Thursday, November 5, 2015

የልማት ኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኞች ጋር በፈጠሩት ጸብ ሰራተኛው እየታመሰ ነው


ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ ዘመን ጋዜጠኞች ለዜና ዝግጅት በፌደራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ባመሩበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ” ልማታዊ ጋዜጠኛ ማሟላት የሚገባውን ስነ ምግባር ፈጽሞ የላችሁም የሚል ቁጣና ማስፈራሪያ አዘል” ንግግር የተናገሩዋቸው ሲሆን፣ ጋዜጠኞችም ” በድርጅቱ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ብለው ሰራተኞችን አነጋግረው ከዘገቡ በሁዋላ፣ ዋና ዳይሬክተሩ በገዛ ስልጣናቸው ሰራተኛውን አስገድደው ስብሰባ እንዲቀመጡ በማድረግ እና ስብሰባውን በመምራት የአቋም መግለጫ እንዲወጣ አድርገዋል።

በድርጅቱ ዌብሳይት ላይ እንዲወጣ ያደረጉት ዘገባ ” የፌዴራል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ አመራርና ሰራተኞች ማክሰኞ ጥቅምት 9/2008 ዓም በኤጀንሲው የሥብሰባ አዳራሽ ባካሄዱት ስብሰባ ጥቅምት 5/2007 ዓም ‹‹የኤጀንሲው ሰራተኞች የመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራር ነግሷል አሉ›› በሚል ርዕስ የወጣው ዘገባ በእውነታ ላይ ያልተመሰረተና የኤጀንሲው ሰራተኞች አቋም ያለመሆኑን ገለጹ የሚል ሲሆን፣ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍልም ዘገባውን ለንባብ ከማብቃቱ በፊት ይህን የማረጋገጥ ሃላፊነቱን አለመወጣቱ አግባብ አለመሆኑን በአቋም መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታትና ሃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ አፍራሽ ተልዕኮን አንግበው የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ሰራተኞችን ታግሎ ወደ መስመር ለማስገባት በትኩረት ይሰራል በማለት በሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል። ዘገባው ሰራተኞችን ከሁለት የከፈላቸው ሲሆን፣ ለአዲስ ዘመን መረጃዎችን የሰጡ ሰራተኞችን አጋልጡ በሚል በድርጅቱ ውስጥ አለመረጋጋት ተፈጥሯል።
ዘገባውን ባቀረቡት ጋዜጠኞች ላይ እስካሁን ስለተወሰደው እርምጃ የታወቀ ነገር የለም።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment