Tuesday, December 1, 2015

አርቲስት ግርማዬ ታደሰ ልማታዊ አርቲስቶችን ማዋረድ የሚል ክስ ቀረበበት

ኀዳር ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰዎች ምን ይላሉ የተሰኘው ኮሜዲ ድራማ አዘጋጆች ለእስር እየተዳረጉ ሲሆን አርቲስቶቹ ልማታዊ አርቲስቶችን ማዋረድ የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።ከአዘጋጆቹ አንዱ የሆነው አርቲስት ግርማዬ ታደሰ እስካሁን ድረስ ለሶስት ሳምንታት በእስር እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን ዋና አዘጋጁ በዋስና ወጥተዋል።
ሰዎች ምን ይላሉ የሚለው ኮሜዲ ፊልም ታትሞ ለገበያ ከቀረበ ከዓመት በላይ የቆየ ሲሆን ልዩ ልዩ የማኅበረሰቡን እለታዊ ሕፀፆችን የሚያስቃኘው ኮሜዲያዊ ፊልም በኢሳት መቅረቡ ገዥዎቹን እንዳስቆጣቸው ታውቋል።
አርቲስት ግርማዬ ታደሰ ከጥቅምት 29 ጀምሮ በእስር ላይ እንዳለ የታወቀ ሲሆን፡፡ አርቲስቱ ከህዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን ፖሊስ “ልማታዊ አርቲስቶችን በማዋረድና በመንግስት ላይ አመጽ በማነሳሳት”ወንጀሎች መጠርጠሩን ገልጾ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ስለጠየቀ አሁንም በተለምዶ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ እየተባለ በሚጠራው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስሮ ይገኛል፡፡
የሰዎች ምን ይላሉ ቁጥር 3 ዳይሬክተር አርቲስት አቤል አለማየሁ እንደገለጸው ከዚህ በፊት የተለያዩ ማስፈራሪያና ዛቻዎች ሲደርስባቸው የቆየ ቢሆንም አሁን ቪሲዲው ለህዝብ ከቀረበ ከ1 አመት ከሰባት ወር በኋላ ክስ የመጣብን ስራችን በኢሳት መተላለፉን ተከትሎ ነው ብሏል፡፡ አያይዞም ከስራ ባልደረባው መታሰር በኋላ እሱም በከፍተኛ ክትትልና ወከባ ውስጥ እንደሚገኝ መግለጹን ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጎስ በፌስቡክ ገጹ ዘግቧል።


No comments:

Post a Comment