ነኅሴ ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተመሠረተበትን 35ኛ ዓመት በታላቅ ፌሽታ ለማክበር ደፋ ቀና በማለት ላይ የሚገኘው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ
ንቅናቄ (ብአዴን) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን ንቅናቄው ሰሞኑን በሚያካሂደው ጉባዔ ላይ እንደማይመረጡ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ህወሃትም በተመሳሳይ ሁኔታ የሟቹን የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ያሰናብታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የብአዴን ምንጮች እንደሚሉት ኢህአዴግ ባስቀመጠው የመተካካት ስርዓት መሠረት አቶ በረከት ከፓርቲ ሃላፊነታቸው
ለመልቀቅ የሚገደዱበት የመጨረሻው ጊዜ አሁን ነው፡፡ አቶ በረከት ባለፉት ጊዜያት በመተካካት ስም ከስልጣናቸው
እንዳይነሱ ሽፋን ያገኙት በአቶ መለስ ዜናዊ ይሁንታ ሲሆን፣ በ2005 በተካሄደው ጉባዔ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ
የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም በስልጣናቸው ላይ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ አቶ በረከት ስልጣን ይዘው የቆዩበት መንገድ ኢህአዴግ በራሱ ያስቀመጠውን የመተካካት ዕቅድ የጣሰ ነው በሚል ከውስጥ ተቃውሞ ሲነሳባቸው ቆይቷል።
ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥሎ አለኝ የሚላቸው ቁልፍ ሰው አቶ በረከት መሆናቸውን የሚናገሩት ብአዴኖች፣ በአሁኑ ሰዓት ያሉት ከፍተኛ አመራሮች ለካድሬ ስልጠና የሚሆኑ ሰነዶችን እንኩዋን ማዘጋጀት ብቃት የሌላቸው ናቸው ይሉዋቸዋል።
ህወሃት ሰሞኑን በሚያካሂደው ድርጅታዊ ጉባዔ በተለይ ከባለቤታቸው ሞት በሃላ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ከፓርቲ ስራቸው ራሳቸውን እንዳገለሉ የሚነገርላቸውን ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከስራ አስፈጻሚነት በማሰናበት በአዲስ ሰው ይተካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አቶ መለስ ጤናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ወይም የሚደርስባቸውን ትችት ለመቋቋም በሚመስል መልኩ ከጀርባ ሆነው አገሪቱን ለመግዛት እንዳወጡት በሚነገርለት የመተካካት ዕቅድ መሰረት ከ2003 ዓ.ም አስከ 2007 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ነባር አመራሮችን ከፊት መስመር በማስለቀቅ ወጣት የተባሉትን የድርጅቱን ሃላፊዎች ወደ ፊት የማምጣት እቅድ ዘርግተዋል። በዚህ ዕቅድ መሰረት ሟቹ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ አንዳንዴ የሚወስነው ድርጅቴ ነው በሚል እያወላወሉም ቢሆን በዚህ ሰሞኑ የህወሃት ጉባዔ ስልጣናቸውን ለማስረከብ ቃል ገብተው ነበር፡፡
ይህ የመተካካት ዕቅድ የአቶ መለስን ራዕይ እናስፈጽማለን በሚሉት እንደአቶ በረከት ባሉ ነባር አመራሮች ላይ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሳይሆን በመቆየቱ ቀደም ሲል በመተካካት ስም የለቀቁትን ከፍተኛ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮችን ያስቆጣና ተታለልን የሚል ቁጭትን ሲፈጥር መቆየቱን ምንጮች ይገልጻሉ።
አቶ በረከት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ባጋጠማቸው የጤና ችግሮች ምክንያት ሃላፊነታቸውን መወጣት ተስኖአቸው ቆይቷል።
ህወሃት በ2003 እና በ2005 ዓም ባካሄደው ጉባዔ በመተካካት ስም አቶ ስዩም መስፍንን፣ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ፣ አርከበ ዕቅባይ አቶ አባይ ጸሐዬና አቶ ዘርዓይ አስገዶም ከፓርቲ ሃላፊነት ያሰናበተ ሲሆን ፣ ብአዴን አቶ ተፈራ ዋልዋ ፣ አዲሱ ለገሰ፣ ታደሰ ካሳ፣ ካሳ ተ/ብርሃንና ብርሃን ሃይሉን ከስራ አስፈጻሚነት አሰንብቷል፡፡ ኦህደዴድ በበኩሉ አቶ አባዱላ ገመዳን፣ ጁነዲን ሳዶ፣ ግርማ ብሩና ኩማ ደመቅሳን ማሰናበቱ የሚታወስ ነው፡፡
Source :http://ethsat.com/amharic/%e1%8a%a0%e1%89%b6-%e1%89%a0%e1%88%a8%e1%8a%a8%e1%89%b5-%e1%88%b5%e1%88%9d%e1%8a%a6%e1%8a%95-%e1%8a%a8%e1%8d%93%e1%88%ad%e1%89%b2-%e1%8a%83%e1%88%8b%e1%8d%8a%e1%8a%90%e1%89%b3%e1%89%b8%e1%8b%8d/
No comments:
Post a Comment