ዛሬ ጥቅምት 15/2008 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት 3 ያህል እስረኞች ማምለጣቸውን የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ እስረኞቹ በተለምዶ ሰባራ ባቡር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ፍርድ ቤት ፊት ለፊት አስፓልቱ ላይ ከመኪና ወርደው ወደ ፍርድ ቤቱ በሚገቡበት ወቅት መጥፋታቸውን የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ ሶስት ያህል እስረኞች እንዳመለጡ የተገለፀ ሲሆን አንድ ከሶማሊ ክልል የመጣ ነው የተባለ እስረኛ በጥይት ተተኩሶ እንደተገደለም የአካባቢው ነዋሪዎች አክለው ገልፀዋል፡፡ እስረኛው ፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ከሚገኘው አስፓልት ወጥቶ 200 ሜትር ያህል ወደ ሰፈር ከገባ በኋላ ከኋላው ተመትቶ እንደተገደለ እማኞቹ የተናገሩ ሲሆን፣ የሶማሊ አካባቢ ተወላጅ መሆኑን የተናገሩት ፊቱን እና ቁመቱን በማየት መሆኑን ገልጸዋል። እስረኞች የት እንደገቡ ባለመታወቁ ፖሊስ ወጣቶችን ከቤታቸው እያስወጣ ፍተሻ አካሂዷል፡፡ አንድ ወጣት ‹‹ልብሴን እየለበስኩ እያለ ፖሊስ አመናጭቆ ከቤት አስወጣኝና እኔ እስረኛው እንዳልሆንኩ ካዬ በኋላ ቤታችንን በረበረው፡፡ እስካሁን ድረስም መግባት አልቻልኩም›› ሲል ተናግሯል። በሌላ በኩል የተገለደውን እስረኛ ለማየት የአካባቢው ነዋሪ በብዛት በተሰበሰበበት ወቅት ፖሊስ ህዝቡን በትኗል፡፡ ሁኔታው ሲረጋጋ ህዝቡ አስከሬኑን ማየት የቻለ ሲሆን፣ ህዝቡ ለፖሊስና ለአንቡላንስ ሾፌሩ ለአስከሬኑ ክብር ስጡት እያለ ጠይቋል፡፡ አንድ የአይን እማኝ፣ ፖሊስ አስከሬኑን በክብር እንዲይዘው በተጠየቀበት ወቅት፣ የአንቡላንስ ሾፌሩ ጣልቃ ገብቶ ‹‹እኛ ይህ አያስጨንቀንም፡፡ ብዙ የሚያስጨንቀን ነገር አለ፡፡ ይህን እንደማንም ቀጥቅጠን እናስተካክለዋለን›› ብሎ በመመለሱ ማዘኑን ገልጿል። አስከሬኑ እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ አልተወሰደም ነበር። አካባቢውም በመከላከያ አባላት ታጥሮ ውሏል፡፡ ሌሎች እስረኞችም ከመኪና ላይ ወርደው በጊዜያዊ ማቆያ ቦታ እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡
No comments:
Post a Comment