሎ፣ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ ውሳኔ ሳያገኝ " ይህ ግድያ የተፈጸመው በአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ነው" በማለት የኖኖ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኢንስፔክተር ሃይሉ ድሪባ፣ የኖኖ አሉ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ጎሳየ ገች እና መቶ አለቃ ገነነ በየነ የተባሉ የፖሊስ አባላት የቀበሌ አመራሮችንና የፖሊስ አባላትን በማስተባበር ፣ የአካባቢው ህዝብ በአካባቢው በሚኖሩ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ እንዲነሳ በማነሳሳት ሚያዚያ 9፣ 2007 ዓም 85 አርሶ አደር አባወራዎችን ለእስራት ዳርገዋቸዋል። በማግስቱ ሚያዚያ 10 ደግሞ ከጧቱ 3 ሰአት አካባቢ ዘር በመምረጥ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች መኖሪያ ቤትና ንብረት ነው ያሉትን እየመረጡ በእሳት እንዲቃጠል ፣ ከታሰሩትም አባዎራዎች ከእያንዳንዳቸው 300 ብር ለነዳጅ ብለው ከተቀበሉዋቸው በሁዋላ "ቤታችሁ ተቃጥሏል" ሂዱ በማለት ከእስር መልቀቃቸውን ሰመጉ የቀረበለትን ማመልከቻ በመንተራስ ባለሙያዎቹ ቦታው ድረስ በመሄድ አርሶ አደሮችን አነጋግረው ማረጋገጣቸውን ገልጿል። የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ ቤቶቹ ከነሙሉ ንብረታቸው በተቃጠሉበት ቦታ ላይ 24 ቆርቆሮ ቤቶች ስራ መጀመሩን ፣ ቤት ለተቃጠለባቸውና ንበረት ለወደመባቸው የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት በራሳቸው ተነሳስተው ገንዝብና እህል አዋጥተው እርዳታ እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑንና ተጎጂዎቹ ተረጋግተው እንዲኖሩ ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ለሰመጉ ቢገልጹም፣ ሰመጉ ግን የአካባቢው ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት የእርዳታ ገንዘብና እህል ማዋጣቱ ትክክል ቢሆንም፣ እርዳታው ግን ሪፖርቱ እስከተጠናከረበት ለተጎጂዎች አለመድረሱን ገልጿል። ሰመጉ ባለስልጣኖች ባነሳሱት ብጥብጥ 1 የሰው ህይወት ማለፉን፣ 10 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ አደጋ መድረሱን፣ 99 የሳር ክዳን ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውን፣ 25 የቆርቆሮ ክዳን ቤቶች በእሳት ተቃጥለው መውደማቸውን አትቷል። ቃጠለውን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ ደካሞች የሚገኙባቸው ተፈናቃዮች ከአካባቢው በመሰደድ ወደ ደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ሀበሽጌ ወረዳ ድንኳን ውስጥ ተጠልለው ሲረዱ መቆየታቸውን ሰመጉ ገልጾ፣ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ " ለምን ከሰሳችሁን " ያሉ ባለስልጣናት፣ ለከፋ ችግር እንደዳረጉዋቸው፣ ሪፖርቱ ከመውጣቱ ጥቂት ቀድም ብሎም በዲኮሻም ቀበሌ የአቶ ደምስ መኩሪያና የአቶ በፈቃዱ ሰጠኝ መኖሪያ ቤቶች በእሳት እንዲቃጠሉ መደረጉን እንዲሁም ከአቤቱታ አቅራቢዎች መካከል 8 ሰዎች "ሽፍቶች ናቸው ይታደኑ"የሚል ትእዛዝ ወጥቶባቸው በፍርሃት አካባቢያቸውን ለቀው ተሰደዋል። ሰመጉ በማጠቃለያው " በአካባቢው የቀበሌና የፖሊስ ባለስልጣናትና አባሎች መሪነት ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው ነዋሪዎች፣ እንደማንኛውም ዜጋ በሀገሪቱ አካባቢ ሁሉ ተዘዋውረው ኑሮ የመመስረትና ሀብት የማፍራት መብት እንዳላቸው በህገመንግስቱ ቢደነገግም፣ " የዚህ ክልል ተወላጆች አይደላችሁም ፣ ህገወጦች ናችሁ ተብለው መኖሪያ ቤታቸው በህገወጥ መንገድ በእሳት እንዲወድም መደረጉ ከአገሪቱ ህጎችና ከተቀበለቻቸው አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር በእጅጉ የሚቃረን ነው" ብሎአል። ይህ ችግር በዳርጌ ወረዳ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ በወረዳ፣ በቀበሌ ባለስልጣናትና በህግ አስፈጻሚና አስከባሪ አካላት የሚፈጸም መሆኑን ሰመጉ ገልጿል። ሰመጉ መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠሉባቸው እና በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ለሚገኙ ዜጎች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንዲያገኙ ፣ ለወደመባቸው ንብረትም ካሳ እንዲያገኙ መንግስትን የጠየቀ ሲሆን፣ በተለይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የጎሳና የዘር ልዩነትና አድልዎ እየተደረገባቸው እየተጎዱና እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው አሳሳቢ በሆነ መልኩ እየጨመረ በመሄዱ፣ መንግስት የተጠናና የማያዳግም የመፍትሄ እርምጃ ከህዝብ ጋር ተመካክሮ መውሰድ እንዳለበት አበክሮ ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment