Wednesday, August 12, 2015

በሆሳዕና በተነሳው የተቃውሞ ሰልፍ ሰዎች ተጎዱ

ነኅሴ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተቃውሞው ሰልፍ መንስኤ ከገንዘብ ምንዛሬ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰአት ተኩል ላይ በተፈጠረው ተቃውሞ ቁጥራቸው በውል ያልተወቀ ሰዎች ተደብድበው ሆስፒታል ገብተዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች በነጋዴዎች በኩል የሚልኩትን ገንዘብ ለማስቀረት ከፌደራል የመጡ ፖሊሶች እርምጃ መውሰዳቸው፣ ለተቃውሞ ሰልፉ መነሻ ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ተወላጆች፣ ነዋሪዎቹ ነጋዴዎቹ ካልተፈቱ ተቃውሞአችንን አናቆምም በማለት ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ፖሊስ ጣቢያውን ከበው ቆይተዋል። ፖሊሶች ሁለት ነጋዴዎችን ይዘው ያሰሩ ሲሆን፣ በአንደኛው ነጋዴ የየባንክ አካውንት ውስጥ 6 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል። ገንዘቡ ልጆቻችን የላኩት በመሆኑ፣ ሊታገድ አይገባም በማለት የሚከራከሩት ወላጆች ፣ እገዳው ካልተነሳ ተቃውሞአቸውን እንደሚቀጥሉና የከፋ ደም መፋሰስ ሊከተል እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነው። የተቃውሞ ሰልፉ እንደተጀመረ ፖሊሶች በወሰዱት እርምጃ 2 ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድበው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎችም ተይዘው ታስረዋል። አንድ የፖሊስ መኪናም ጉዳት ደርሶባታል። በርካታ የሃድያ ተወላጆች ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ በተለያዩ ገንዘብ ነክና ገንዘብ ነክ ባልሆኑ ምክንያቶች ፣ ገንዘባቸውን በባንክ ለመላክ አይፈልጉም። አንድ አስተያየት ሰጪ በነጋዴዎች በኩል የሚሰጠው ምንዛሬ በባንክ ከሚሰጠው የተሻለ መሆኑ፣ ወላጆች የሚላክላቸው ገንዘብ በነጋዴዎች በኩል እንዲሆንላቸው ይመርጣሉ ብሎአል። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚሰቃየው መንግስት፣ ከባንክ ቤት ውጭ ገንዘብ ያስተላልፋሉ በሚላቸው ግለሰቦች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቢቆይም፣ አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም አልቻለም።
Source :http://ethsat.com/amharic/%e1%89%a0%e1%88%86%e1%88%b3%e1%8b%95%e1%8a%93-%e1%89%a0%e1%89%b0%e1%8a%90%e1%88%b3%e1%8b%8d-%e1%8b%a8%e1%89%b0%e1%89%83%e1%8b%8d%e1%88%9e-%e1%88%b0%e1%88%8d%e1%8d%8d-%e1%88%b0%e1%8b%8e%e1%89%bd/

No comments:

Post a Comment