ኀዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ድርጊቱ የተፈጸመው ባለፈው መስከረም ወር ሲሆን የቀብሩ ስነስርዓት የተፈጸመው ግን ባሳለፍነው ሳንምት ነው። በመተከል ዞን በዳንጉር ወረዳ 12 የአማራ ተወላጆች ለቀን ስራ ተብለው ከተወሰዱ በሁዋላ በወረዳው አስተዳደሪ ትእዛዝ ኮከል ቀበሌ ላይ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ተረሽነዋል።አስከሬናቸው ተቆራርጦ በጆንያ ተጠቅሎ መገኘቱንና የቀብር ስነስርዓታቸውም መፈጸሙን ምንጮች ገልጸዋል። የተገደሉት ነዋሪዎች 20 የሚደርሱ ሲሆን፣ እስካሁን አስከሬናቸው የተገኘው የ12ቱ ብቻ መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ አስከሬኑ ሊገኝ የቻለው አንድ የአካባቢው ተወላጅ ወጣት መጥፋቱን ተከትሎ ቤተሰቦቹ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ፍለጋ በመጀመራቸው ነው። የወጣቱን አስከሬን ለማውጣት ፍለጋ ሲጀመር፣ የሌሎችም አስከሬን በጆንያ ተጠቅሎ ከተገኘ በሁዋላ ህዝቡ በማውጣት ቀብሯቸዋል። ለሌሎች አስከሬኖች መገኘት ምክንያት የሆነው በአካባቢው ተወልዶ ያደገው ወጣት ከዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ ስራ በመፈልጋ ላይ የነበረ ነው። ወጣቱ ከዚህ ቀደም ከክልሉ በተባረሩት የአማራ ተወላጆች ዙሪያ ባለስልጣናትን በአደባባይ በመንቀፍ የታወቀ ሲሆን፣ እሱና ሌሎች ሟቾች ክልሉ የአማራ ተወላጆችን ለማስወጣት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ይቃወማሉ ተብለው ሲጠረጠሩ ቆይቷል። ምንጮች እንደሚሉትም ለመገደላቸው ምክንያት የሆነውም በክልሉ ነዋሪ በሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ በባለስልጣናት የሚፈጸመውን ኢሰባዊ ድርጊት በመቃወማቸው ነው። ጉዳዩ ያበሳጫቸው የሟች ቤተሰቦች አስከሬኖቹን እየቆራረጡ በጆንያ ከተዋል በተባሉ ሰዎች ላይ ክስ ሲመስርቱ፣ እኛ ከመንግስት ታዘን ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል። እነዚሁ ቤተሰቦች ባደረጉት ማጣራት የግድያ ትእዛዙ በቀጥታ የመጣው ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ምክትል ፕሬዚዳንት ከአምባሳደር ምስጋናው መሆኑን ለማረጋገጥ ችለዋል። ኢሳት መረጃው እንደደረሰው በቀጥታ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ስልክ ቢደውልም ጸሃፊያቸው ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከክልሉ ውጭ መሆናቸውን፣ መግለጫ ለመስጠት የተመደቡ ሰው መኖራቸውን ገልጸው ስልካቸውን ቢሰጡንም፣ በሰጡን ስልክ ብንደውልም መረጃ ይሰጣሉ የተባሉትን ሰው ለማግኘት አልቻልንም። በመቀጠልም ከክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ትእዛዝ ተቀብለው ግድያውን አስፈጽመዋል ለተባሉት ግድያው ሲፈጸም የወረዳው አስተዳደሪ ለነበሩትና ከግድያው በሁዋላ በሹመት የዞኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆነው ወደ ተሾሙት አቶ አስማማው ላቀው በቀጥታ ስልክ በመደወል ለማናገር ሞክሯል። አቶ አስማማው በመጀመሪያ እርሳቸው መሆናቸውን ከገለጹ በሁዋላ፣ ጥያቄው ሲቀርብላቸው፣ "አስማማሁ አይደለሁም" ብለው ስልኩን ዘግተውታል። ከዚያ በሁዋላ በተደጋጋሚ ቢደወልላቸውም ስልካቸውን አያነሱም፣ በመጨረሻም ስልካቸውን ዘግተዋል። ። አቶ አስማማው የጉሙዝ ብሄረሰብ ተወላጅ ናቸው። በመቀጠል ደግሞ ግድያው ከተፈጸመ በቤተሰብ አባላት ክስ መመስረቱን ተከትሎ ግድያው አይጣራም በሚሉት በአቶ አስማማውና ግድያው መጣራት አለበት በማለት አቋም በወሰዱት በምክትል አስተዳዳሪው አቶ ጌታሁን እጅጉ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር በደረሰን መረጃ መሰረት በቀጥታ የእጅ ስልክ አቶ ጌታሁንን ደውለን አናግረናቸዋል። አቶ ጌታሁን አሁን ከሃላፊነት የተነሱ በመሆኑ መረጃ በስልክ ለመስጠት ዋስትና የሌላቸው መሆኑን በመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ቢገልጹም፣ እያመነቱም ቢሆን አንዳንድ መረጃዎቸን ሰጥተዋል። አቶ ጌታሁን ግድያ መፈጸሙን አረጋግጠዋል። አቶ ጌታሁን እንዳሉት የሟች ቤተሰቦች አቤቱታ ሲያቀርቡ የወረዳው አስተዳዳሪና ፖሊስ አዛዡ አጣርተናል የተፈጸመ ግድያ" የለም" ብለው በመመለሳቸው እና ቤተሰቦች አቤቱታ በማሰማታቸው፣ እኔም "ሰውን የሚያክል ነገር ተገድሎ ግማሽ ሰው እንኳ ቢሆን ዝም ማለት የለብንም በማለት ፣ የመንግስት አካላትን ሽምቅ ሃይልንና ሌሎችንም በርካታ ሰዎች አቀናጅቼ ሰዎችን ወደ አካባቢው በመላክ አጣርተው እንዲመጡ አድርጌ በሁለተኛው ቀን ያው አስከሬኖቹ መጡ ፣ አስከሬኑ ከመጣ በሁዋላ ነዳጅ አስሞልቼ በትራክተር ቤተሰብ ጋር እንዲደርስ አድርጌአለሁ ፣ እስከነበረኝ ሃላፊነት ይህንን አድረጌአለሁ ብለዋል። እሳቸው የላኩዋቸው መርማሪዎች ሁለት አስከሬኖችን ይዘው መምጣታቸውን ፣ ነገር ግን ሁለት ብቻ አይደለም በሚል ጥያቄ ለዞን ባለስልጣናት ቀርቦ ፣ ፖሊስና አጣሪ ሃይል ከተላከ በሁዋላ፣ አጣሪ ቡድኑ በጉድጓዱ ውስጥ የተቆረጠ እግር ብቻ መገኘቱን በግምገማው ሪፖርት ቢያደርግም፣ እሳቸው በግምገማው ላይ ስላልተገኙ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል። ሃያ ነው ወይም ከዛ በላይ ነው የሚለውን መረጃ በግምገማው ላይ ባለመገኘቴና በቦታውም ምርመራ ባለማድረጌ ለማወቅ ባልችልም፣ የአካባቢው ነባር ነዋሪዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች መረጃውን ይበልጥ ስለሚያዉቁት እነሱን ብታናግሩቸው የበለጠ መረጃ ይሰጡዋችሁዋል ብለዋል። አቶ ጌታሁን በቅርቡ ከሃላፊነት መነሳታቸውን ገልጸው ለምን እንደተነሱ ግን እንደማያውቁ ተናግረዋል። አቶ ጌታሁን የሽናሻ ብሄረሰብ ተወላጅ ናቸው። በ2005 ዓም በቤንሻንጉል ጉሙዝ የአማራ ተወላጅ ተብለው የተለዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ መጣችሁበት ክልል ተመለሱ በሚል ከክልሉ እንዲወጡ ከተደረጉ በሁዋላ፣ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ከፍተኛ ጫና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነዋሪዎች ላይ የመንግስት ባለስልጣናት ቂም ቋጥረው የተለያዩ በደሎችን ሲያደርሱባቸው መቆየታቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ለአማራው ህዝብ መብት መከበር ቆሜያለሁ የሚለው ብአዴን 35ኛ አመቱን በማክበር ላይ ነው። እስካሁን በእነዚህ ዜጎች ላይ ስለተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ያወጣው መግለጫ የለም። በግድያው እጃቸው አለበት የተባሉ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምርመራ አልተደረገባቸውም። ቀደም ብሎ በተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትም፣ የተጠየቁት መለስተኛ የወረዳና የቀበሌ ባለስልጣናት እንጅ፣ ዋናዎቹ ባለስልጣናት አይደሉም።
No comments:
Post a Comment