1ኛ) ኬንያም ኢትዮጵያም ሽብርተኝነት ላይ ሚዛን ስተዋል
ከሁለት ዓመት በፊት ዘ-ኢኮኖሚስት መጽሔት ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚከተሏቸው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አስተዳደር ሞዴሎች መካከል ያለውን ልዩነት የሚገልጽ ጽሑፍ አስነብቦን ነበር። ጽሑፉ የሚጀምረው ሁለት የድንበር ከተሞችን በማነጻጸር ነበር፤ መተማን እና የኬንያ ሞያሌን። በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ጥብቅ በኾነ የፍተሻ ሂደት ውስጥ ማለፍ ግድ ይላል። ድንበር ጠባቂዎቹ የተጓዦች ፓስፖርቶችን በእጅ ጽሑፍ ከተጻፈ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር ከያዘ ዶክመንት ጋራ ያመሳክራሉ። ፓስፖርቶቹ የሐሰት እንዳልኾኑ በጥንቃቄ ይመረምራሉ፤ ግልምጥምጥ እያደረጉ እና ኮስተርተር እያሉ ጥያቄ ይጠይቃሉ። በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ለመግባት ግን ይህ ሁሉ ጣጣ የለም። የደንህንነት መኮንኖቹ ፓስፖርት ሲመለከቱ ፈታ፣ ዘና ብለው ነው። ጥበቃው ልል ከመኾኑ የተነሳ “የድንበር ፍተሻ ሳይኾን የእንኳን ደህና መጡ አቀባበል ይመስላል” ይላል ዘ-ኢኮኖሚስት። የኢትዮጵያ የአስተዳደር ሞዴል መተማን ይመስላል፤ መንግሥት ሁሉ አወቅ የኾነበት እና ከዳር እስከ ዳር ሥልጣኑንና ቁጥጥሩን ያረጋገጠበት። የኬንያ መንግሥት በተቃራኒው የቁጥጥር ድክመት ያለበት እና ክፍትነት የሚታይበት ነው።
BEN CURTIS, FILE — AP Photo
Read more here: http://www.adn.com/2013/10/10/3119796/africa-vs-icc-quotes-on-court.html#storylink=cpy
Read more here: http://www.adn.com/2013/10/10/3119796/africa-vs-icc-quotes-on-court.html#storylink=cpy
ባለፈው ሳምንት በጋሪሳ 147 ሰዎች ያለቁበትን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ ሞዴሎች ጉዳይ ክርክር ተጀምሯል። በኬንያ እንዲህ ዐይነት የሽብር ጥቃት ሲፈጸም የመጀመርያው አይደለም። በተቃራኒው በኢትዮጵያ ከ1999 ዓ.ም በኋላ መጠነ ሰፊ የሽብር ጥቃት አልተፈጸመም። አልሸባብ ሁለቱንም አገሮች (በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን) እንደ ከባድ ጠላት ይመለከታል። ነገር ግን የኬንያ ስኬቱን በኢትዮጵያ ሊደግመው አልቻለም። ይህን ያስተዋሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን የአስተዳደር ሞዴል አንቆለጳጵሰውታል። እንዲህ ያሉ ክስተቶችን ተገን አድርገው ቋጥኝ የሚያካክሉ መደምደሚያዎች ላይ የሚደርሱ ሙግቶችን እና ትንተናዎች (ad hoc reasoning) ፋይዳ አነስተኛ ነው። ሲስተሞችን እና ሞዴሎችን በርትዕ እንዳንማር ያደርጉናል። ትልቁን ሥዕል እንዳንመለከት ዐይኖቻችንን ይጋርዷቸዋል። ይልቁንስ የሞዴሎችን ብቃት ለማወቅ መለኪያዎችን አውጥቶ መገምገም የተሻለ መንገድ ነው።
የፖለቲካ ፈላስፋዋ ሴይላ ቤን ሃቢብ ውስብስብ የፖለቲካ ማኅበረሰቦች አራት እሴቶች እንዳሏቸው ያስቀምጣሉ፤ ሌጂትሜሲ፣ የኢኮኖሚ ዋስትና፣ ደኅንነት እና አመክኗዊ የጋራ ማንነት። እነዚህ ግቦች በብዙኀኑ የፖለቲካ ማኅበረሰቦች አባላት የሚደገፉ ናቸው፤ በትርጉማቸው እና በይዘታቸው ላይ በየማኅበረሰቡ ጠንካራ ሙግቶች እና ያለ መስማማቶች ቢኖሩም። እነዚህ ግቦች እርስ በእርሳቸው የተወሳሰበ መስተጋብር አላቸው። አንዱን በተትረፈረፈ ኹኔታ ማግኘት ሌላውን ሊያሳጣ ይችላል። ለምሳሌ፦ ሌጂትሜሲን ለማምጣት እጅግ ክፍትና ነጻ የኾነ ሥርዐት ፈጥረን ደህንነትን አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን። የኢኮኖሚ ዋስትናን ለመጨመር ደግሞ የሰዎች ነጻነት ላይ ከመጠን ያለፈ ገደብ እናስቀምጥ ይኾናል። የጋራ ማንነታችንን ለማጠናከር ውህዳንን (minorities) እንጨቁናለን። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሞዴሎች ብስለት እና ብቃት የሚለካው እነዚህን አራት እሴቶች አመዛዝኖ በማቅረብ ችሎታቸው ነው። በእነዚህ መለኪያዎች እንደ ኢትዮጵያ ያለ እጅግ ጣልቃ ገብና ሁሉን ዐወቅ መንግሥት በሳል ነው ለማለት ያስቸግረናል። ሕዝቡን መንግሥታዊ ካልኾነ ሽብር ለመጠበቅ ቢችልም፤ ይህን የሚያደርገው ሌጂትሜሲን እና የጋራ ማንነትን አደጋ ላይ በመጣል ነው። ለምሳሌ በ1999 ዓ.ም በኦጋዴን የተፈጠረውን ክስተት እናንሳ። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ታጋዮች በቻይና የነዳጅ ኩባንያ ላይ ጥቃት ፈጽመው 74 ሠራተኞችን ገደሉ፤ ብዙ ንብረት አወደሙ። የኢትዮጵያ መንግሥት በአጸፋው ለሦስት ዓመታት ሳያሰልስ የቀጠለ መሬት አንዳጅ፤ ጅምላ ጨራሽ ወታደራዊ እርምጃ ወሰደ። በርካታ የኦጋዴን ነዋሪዎች ተገደሉ፤ ተገረፉ፣ ተሰቃዩ፣ ቀያቸውን ለቀው ተሰደዱ። ይህ ጥቃት ኦብነግን ቢያሽመደምደውም የኦጋዴን ነዋሪዎችን መብቶች ክፉኛ የጣሰ እና ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን የበለጠ እንዲጠይቁ ያደረገ ነበር። አራቱን እሴቶች የሚያመዛዝን ሳይኾን ወደ አንዱ እሴት በእጅጉ ያዘነበለ ጥቃት ነበር። የተከፈለው ዋጋ የፖለቲካ ማኅበረሰባችንን አናግቷል። ኬንያ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ ጫፍ ላይ ያለ የራሷ የኾነ አመዛዝኖ የማቅረብ ችግር አለባት። ለብሔራዊ ደህንነት የምትሰጠው ዋጋና ክብር አነስተኛ ነው። በኬንያ ላይ ጣታቸውን የቀሰሩ ኢትዮጵያውያን ይህን በሚገባ አብራርተውታል። ችግሩ ሦስቱ ጣቶቻቸው ወደራሳቸው እንደሚጠቁሙ መዘንጋታቸው ነው።
2ኛ) ዶናልድ ሌቪን የኔታ ናቸው
ታላቁ አሜሪካዊ የፖለቲካ ፈላስፋ ጆን ሮውልስ ከወጥ ሥራዎቹ በተጨማሪ በአንድ ነገር ይታወቃል፤ በየኔታነት (mentorship)። ለተማሪዎቹ የቅርብ ጓደኛ ኾኖ ሥራቸውን መከታተል እና ማበረታታት እንደ ምሁራዊ ግዴታው ይመለከት ነበር። ይህ ጠባዩ በርካታ ድንቅ ፈላስፎችን እንዲፈጥር ከማስቻሉም በተጨማሪ ተክለ ሰብእናውን እና ምሁራዊ ብቃቱን የሚያበስሩ ደቀ መዛሙርት እንዲያፈራ አድርጎታል። የምሁራን ስኬት በሥራቸው ብቃት ብቻ ሳይኾን በሌሎች ምሁራን ዘንድ ባላቸው ማኅበራዊ ካፒታል (social capital) ይወሰናል። ባለፈው ሳምንት በሞት የተለዩን የኢትዮጵያ ጥናቶች ታላቅ ሊቅ አሜሪካዊው ሶሲዮሎጂስት ዶናልድ ሌቪን ይህን እውነታ በሚገባ የተረዱ ነበሩ።
3ኛ) ድምጻችን ይሰማ ብርቱ ነው
በአምባገነን ሥርዐቶች መንግሥታት ላይ ግፊት የሚያደርጉ ማኅበራዊ ንቅናቄዎች ዕድሜ እጅግ አጭር ነው። ከምሥረታቸው አንስቶ የማኅበራዊ ድርጊት ችግሮች (collective action problems) ይገጥሟቸዋል። መንግሥት ሰርጎ ገቦችን ያዘልቅባቸዋል፤ መሪዎቻቸው እና አባሎቻቸው ይታሠራሉ፤ ተለጣፊ ቡድኖች ይፈጠሩባቸዋል። በአጠቃላይ በእነዚህ ንቅናቄዎች ውስጥ የመሳተፍ ዋጋ (cost of participation) ይሰቀላል። ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ንቅናቄውን እንዲተዉ ያደርጋል፤ ዋጋ ሳይከፍሉ ስኬት መካፈል የሚፈልጉ ሰዎችን (free riders) ያበራክታል። ማኅበራዊ ንቅናቄዎች ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በበለጠ ለእንደዚህ ዐይነቶቹ የአምባገነን መንግሥት ጥቃቶች የሚጋለጡባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ማኅበራዊ ንቅናቄዎች የአይዲዮሎጂ ጥራት እና ጥልቀት ይጎድላቸዋል፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የበለጠ ሰፊ እና ልል ናቸው፤ አባላቶቻቸውን የሚያጣሩበት ወንፊት ዘርዘር ያለ ነው። ይኼን ሁሉ ግምት ውስጥ ስናስገባ ከአራት ዓመታት በላይ የቆየው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ድማጻችን ይሰማ ንቅናቄ ቀጣይነት ያስገርማል።
Source:zehabesha.com
No comments:
Post a Comment