የኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኛ ወንጀል ይፈለጋሉ በማለት ኬንያ 131 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን አሳልፋ እንድትሰጠው ጥያቄ መቅረቡን የምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ሊግ ገለጠ።
የኢትዮጵያ የደህንነት እና ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ለኬንያ አቻው ያቀረበውን ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎም በእስካሁኑ ሂደት አቶ ደበሳ ጉያ የተባለ ስደተኛ ኢትዮጵያ የገባበት ሊታወቅ አለመቻሉን የሊጉ ፕሬዚዳንት አቶ ጋሩማ በቀለ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በሽብርተኛ ወንጀል እፈልጋቸዋለሁ ብላ ስማቸው አስተላልፋ የሰጠቻቸው 131ዱ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በኬንያ ለ20 ዓመታት ያህል የኖሩና ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ገልጸዋል።
የኬንያ መንግስትም ኢትዮጵያኑን ስደተኞች አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥያቄ መቅረቡን የሊጉ ሃላፊ በሰጡት ቃለምልልስ አስታውቀው የኢትዮጵያውኑ ደህንነትም አሳሳቢ ሆኖ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
መንግስት በሽብርተኛ ወንጀል እፈልጋቸዋለሁ ያላቸው ስደተኞች በሃገሪቱ ያለን እስርና እንግልት በመሸሽ ኑሯቸውን በኬንያ አድርገው እንደሚገኙ የሰብዓዊ ሊጉ ሃላፊ አቶ ጋሩማ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ ነጻነት ግንባት ታጣቂዎች እፈልጋለሁ በማለት በየጊዜው ድንበርን በመጣስ በኬንያ ወታደራዊ ዘመቻን ሲፈጽም መቆየቱን የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት ኣንዲሁ የኬንያ የደህንነት ሃይሎች ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በኬንያ ጥገኝነት የሚፈልጉ የፖለቲካ ስደተኞችን አሳልፈው ይሰጣሉ ሲሉ ተቃውሞ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ባለፈው አመትም የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ለድርድር በናይሮቢ የተገኙ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ሁለት አመራሮችን በማገት ወደአዲስ አበባ መወሰዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፥ ከአመት በኋላም መለቀቃቸው ይታወሳል።
የኬንያ መንግስትም ለእገታው ድርጊት ተባብረዋል ባላቸው ሁለት የሃገሪቱ ፀጥታ ሃይሎች ላይ ክስን የመሰረተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች በተደጋጋሚ የሚወስዱት እርምጃ በድንበር አካባቢ ለሚኖሩ ኬንያውያን የፀጥታ ስጋት መፍጠሩን ነዋሪዎች ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
የኬንያ መንግስት ተወካዮች ሊጉ ላቀረበው ጥሪ እንደሚተባብሩ ቢገልፁም የገባበት ስላልታወቀው አንድ ኢትዮጵያዊ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ምላሽ መስጠታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment