ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ችግሩ የተባባሰባቸው ወረዳዎች 438 መሆናቸው ተገለጠ። የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ሰሞኑን ለመንግስት አካላት ባሰራጨውና “አስቸኳይ” በሚል በበተነው ማሳሰቢያ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ድርቁ የተከሰተ ሲሆን፣ በአንዳንድ ወረዳዎች ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖ ተገኝቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያለ ሪፖርት ያወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ በውስጥ በኩል ባሰራጨው መረጃ መሰረት 100 ያህል ወረዳዎች ክፉኛ ተጠቅተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ለሚመለከታቸው አካላት ባለፈው ሳምንት ባሰራጨው ሪፖርት በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ ከተጠቁ 438ቱ ወረዳዎች 123ቱ በኦሮሚያ ክልል ሲሆኑ፣ በአማራ ክልል 80 ፥ በደቡብ 72 ፥ በሶማሊ ክልል 63 ፥ ወረዳዎች በተመሳሳይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአፋር ክልል በ32 ወረዳዎች፣ በትግራይ 31 ወረዳዎች፣ በጋምቤላ 13 ወረዳዎች በቤኒሻንጉል 9 ፥ በሃረር 2 ፥ እንዲሁም በድሬደዋ አንድ ወረዳ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቅተዋል።
በድርቅ ክፉኛ ከተጠቁት 438 ወረዳዎች 85 ያህሉ ወረዳዎች ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተመልክቷል። በተለይ በአፋር ድርቁ የተከሰተባቸው 32 ወረዳዎች ሁሉም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸው ይፋ ሆኗል። በኦሮሚያ ከ123ቱ ወረዳዎች 52ቱ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሲሆኑ፣ በአማራ ክልል ከ80 ተጠቂ ወረዳዎች 38ቱ ላይ የተባባሰ መሆኑም መደረጉ ተችሏል።
በትግራይም በድርቁ ክፉኛ የተጠቁ 31 ወረዳዎች 20ዎቹ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውም ይፋ ሆኗል። በሶማሊ ክልል ክፉኛ ከተጠቁት 63 ወረዳዎች 24ቱ ይበልጥ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ሲገለጽ፣ በደቡብ ክልል ከተጠቁት 72 ወረዳዎች 17ቱ ይበልጥ የከፋ ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸውንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰንጠረዥ አስደግፎ በውስጥ ካሰራቸው መረጃ መረዳት ተችሏል።
No comments:
Post a Comment