Thursday, January 7, 2016

በባህርዳር እስረኞች ለ2 ቀናት በቤተሰብ እንዳይጠየቁ ተደረጉ


ታኀሳስ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው እሁድ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ” በእስር ቤቱ ውስጥ ቦንብ ገብቷል” የሚል መረጃ ደርሶናል በሚል እስር ቤቱን በአድማ በታኝ ፖሊሶች አጥለቅልቀውና ዋናውን መንገድ በመዝጋት ጠያቂዎች እንዳይገቡ ከልክለዋል። በዚሁ ሰበብ በእስረኞች ላይ ከፍተኛ እግልት የደረሰ ሲሆን፣ ለሁለት ቀናት ያክል እስረኞች በቤተሰቦቻቸው እንዳይጠየቁ አግደዋል። በእስር ቤቱ ውስጥም ከፍተኛ ፍተሻ ተካሂዷል።
ዛሬ ታህሳስ 28 ከቀኑ 8 ሰአት ላይ እስረኞችን ለመጠየቅ መግባት እንደተጀመረ ድንገተኛ የተኩስ ድምጽ በመሰማቱ፣ ወታደሮች ጠያቂ ቤተሰቦችን ከአካባቢው በማባረር የተወሰኑትን አግደዋል።
የተኩሱ ትክክለኛ መንስኤ እስካሁን ባይታወቅም ፣ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ፖሊስ ግን በጣና ሃይቅ በኩል ለማምለጥ የሞከረን እስረኛ ለማስቆም በሚል ተኩስ መከፈቱን ለዘጋቢያችን ተናግሯል።
በባህርዳር ዋናው እስር ቤት መንግስትን ይቃወማሉ የሚባሉ በርካታ ወጣቶች ታስረው ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment