Sunday, August 23, 2015

ማሪንጌ ቻቻ ፤ የወያኔ (የሃይልዬ) ጨዋታ – ሰሎሞን ታምሩ ዓየለ (ከካሊፎርኒያ)

August 22, 2015
የሃይልዬ የድርቅ ፖለቲካ !!!
ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም !!!
ሰሎሞን ታምሩ ዓየለ (ከካሊፎርኒያ)
ለጽሁፌ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ የኢትዮጵያው ጠ / ሚኒስቴር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ” የዳያስጶራ “ ሳምንት በሚል በአዲስ አበባና አካባቢዋ ስለተከበረውና ከተሳታፊዎቹ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ በአገራችን እየተንሰራፋ ስላለው ድርቅ ገጽታውን እንዲያብራሩ ተጠይቀው እንደነበር ይታወሳል። የሰጡትን ምላሽ በኢሳት ሬዲዮ ካዳመጥኩኝ በኋላ ሰውዬው ምን ነካቸው ? ምንስ ቢተማመኑ ነው የኢትዮጵያውን ድርቅ ከካሊፎርኒያና ከአገረ አውስትራሊያ ጋር ለማዛመድ ያነሳሳቸው የሚል ሃሳብ በጭንቅላቴ እየተመላለሰ ስላስቸገረኝ ፤ እስቲ እኔም የድርሻዬን የማውቀውንና የተረዳሁበትን መንገድ አንድ ልበል በሚል ምላሽ ለመስጠት ነው። ከሁሉ ደግሞ የደነቀኝ “ ዳያስጶራው “ ንግግራቸውን በጭብጨባ ማጀቡ፤ ኢትዮጵያ ሌላ ተፈጥሮን መቆጣጠር የሚችል መሪ አገኘች ወይ የሚል ጥያቄ በህሊናዬ ማጫሩ አልቀረምና የድርቁን ችግር በራሷ ጥረት ብቻ ልትቀረፍ የተዘጋጀች አገርም መሰለኝ። ለማንኛውም ትችቴ በዕውቀትና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆንልኝና ሰውዬው ” የሳቱትንና “ በእኔ አማርኛ ደግሞ “ የቀዘቀዙበትን “ ጉዳይ በተጨበጠ ማስረጃ አያይዤ ነካ ነካ ላድርገው። ሌሎቻችሁም ሃሳባችሁን እንድንሰማ ያብቃን እላለሁኝ። ጽሁፌንም ለአንባቢያን ምቹና ተስማሚ ወዲያውም ግንዛቤ ጨማሪ እንዲሆን በማሰብ በሁለት ክፍል ከፍዬዋለሁኝ።ትልቅ ትንተና ውስጥ ግን አልገባም። በቀላሉ ከዚህም ከዚያም ያገኘሁትን አስረጂዎችና ዘገባዎች በማዛመድ ለማቅረብ እሞክራለሁኝ ። የመጀመሪያውን ክፍል እነሆ !!!california drought
ትናንት ሃይሌ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሊስትሮ ሆነው ሊያገለግሉ የቆረጡለትን የፖለቲካ ፓርቲያቸውን ዛሬ ደግሞ መንፈሳቸውንና ኩራታቸውን ከፍ አድርገው ከፊታቸው የተደቀነውን የድርቅና አስከፊ ውጤቱን ለማሸነፈ የመንፈስ ዝግጅት ያደረጉበት እስኪ መስል ድረስ ድርቁን አጣጥለው ችግሩ የኛ ብቻ አይደለም በካሊፎርኒያም በአገረ አውስትራሊያም ተከስቷል አሉን። ትልቅ ማሰባቸው ባልከፋ ነበር። መልዕክታቸው ግን ዕውን የሚወዱትና የሚንገበገቡለት መንግስታቸውእንዲህ ጉልበትና አቅም ፈጥሮ እናንተ አታስቡ ለችግሩ እኔ አለሁ የሚል ከሆነ እሰየው ብለን እንለፈው። ታለባለዚያ ግን እንደው እንደ “ መልስ በኪሴ “ጫን ብሎ ለመጣው ጥያቄ በቂና አሳማኝ መልስ ጠፍቶ ለማምለጫና ለብልጣብልጥነት የተሰነዘረ ከሆነ ግን “ የሃይሌ ቶክ ሾው “ ነው ብዬ ልደምድመው።
ድርቅ የተፈጥሮ ክስተት በመሆኑ በማናቸውም የዓለማችን ምድር ላይ በሚገኘ አህጉሮችና አገሮች ላይ ይከሰታል ፤ ዋነኛ ምልክቶቹ በየትኛውም የአየር ንብረትና ሃብት ፤ ወቅቶችና ከባህር ወለል በላይ ከፍታዎች ላይ ሊታይ ይችላል። በቀጠሮም አይመጣም። ሲጀማምረውም በቅጡ ላናስተውለው እንችላለን። እያዘገመ ቀስ በቀስ ግን መጠኑን እያሰፋና እየጨመረ የሚሄድም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአንድ ምሽት መጣሁኝ አይልም ወይም ደግሞ የሞቀ ዘይት ውስጥ ሲገባ ወዲያውኑ እንደሚፈነዳው በቆሎና ፈንዲሻ ማሽላም አይደለም ። የተወሰነ የወሰንና ድንበር ክልል የለውም። አንድ ወጥ የሆነ ትርጉምም ወይም ፍቺም ያለው አይመስለኝም። የሚያስከትለውም አስከፊ፤ ጎምዛዛ ፤ ጥፋትና ጉዳት ወዲያውኑም ሊገለጽ አይችልም ይሆናል። የማይናቀው ግን በሰውና በእንስሳት ህይወት፤ በሌሎች ብዝሃ ህይወት፤ በተፈጥሮ ሃብታችን፤ በንብረታችንና በምጣኔ ሃብታችን ላይ ግን አሌ የማይባል ጉዳት፤ ጥፋትና ብክነት እስከወዲያኛው እንዳናንሰራራ አድርጎ የማለፍና የማስከተል ብቃት ግን አለው። ዛሬ በዓለማችን የድርቁን ሁኔታ የሚያባብሱና የሚያፋጥኑ ተግባሮች እንደ አሸን ፈልተዋል። በየትኛውም የዓለማችን ክፍል በሚገኙ ህዝቦች በየዕለት የመግባቢያ ቋንቋቸው ውስጥ ስለ ድርቅ አይወራም ማለት ዘበት እየሆነ መጥቷል። በትንሹ ቤተሰብ ውስጥ እንኳን ኑሮው ቢደላም ባይደላም ፤ ድርቅ ሳይወራ የሚታደርበት ቋንቋ ያለም አይመስልም።
በተባበሩት የአሜሪካ መንግስታት ስለሆነችውና ሃይሌ በቅድሚያ ድርቁን አጣጥለው አዲስ ክስተት እንዳልሆነ በድርቅ ስለተመታችው ካሊፎርኒያ ግዛት ትንሽ ከማለቴ በፊት ግን ጠቅላይ ሚኒስቴራችን እንዲህ ብለው ቢሆን ኖሮ ምንኛ ሃሳባቸውን በደገፍኩላቸው። ከሚወዱትና ሁሌ ሳያነቡ ወደ መኝታቸው የማያመሩት ሃይሌ ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ድርቅ የተነገረበትን ወንጌልም ሆነ መጽሃፍ ስም ፤ ምዕራፍና ቁጥር ጠቅሰው ድርቅ ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር ቁርኝት እንዳለው ወይም ደግሞ ይሄ ታልሆነላቸው በአህጉራችን አፍሪካ በተለይም የሣህል አገሮች ተብለው በሚጠቀሱቱ ሴኔጋል ፤ ሞሪታኒያ፤ ማሊ፤ ቡርኪና ፋሶ ፤ ኒጀር፤ ናይጄሪያና ሱዳን ሌሎችንም እንዲሁም የኛኑ አገር ጭምር ውስጥ የሚኖሩ በመቶዎቹ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች በየጊዜው በድርቅ ምክንያት እንደሚሰቃዩ ፤ በረሃብና በችጋር አለንጋ እየተገረፉ እንደሚኖሩ፤ ያ ታልሆነ ደግሞ ጎረቤቶቻችንን ሶማሊያን፤ ኬኒያን፤ ሁለቱንም ሱዳኖችን፤ ታንዛኒያንና ዑጋንዳን ጠቅሰው ቢሆን ኖሮ ማለፊያ ነበር ብልስ ስህተት የሰራሁኝ አይመስለኝም ።
ካሊፎርኒያ እኔንና አንድ ወንድ ልጄን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ፤ ኢትዮ አሜሪካዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ልክ እንደተወላጁና ነዋሪው ህዝብ የሚኖሩበት ግዛት ነው። በተለይም በሎስ አንጀለስና አካባቢው ፤ በሳንሆዜና አካባቢው ፤ በሳንፍራንሲስኮና በኦክላንድ እንዲሁም በሳንዲያጎ ከተሞች በድምሩ ቁጥሩ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ የኢትዮጵያውያን ደም ያላቸው ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። ነገር ግን የካሊፎርኒያ ህዝብ ብዛቱ ወደ 40 ሚሊዮን ይጠጋል። በተለያዩ የቅጽል ስም የምትጠራው ካሊፎርኒያ በዋናነት “ ወርቃማዋ ስቴት “ በመባል ትታወቃለች።
የካሊፎርኒያ ኢኮኖሚ ትልቅ ከሚባሉትና ከአሜሪካም አገር ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ የሚገኝ ነው። በጠቅላላው ኢኮኖሚዋ በቅርቡ በተባበሩት አሜሪካ የኢኮኖሚ ትንተና ቢሮ አማካይነት የተለቀቀው ዘገባ እንደሚጠቁመው ከሆነ ጠቅላላ የግዛቱ ምርትና አገልግሎት ዋጋው 2.342 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል። እንደውም ቀደም ሲል ካሊፎርኒያ እንደ አገር ብትቆጠር ከዓለማችን በምጣኔ ሃብት ብዛቷ የ፲ ኛ (አስረኛ) ደረጃ ይኖራታል ተብሎ የሚነገረውን በማሻሻል ዛሬ ከብራዚል ቀጥላ በ፰ ኛ (በስምንተኛ) ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ታዲያ ሃይሌ እንደው ዕድሜያቸው በፈጣሪ ዕገዛ በዝቶ ከነአመራራቸው እንኳን የ፻ ዓመት ዕድሜ ቢቸራቸው በምን ተአምር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከዚህ ያደርሱት ይሆን?
ካሊፎርኒያ ለግብርና ስራ አመቺና ተስማሚ ነች። አፈሯ ለም ነው ፤ ብዝሃነት ያላቸውን ተክሎች ፤ አዝርዐቶች፤ ፍራፍሬዎች፤ አትክልቶችና ሌሎች ጠቀሜታ ያላቸውን ዕጽዋቶች ለማብቀል የሚያስችል ተስማሚና ረዠም ቆይታ ያለው ወቅት አላት። የዘመኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎች መጠቀሚያና ማፍሪያም ግዛት ነች። ሸለቆዎቿን በዘመኑ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ጭምር የውሃ ሃብቷን እያጠጣች ምርቶቿን ታመርታለች። የወተትና ተዋጽዎቿም በዓይነትም በጥራትም የታወቁና የተመረጡ ናቸው ። በግብርና ምርትና ውጤቶቿ በዓለምም ሆነ በአሜሪካ ደረጃ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛ የምትገኘው ካሊፎርኒያ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚዋ ግምቱ ወደ 46 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደረጃ ደርሷል። የካሊፎርኒያ ግብርና ምርትና ወጤቶችም በተቀረው ዓለምም ላይ ተጽዕኖ ማሳረፋቸው አልቀረም። ወደ ውጭ የሚላኩት የግብርና ምርቶችም እንደ 2013 መረጃ መሰረት ከ21 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል ።የግብርና ኢኮ ኖሚው ለብቻው ድርሻው በመቶኛ ትንሽ ቢመስልም ቅሉ፤ መሬት ላይ ያለው ዕውነታው ግን የተለየ ነው። ግብርና በግዛቷ ኢኮኖሚ ትልቅና ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰራተኛ ህዝቧ የኑሮው መሰረቱና ምንጩ ይኸው የግብርናውና ተያያዥነትና ተደጋጋፊነት ያላቸው የስራ ዘርፎች ነው።
ካሊፎርኒያ ታዋቂ ፍራፍሬዎቿን ፤ አትክልቶቿን፤ የምግብ ሰብል ምርቶቿን ለማምረት ከፍተኛ የሆነ የውሃ ሃብቷን እንደምትጠቀም ጥናቶች ያመለክታሉ። 80 % የሆነውን የውሃ ሃብቷን ለግብርናው ልማት ታውላለች። በመስኖ የሚጠጣው መሬት መጠን ልክም ወደ 10, 000,000 ኤከር ( 5,000,000 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ) ይደርሳል ። መንግስትም በተለያዩ ተቋሞቹ አማካይነት ይህንን ውሃ ሃብት በማሰራጨትና በማደል ተግባር ላይ ተሰማርቷል ። የውሃ ሃብቷ ምንጭም ወቅቱን ጠብቆ የሚጥለው ዝናብና በሲየራ ተራራማ ሰንሰለቶችና በሰሜን አቅጣጫ ገዝፎ የሚታየው የሻሽታ ተራራዎች ላይ የሚጥለው ጥቅጥቅ የበረዶ ክምርና የደቡቡ ክፍል ደግሞ ከኮሎራዶ ወንዝ ነው። ይህ የውሃ ሃብት ምንጭ ነውታላላቅ ወንዞ ቿን ፤ ጅረቶቿን፤ ምንጮቿን፤ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎቿን ረግረግማ ስፍራዎቿን በውሃ የሚያረሰው ።ዝናብ አብዛኛውን ጊዜ በግዛቱ የሚጥለው በክረምቱና በጸደይ ወቅቶች ( ከጥቅምት እስከ ግንቦት ) ነው። ሞቃታማው የበጋው ወቅት ግን በአብዛኛው የግዛቱ ስፍራዎች ላይ ዝናብ አልባና ደረቅ ነው። ይህ ደረቅ ወቅት ከተራዘመና በቂ የበረዶ ክምር በተራሮቿ ጫፍ ላይ ከሌለ ካሊፎርኒያን ድርቅ ይመታታል።
በርግጥ ካሊፎርኒያን ድርቅ መቷታል ?
አዎን ! ካሊፎርኒያን ካለፉት አራት ዓመት ጀምሮ ድርቅ እየመታት ይገኛል። አንዳንዶቹ እንደሚናገሩት በግዛቷ ታሪክ አስከፊ ነው ይሉታል። የግዛቱ ዋና ዋና ከተማ ነዋሪዎች ፤ በትናንሽ ከተሞች የሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰብ አባላቶችና ነዋሪዎች ፤ የተለያዩ በቀጥታ ከውሃ ሃብት ጋር የሚሰሩ የመንግስት ተቋሞች፤ የሁለቱም ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰዎችና ምክር ቤቶች፤ መገናኛ ብዙሃኖች፤ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎችና ወዳጆች ፤ በዋናነት ሰብል አብቃይ ገበሬዎችና በእንስሳት ርባታ ላይ የተሰማሩ ቢዝነስ ሰዎች፤ የዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች፤ የውሃ ላይ ስፖርት አፍቃሪዎችና በሳርማ አረንጓዴው ላይ ጎልፍ ስፖርት አዘውታሪዎች ወዘተረፈ ሁሉም በውሃና በውሃ ሃብታቸው መብት፤ አጠቃቀምና አይያዝ እንዲሁም በመንግስት ሚና ላይ ይከራከራሉ ፤ ይጨቃጨቃሉ ፤ ይወያያሉ ፤ ህግ ያጸድቃሉ። ትልቅ መነጋገሪያ አጀንዳ ነው። የድርቁ ፖለቲካ ድብቅ የለውም ፤ መሸዋወድ ቦታ የለውም ፤ እኔን ብቻ ስማኝ የሚል መልዕክትም ስፍራ የለውም ። ልኩ ሲበቃ ወደ ህግ ተቀይሮ መተግበር ብቻ ነው። ወለም ዘለም የለም። ህግና ስነ ስርዓት የተከበረበትና ተጠያቂነት ያለበት ነው። በጠመንጃ ነካሾች አይደለም ካሊፎርኒያ የምትገዛውና የምትተዳደረው።
የኛው ጠቅላይ ሚኒስቴር የእርሳቸውን አገር ድርቅ ደረጃውን ሳይረዱና ግንዛቤ ሳይጨብጡ በካሊፎርኒያና በአውስትራሊያም ተከስቷል ብለው ለማጣጣልና ትኩረት እንዳይሻው ለማድረግ ሞ ክረዋል። በዕለተ ሃሙስ በኦገስት 18 2015 ላይ በሳክራሜንቶ ቢ ጋዚጣ ላይ ግን የሚከተለው ዘገባ በታዋቂ የዩኒቨርስቲ ካሊፎርኒያ ተመራማሪዎች ድርቁ በግዛቱ ያስከተውን ውጤት እንዲህ ገልጸውታል። በ2015 የካሊፎርኒያው ድርቅ የግዛቱን መንግስት በጠቅላላው ወደ 2.74 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንዳስወጣውና የግብርናው ሴክተርም ለብቻው 1.84 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚገመት ወጭ ላይ እንደጣለው ተገምቷል። በተጨማሪም ግምቱ 542,000 ኤከር ( 220,000 ሄክታር ) መሬት ስፋት ገበሬዎች በውሃ ዕጥረት ሳቢያ መሬታቸውን ጦም እንያሳደሩ እንደተገደዱና ወደ 10, 000 ( አስር ሺ) የሚጠጋ ጊዜያዊ ሰራተኛ ስራ አልባ እንደሆነባቸው ገልጸዋል። ርግጥ ነው የምግብ ምርቶችም የሸቀጥ ዋጋቸው ቀጥሏል ነገር ግን አብዛኛው ሰው ስራውን ይሰራል ኑሮውን እንደ ቀድሞው ይኖራል። ተርቦ ምግብ ፍለጋ ቀዬውን የለቀቀ ወይም የተሰደደ ሰው የለም። ካሊፎርኒያም የአሰቸኳይ የረሃብ ጊዜ አዋጅም አላወጀችም። የትኛውንም መንግስት የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋላት ልመና አልገባችም። እንደውም ይህ ሁሉ ሆኖ እንኳን ግብርናው ኢንዱስትሪ በተመራማሪዎች ያላሰለሰ ምርምርና የቴክኒክ ድጋፍ በተለይም በብቅለት ወቅታቸው አነስተኛ ውሃን መጠቀም የሚችሉ ተክሎች ዝርያዎችንና ዓይነቴዎችንና የመስኖ አጠቃቀማቸውን ውሃ ቆጣቢ በማድረግ ክፍለ ኢኮኖሚው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በመጣር ላይ ናቸው።በአጠቃላይ መግለጫቸው ምሁራኖቹ ሲናገሩ የግዛቱ ግብርና ኢኮኖሚ ካላፉት ዓመቶች ሲነጻጸር የተሻለ፤ በማበብና በማደግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
እንግዲህ ይህ ነው ድርቅ መታት ተብላ የተነገረላት ካሊፎርኒያ ዕውነታው። ዕውን የጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም መንግስት ” የድርቅ ፖለቲካ “ ማብራሪያ ካሊፎርኒያን እንደ ምሳሌ ማቅረቡ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ወይስ እንደው ተባራሪ ዜና ሰምቶ ነው ለአገራችን ድርቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ ማወዳደሪያና ማነጻጸሪያ ያቀረበው ?
ለዛሬው ላብቃና በሚቀጥለው እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት !!!!!!

Source:http://ecadforum.com/Amharic/archives/15525/

No comments:

Post a Comment