Tuesday, August 25, 2015

የደቡብ ክልል አመራሮች እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ነው


ነኅሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በታደለ ቱፋ የተጻፈውን የጋሞን ህዝብ ማንነት የሚያንቋሽሸውን መጽሃፍ ፣ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚመሩት የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች የገንዘብ ደጋፍ በማድረግ አስጽፈውታል በሚል ምክንያት ፣ በአርባምንጭና በተለያዩ የጋሞ ወረዳዎች የተቃውሞ ሰለፎች መደረጋቸውን ተከትሎ፣ በከፍተኛ አመራሩ እና በታች አመራሩ መካከል ያለው አለመግባባት ይፋ ሆኗል።
ለኢሳት የደረሰው የድምጽ ማስረጃ ከመጽሃፉ ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ ኢሳት በአመራሩ መካካል ልዩነት መፈጠሩን በተመለከተ ያቀረበውን ዘገባ የሚያረጋገጥ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደሴ ዳልኬ፣ የጋሞ ጎፋ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የደኢህዴን ባለስልጣናት እጃቸው አለበት በሚል የሚያናፍሱት ወሬ ትክክል አይደለም በማለት፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ጥፋታቸውን እንዲቀበሉ ጫና አድርገዋል። የወረዳ አመራሮች በተለይም የጨንጫ እና የአርባምንጭ የወረዳ አመራሮች ሂሳቸውን ወይም ጥፋታቸውን ለመቀበል ዝግጁ ካልሆኑ፣ የጥገኞች አስተሳሰብ አራማጆች ተብለው እንደሚፈረጁ በፕሬዚዳንቱ ተነግራቸዋል።
የወረዳ አመራሮች ከመጽሃፉ ጋር በተያያዘ ” ህዝቡ ከአመራሩ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል” ቢሉም፣ የክልል መሪዎች ” ሊቀበሉት ፈቃደኞች አልሆኑም።
ፕሬዚዳንቱ መጽሃፉን ደኢህዴን እንደላስጻፈውና እንዲያውም ሁሉም የድርጅቱ መሪዎች ደራሲውን ማውገዛቸውን ገልጸዋል። ምንም እንኳ ደራሲው ታስሮ በዋስ የተፈታ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱ ግለሰቡ ተመልሶ እንዲታሰርና ፍርድ ቤት የዋስትና መብቱን ጠብቆ የሚፈታው ቢሆን እንኳ፣ እርሳቸው እንደማይፈቱት በመናገር፣ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ከህግ በላይ ወይም ከፍርድ ቤት በላይ መሆናቸውን አስመስከረዋል፡፡
ይህ አንድ መጽሃፍ እርስ በርስ እንድንጠራጠርና እንዳንተማመን ካደረገን፣ እስከዛሬ አብረን የተጓዝነው ጉዞ የውሸት ነበር ያሉት መሪው፣ መጽሀፉ የድርጅቱን መዋቅር እንዲፈትሹ እና የደኢህዴንን የድርጅት ጥንካሬና በአመራሩ መካካል ያለውን መተማመንና መደጋገፍ እንደገና እንዲመረምሩ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ዶ/ር ካሱ ኢላላ ከአመራር ቦታ ላይ ሲነሱ ዶ/ር ሽፈራው ደግሞ ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚነት ተነሱ
የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ደኢህዴን/ ጉባኤ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የድርጅቱ የስራ
አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን የመረጠ ሲሆን፣ በሕዝበ ሙስሊሙ ጠላት ናቸው የሚባሉትን ዶ/ር
ሽፈራው ተ/ማርያም ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚነት አሰናብቶ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አድርጓቸዋል። ዶ/ር ካሱ ኢላላን በመተካካት ስም ሸኝቶአል፡፡
ጉባዔው 65 አባላት በማዕከላዊ ኮምቴ አባልነት የመረጠ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ዘጠኝ ያህሉ ማለትም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ፣ ደሴ ዳልኬ ፣ ተስፋዬ በልጂጌ ፣ ሲራጅ ፈጌሳ ፣ ሬድዋን ሁሴን ፣ መኩሪያ ሀይሌ ፣ መለሰ አለሙ ፣ ተክለወልድ አጥናፉ እና ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚዎች ሆነዋል።

ኢትዮጵያዊያን አሁንም በመተማ በኩል መፍለሳቸውን አላቋረጡም


ነኅሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያዋ የድንበር ከተማዋ መተማ አሁንም ኢትዮጵያዊያን መሰደዳቸውን አላቋረጡም ሲል ዘጋርዲያን ዘገብዋል።
መንግስት ጥበቃውን አጠናክሮ በአካባቢው ብዙ ሰራዊት ቢያሰማራም በቀን ከ100 እስከ150 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞ ድንበር አቋርጠው ይሰደዳሉ።
መተማ ከተማ ወደ መቶ ሽህ የሚገመት ነዋሪዎች ያላት ስትሆን የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሌ ስደተኞች መተላለፊያ ናት።ከተማዋ መንግስት በወሰደው የጥበቃ ማጠናከር ሳቢያ ገቢዋ መቀዝቀዙንም ፣ 80% የሚሆነው የከተማዋ ገቢ የሚገኘውም ከሕገወጥ ስደተኞች መሆኑንም ዘጋርዲያን አትቷል።
ከዚህ ቀደም በቀን ከ250 በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ይሰደዱ ነበር። መንግስት ጥበቃውን ያጠናከርኩት ኢትዮጵያውያን ሊቢያ ውስጥ በአይሲስ ከተገደሉ በኋላ ነው ቢልም፣ የአካባቢው ሰዎች ግን ጥበቃው የተጠናከረው ወጣቱ የመንግስት ተቃዋሚዎችን ለመቀላለቀል በገፍ ወደ ኤርትራ እየፈለሰ መሆኑን ተከትሎ ነው ይላሉ።
ምንም እንኳ የድንበር ጥበቃው ተጠናክሮ ቢቀጥልም፣ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ በትጥቅ ትግል ስርአቱን ለማስወገድ የሚታገሉ ሃይሎችን እየተቀላቀሉ ነው።

ፍርድ ቤቱ በነፃ ያሰናበታቸውን እስረኞች ከእስር ቤት አልወጡም


ነኅሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በሽብርተኝነት ወንጀል ከተጠረጠሩ በኋላ፤ በእነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ፣ ከአንድ ዓመት በላይ ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ሲታይ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት በነጻ እንዲሰናበቱ ከተፈረደላቸው አምስት ግለሰቦች መካከል 2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው እና 7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሠለሞን እስከአሁን ድረስ ከቂሊንጦ እስር ቤት መፈታት ባለመቻላቸው የተነሳ፣ በዛሬው ዕለት ማረሚያ ቤቱ ላይ ክስ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
እስረኞቹ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የመፍቻ ትዕዛዙ ለማረሚያ ቤቱ ቢደርስም፣ ተከሳሾቹ እስከአሁን ድረስ ከእስር ሊለቀቁ አልቻሉም።
‹‹የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እና ተከሳሾቹ እንዲለቀቁ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው የ2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው ባለቤቱ ወ/ሮ ቤተልሄም አዛናው እና የ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሠለሞን ወላጅ እናት ወ/ሮ መሠረት ገ/ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት ትዕዛዙን ለሰጠው ችሎት ክሳቸውን ማቅረባቸው ታውቋል ሲል ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ በፌስቡክ ገፁ ዘግቧል።

አዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ በአማካሪዎች ብዛት ተጨናንቀዋል


ነኅሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የመስተዳድሩም ምንጮች እንደገለጹት የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በአማካሪዎቻቸው ብዛት ተጨናንቀዋል። አማካሪዎቹ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሹሙ የሚመጡ በመሆኑ፣ ከንቲባው ግራ ተጋብተዋል። አማካሪ የሚባሉት ሰዎች በጸሃፊያቸው በኩል አስፈቅደው ወደ እርሳቸው ቢሮ ከገቡ በሁዋላ ” እኔ እኮ የዚህ ዘርፍ አማካሪዎ ነኝ” ሲሉዋቸው፣ ከንቲባው በመደናገጥ ” ከስራ ብዛት ነው ያላወኩዎት” በማለት ይቅርታ እየጠየቁ ማሰናበት የተለመደ ተግባር ሆኗል።
ከንቲባው 10 በምክትል ከንቲባ ማእረግ የሾሙዋቸው የዘርፍ አማካሪዎች አሉዋቸው። ይሁን እንጅ በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ የዘርፍ አደረጃጃቶች በመኖራቸው እርሳቸው ፈርመው የሾሙዋቸውም ይሁን ከድርጅቱ የሚሾሙትን አማካሪዎችን ለይተው ለማወቅ ባለመቻላቸው፣ አማካሪዎቹ፣ ራሳቸውን እንዳማካሪ እየጠቀሱ በስብሰባዎች ላይ ሁሉ አስተያየት ሲሰጡ ከንቲባው በከፍተኛ ሁኔታ ይደናገጣሉ። በተለይም እርሳቸው የማያዉቋቸው ሰዎች ስራቸውን በተመለከተ በግምገማ ወቅት አስተያየት ሲሰጡ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የሚገቡት አቶ ድሪባ፣ ድንጋጤያቸው ለመደበቅ አለማወቃቸውን እንደምክንያት እንደሚያቀረቡ የውስጥ ታዛቢዎች ገልጸዋል።
አቶ ድሪባ የኦህዴድ አባል ቢሆኑም፣ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎች የሚተላለፉት በህወሃቶች ነው። ይሁን እንጅ ኢህአዴግ ስራ ያጡ አባሎቹን ለመያዝ ሲል በየጊዜው የሚሰጠው ሹሙት የአገር ሃብትን ከማባከን የዘለለ ውጤት እንደሌለው ምንጮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታው በቅርቡ በተደረገው ግምገማ ዝቅተኛ ነጥብ በማምጣታቸው ባሉበት ቦታ ላይ ላይቀጥሉ ይችላሉ ተብሏል።

Monday, August 24, 2015

በነባሩና በአዲሱ የድርጅቱ አመራር መካካል ልዩነት መኖሩን ብአዴን ገለጸ


ነኅሴ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርጅቱ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ እንደገለጸው፣ ለረጅም ጊዜ በአመራርነት ቆይቶ ስልጣኑን በመተካካት ሂደት ባስረከበውና ቁልፍ ስልጣኑን በተረከበው መካካል የመግባባት ችግር መኖሩን ገልጿል።
ነባሩ አመራር ሁሉንም ሃላፊነት አስረክቦ ድርጅቱን የመልቀቅና ራሱን ገለል አድርጎ ለመኖር ይፈልጋል ያለው ብአዴን፣ በዚህም ላይ ነባሩ አመራር በአዲሱ አመራር እንደማይረካና ተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያቀርብም ገልጿል።
ቁልፍ ስልጣን የተረከበው አዲሱ አመራርም የራሱን አቅም የማያውቅ፣ ስልጣኑን ካስረከበው ነባር አመራር ለመማር ፍላጎት የሌለው ነው ብሎአል።
በአዲሱ እና በነባሩ አመራር በኩል ለታየው አለመግባባት ምንጩ ዲሞክራሲያዊ ትግል አለመጎልበት፣ አድባርይነት ፣ ፊት ለፊት ለመታገል አለመፈለግ፣ ድክመቶችን ለመቀበል ፍላጎት አለመኖር፣ ሂስና ግለሂስን አለመቀበልና የድርጅቱን አሰራሮችን በተግባር ለማዋል ፍለጎት አለማሳየት ናቸው ብሎአል።
በቅርቡ ቁልፍ የሃላፊነት ቦታዎችን በተረከበው አመራርና በቆየው አመራር መካከል መደጋገፍ የሰፈነበት ግንኙነት ካልተፈጠረ መተካካቱ ህይወት አይኖረውም ብሎአል።
በአዲሱ አመራርና እና ሃላፊነቱን ባስረከበው አመራር መካካል የታየው ልዩነት፣ ነባር አመራሩ የመተካካት መርሆ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እንዲዛመዱ እየጠየቀ ነው። ምንም እንኳ አቶ በረከት ስምኦን በ11ኛው የድርጅቱ ጉባኤ ከስራ አስፈጻሚነት ቦታቸው እንደሚነሱ ቢታወቅም፣ ከዚህ ቀደም በተገለሉት በእነ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋ እና ሌሎችም አመራሮችና በአዲሱ አመራር መካካል የተፈጠረው ክፍተት ስጋት ላይ ሳይጥላቸው አይቀርም። አዲሱ አመራር ነባሩን አመራር የሚንቀው ሲሆን፣ ነባሩ አመራር ደግሞ አዲሱ አመራር የትግል ወኔ የለውም ሲል ይተቻል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብአዴን በተለያዩ ክልሎች እና በውጭ አገር የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን ለማደራጀት ያደረገው ሙከራ መክሸፉን አስታውቋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የድርጅቱን አስተሳሰብ እንደማይደግፉና ተወላጆቹን ለማደራጀት ቀደም ብሎ ያደረጋቸው ሙከራዎች መክሸፋቸውን አስታውቋል።

Source : Esat

ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ አስቸኳይ የገንዘብ እርዳታ ያስፈልጋል ተባለ


ነኅሴ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ 4 ነብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጋር የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በተያዘው አመት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ የተረጅዎች
ከግምት ውጪ ላሻቀበው የተረጅዎች አሀዝ ብቻ 230 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ በጋራ መግለጫው ላይ የተመለከተ ሲሆን፤ከዚህ መካከል መንግስት 33 ሚሊዮን ዶላር ያህሉን መመደቡና ቀሪው 200 ሚሊዮን ዶላር በአስቸክይ ከውጭ ለጋሾች የሚጠበቅ መሆኑ ተገልጿል።
2015 ከገባ አንስቶ እስካሁን ድረስ 386 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ እርዳታ ሲሰጥ መቆየቱ በመግለጫው ተጠቅሷል።
የተመድ የስብዊ እርዳታ ሃላፊ ዴቪድ ዴል ኮንቴ ፣ የኢትዮጵያ ሚቲሪዮሎጂ ድርጅት የበልግን ዝናብ አስመልክቶ ከተነበየው በጣም የከፋ የዝናብ እጥረት በበልግ ወቅት ተከሰቷል ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ፤ ትርፍ አምራች የነበሩት እንደ አርሲና ምእራብ አርሲ የመሳሰሉ አካባቢዎች ሳይቀሩ አሁን እርዳታን ይሻሉ።
እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወረዳዎች ቁጥር ከ49 ወደ 97 ከፍ ማለቱ፤ እንዲሁም አሣሳቢ ሁኔታ ላይ የደረሱና አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ህጻናት አሀዝም በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ ተገልጿል።
-በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ሚስ ጁሊያን ሜልሶክ- ለጋሽ ሀገሮች እስካሁን በጥሩ ሁኔታ እርዳታ ሲሰጡ መቆየታቸውን በማውሳት- አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ የከፋ በመሆኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተማጽነዋል።

Source :Esat

በሰቆጣ ከተማ ከፍተኛ የውሃ ችግር መከሰቱን ነዋሪዎች ገለጹ


ነኅሴ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተያዘው ክረምት በአብዛኛው ምስራቅና ሰሜን ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍሎች የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ የሰቆጣ ከተማና የአካባቢው ወንዞች በመድረቃቸው የውኃ እጥረቱ መከሰቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ነዋሪዎች ፣ በዝናቡ እጥረት የተነሳ የጉድጓድ ውሃ መጠን በማነሱ የሚጠጣ ውኃ እጥረት መከሰቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
“በከተማዋ በአጠቃላይ የውኃ ችግር ተከስቷል፡፡በከተማዋ የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ ልማት ጽህፈት ቤት ምን እየሰራ እንደሆን አናውቅም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ የውሃ መስመሩ በየሳምንቱ ተበላሽቷል እንደሚባሉ ይናገራሉ፡፡ በየቤቱ የሚገኘው የቧንቧ መስመር አገልግሎት በመቋረጡ የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት ከሌሊቱ አስር ሰዓት በመነሳት ወረፋ በመያዝ የገደል ውሃ ለመቅዳት መገደዳቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች በሌሊት ወጥተው እስከ ቀኑ አራት ሰዓት ድረስ አርፍደው ውሃ እንደሚያገኙ በምሬት ገልጸዋል፡፡
በከተማው ውስጥ ከፍተኛ የውኃ ችግር እንዳለ የሚገልጹት ሌላው የከተማ ነዋሪ ከዝናቡ መጥፋት ጋር ተያይዞ የሚታይ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡በከተማው ውስጥ ለውስጥ የሚያቋርጡና በዙሪያው ያሉ ወንዞች መድረቅ ህብረተሰቡ ከወንዝ ቀድቶ መጠቀም እንዳይችል አድርጓል፡፡ዝናብ አንድ አንድ ጊዜ ሲዘንብ እንዲህ ያለ መጨናነቅ እንደማይከሰት የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ አልፎ አልፎ በሚጥለው ዝናብ ከቆርቆሮ ላይ በመሰብሰብ የየዕለት ችግራቸውን ለመቅረፍ እንደሚሞክሩ ይናገራሉ። ዝናብ በወር አንዴ ብቻ መዝነቡንና ከዚህ ውጭ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የሚቆይ ካፊያ ብቻ መሆኑ የውኃውን ችግር እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ አስተድደር ከአሁን በፊት ውኃ በቦቲ በማቅረብ የህዝቡን ጊዜያዊ ችግር ለመቅረፍ ቢሞክርም፣ አሁን አገልግሎቱ በመቋረጡ የከተማው ህዝብ በችግር ላይ ነው፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚናገሩት በነሃሴ ወር ከአሁን በፊት እንደዚህ ዓይነት የውኃ ችግር ተከስቶ እንደማያውቅ ተናግረው፤አልፎ አልፎ በሚጥለው ዝናብ የደረቀውን መሬት ከማራስ አልፎ ወደ ከርሰ ምድር የሚዘልቅ ውኃ ባለመኖሩ ከመስከረም ወር በኋላ ከፍተኛ የውኃ ችግር ሊከሰት ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳላቸው አክለዋል።
የገዢው መንግስት አመራሮች ምንም አይነት ትኩረት ባለመስጠታቸው ህብረተሰቡ ለከፍተኛ የውሃ ችግር መጋለጡን የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ የጉድጓድ ውኃ ለመቅዳት በወረፋ ሰበብ ህዝቡ እርስ በርሱ ሲጣላ እና ቀኑን ሙሉ አንድ ጀሪካን ውኃ ለመቅዳት ተሰልፎ ስራ ሲፈታ በዝምታ ከማየት ሌላ የፈየዱልን የመፍትሄ ነገር የለም በማለት ይናገራሉ፡፡
ከአሁን በፊት ለሃያ አመታት ያገለግላል ተብሎ በከፍተኛ ወጪ የተሰራው የቧንቧ ውኃ ፣ ሶስት ዓመት ብቻ አገልግሎ ደርቋል።

Source : Esat