Saturday, November 7, 2015

ከወያኔ አዲሱ ማደናገሪያ ይጠንቀቁ – በረከት ስምዖን ጉዳይ…


በጠዋቱ ወደ ዘ-ሐበሻ ዝግጅት ክፍል የሚደርሱ መረጃዎች በጠቅላላ “ድሬ ቲዩብ የተባለ ድረ ገጽ በረከት ስምዖን ሞቱ ብሎ ዘግቧል:: መረጃው እውነት ነው ወይ?” የሚሉ ናቸው:: ራሱ ድሬ ቲዩብ ድረገጽ እንዳሰራጨው መረጃ “በስሜ ሌሎች ሰዎች ያስወሩብኝ ወሬ እንጂ እኔ ማንም ባለስልጣን ሞተ ብዬ አልዘገብኩም” ብሏል::

ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው ወያኔዎች በየጊዜው ሕዝቡን ለማደናገር የተለያዩ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል:: በኢትዮጵያ ውስጥ የነፃ ፕሬስ ጋዜጦችን ለማስጠላትና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትን እንዳያገኙ ለማድረግ ራሱ ወያኔ ራሱ ባሰማራቸው ሰዎች የግል ጋዜጣ በማውጣትና ሐሰተኛ ወሬዎችን ለሕዝብ በማድረስ በኋላም ይህን ራሱ ያሰራጨውን ሃሰተኛ ዜና በሚቆጣጠራቸው ቲቭ እና ራድዮ “እዩ እነዚህ የግል ጋዜጦች የሚዘግቡትን ሃሰት እያለ” በአንዱ ስም ሌላውን ሲያጥላላ እና ተአማኒነት እንዲያጡ ሲያደርግ ቆይቷል::

አሁን ለሕወሓት መንግስት ራስ ምታት የሆነበት መረጃዎች በፍጥነት የሚደርሱት በሶሻል ሚዲያዎች እና በድረ ገጾች መሆኑ ነው:: በሃገሪቱ ያሉ ነፃ ጋዜጦች ተዘግተው ከ150 በላይ ጋዜጠኞቿ በተሰደዱባት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ከመንግስት ጫና ነፃ የሆነ ሚዲያ የላትም:: አብዛኞቹ መረጃዎች ከውጭ ሃገርም ሆነ ከሃገር ውስጥ የሚሰራጩት በድረገጾች እና በሶሻል ሚድያዎች በመሆኑ የሕወሓት መንግስት ሕዝቡ እነዚህን እንዳያምን ከዚህ ቀደም ያደርጋቸው የነበሩትን ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ነው::

ከነዚህም መካከል ራሱ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ራሱ የሚያስተባብልበት መንገድ አንደኛው ነው:: ሁለተኛው ደግሞ በርካታ ተሳዳቢዎችን በሶሻል ሚድያ በማሰማራት አንዱ አንዱን ብሄር እንዲሳደብና እንዲከፋፈል የሚያደርገው ጥረት ነው::

የሕወሓት መንግስት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከናቀው ቆይቷል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቅ አይመስለውም:: ሕዝብ ግን ከመንግስት በላይ የነቃና ሁሉን የሚያውቅ መሆኑን በተደጋጋሚ አውቋል:: አሁንም ሕዝቡ እንደ በረከት ስምዖን ሞቱ አይነት የሕወሃት መንግስት ሆን ብሎ የሚያሰራጫቸውን ዜናዎች በብልጠት በማየት ጥሬውን ከገለባው መለየት ይኖርበታል::

በርግጥ አቶ በረከት በከፍተኛ ሕመም እንደሚሰቃዩና በተደጋጋሚ በሳዑዲ አረቢያ; በደቡብ አፍሪካና የተለያዩ ሃገሮች ህክምናቸውን እየተከታተሉ ወደ ሃገር ቤት እንደሚመላለሱ የታወቀ ነው:: ሼህ መሀመድ አላሙዲም በአንድ ወቅት ደቡብ አፍሪካ እጁን አንጠልጥዬ ወስጄ ያሳከምኩት እኔ ነኝ ሲሉ ስለ አቶ በረከት መናገራቸው አይዘነጋም::

The post ከወያኔ አዲሱ ማደናገሪያ ይጠንቀቁ – በረከት ስምዖን ጉዳይ… appeared first on Zehabesha Amharic.

Source:: Zehabesha

No comments:

Post a Comment