Thursday, May 19, 2016

በአሶሣ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ሰበብ የተፈናቀሉ 400 የአማራ ብሔር ተወላጆች ካለ ፍትሕ ከስድስት ዓመት በላይ እየተጉላሉ ነው

ግንቦት ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ቁጥራቸው ከ400 በላይ የሚሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከነባር ይዞታቸው መፈናቀላቸውን አስመልክቶ ለአማራ ክልል ብሶታቸውን አሰምተዋል።
ለአሶሣ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተብሎ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት 163 ሺህ ሄክታር መሬታቸው ላይ ካለምንም ካሳ ተነስተው ጎዳና ላይ መጣላቸውን ገልጸዋል። እስከ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ድረስ አቤት ቢሉም ሰሚ አካል ማጣቸውንና የፍትሕ ያለህ በማለት ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን አመልክተዋል።
ከቦታቸው መወሰድ በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ የመኖር ዋስትና ማጣቸውንና ከክልሉ ነባር ተወላጆች እኩል የአስተዳደር አገልግሎት እንደማያገኙም አስታውቀዋል። በአማራ ተወላጅነታችን ብቻ እኛ ላይ የተለየ አስተዳደራዊ በደል ተፈጽሞብናል ያሉት አርሶ አደሮቹ በክልሉ የነበረንን የእርሻ መሬት ከህግ ውጪ ተቀምተን የመኖሪያ ቦታ ከሌለንና ተሠማርተንበት በነበረው ግብርና ልጆቻችንን ማሳደግ ካልቻልን የኛ በክልሉ መኖር ትርጉም የለውም ብለዋል፡፡
ከ6 ዓመት በፊት ለአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ተብሎ ለተወሰደባቸው ቦታ ምትክ እንዲሰጣቸው ወይም ካሣ እንዲከፈላቸው የጠየቁት አባወራዎቹ ለዚህም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትንና ትምህርት ሚኒስቴርን በፍርድ ቤት ቢከሱም ሰሚ አካል አለማግኘታቸውን በመጥቀስ፡ ክልሉ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ጠይቀዋል፡፡
አቤቱታቸውን ለአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ቢሮ ለማቅረብ ከአሶሣ ወደ ባህርዳር ቢያቀኑም አቶ ገዱ ሊያነጋግሯቸው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ወኪላቸው ደብዳቤያቸውን እንዲቀበሉዋቸው አድርገዋል። ይህን ያህል ዓመት ካለ ፍትሕ ከቀያችን እንድንፈናቀል የተደረግነው የአማራ ብሔር ተወላጅ በመሆናችን ብቻ ነው ሲሉ መናገራቸውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል።

Source:

No comments:

Post a Comment