Friday, September 18, 2015

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የግል ትምህርት ተቋማት የትምህርት አገልግሎት አሰጣጥና የክፍያ ስርዓት መመሪያ አወጣ፡፡


መስከረም ፯ (ሳባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዋጋ ቁጥጥር ውሳኔው አንዳንድ ት/ቤቶች አደናግጦአቸዋል፡፡
መመሪያው ፍትሐዊነት ጎድሎታል ያለውን የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ሁኔታ ሰርኣት የሚያሲዝ ነው ቢባልም ፣ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው።
አዲሱ መመሪያ ከስርኣተ ትምህርት ውጪ ልዩ ልዩ የትምህርት ኣይነቶችን ማስተማርና ለዚህም ክፍያ መጠየቅ ይከለክላል፡፡ ክፍያ ሲጠየቅ ለ10 ወራት ብቻ መሆኑን፣ የክረምትና የቅዳሜና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርቶች ወላጆች ሙሉ ስምምነት ካልጸደቀ ስራ ላይ ሊውል እንደማይችል ደንግጎአል፡፡ በአጠቃላይ ተጨማሪ ትምህርቶችን ለማስተማር ወይንም አንድን ትምህርት በሌላ ቋንቋ በማስተማር ስም ተጨማሪ ክፍያ መሰብሰብ የተከለከለ መሆኑን አስቀምጦአል፡፡
ይህን መመሪያ በማያከብሩ የትምህርት ተቋማት ላይ የአዲስአበባ ትምህርት ቢሮ ፈቃድ እስከመንጠቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቆአል፡፡ መመሪያው ሊወጣ የቻለው ትምህርት ቤቶች የተጋነነ ዋጋ በመጠየቅ የዋጋ ንረትን የማባባስ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተደጋጋሚ ቅሬታ በመቅረቡ ተከትሎ ነው ተብሎአል።
የአንድ የግል የትምህርት ተቋም ርዕሰ መምህር ለአዲስአበባው ዘጋቢያችን በሰጡት አስተያየት የትምህርት ቢሮው ግብታዊ ውሳኔ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን መስማታቸውን በመጥቀስ በሁኔታው ለመስማማት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተጋነነ ዋጋ ተጠይቆአል ሲባል ለምንድነው የተጠየቀው ብሎ መልሶ መጠየቅ ይገባል ያሉት መምህሩ፣
ባለሃብቶች ከፍተኛ መዋዕለንዋይ አውጥተውና ተቋም አደራጅተው፣ በውድ ዋጋ መምህራንን ቀጥረው ወጪያቸውን የሚያካክስና ተገቢ የሆነ የትርፍ ህዳግ የጠበቀ የአገልግሎት ክፍያ መጠየቃቸው አግባብ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት የነጻ ኢኮኖሚ መርህ እከተላለሁ፣ በገበያ ስርኣት እመራለሁ በማለቱ እሳቸው የሚያስተምሩበት ተቋም ባለቤት ከውጭ ሀገር ወደሀገር ውስጥ በመመለስ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋያ አፍስሰዋል፡፡ ዛሬ ይህ የነጻ ገበያ መርህ በዋጋ ቁጥጥር የሚተካ ከሆነ ከኢንቨስትመንቱ ከመውጣት ውጭ አማራጭ የለንም ብለዋል፡፡
በየጊዜው ት/ቤቱ ዋጋ ሲጨምርም ከወላጆች ጋር ተመካክሮ ችግሩን አሳምኖ ነው ያሉት መምህሩ፣ በግብታዊነት እንደሚጨመር፣ አሻጥር እንዳለ አድርጎ ት/ቤቶችን ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ማብጠልጠልና መመሪያ አውጥቻለሁ እያሉ ማስፈራራት ከአንድ መንግስታዊ አካል የሚጠበቅ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
አንድ በአጸደ ህጻናት የትምህርት ስራ የተሰማሩ ግለሰብ ስለጉዳዩ ከሰዎች ሰምተው መደንገጣቸውን በመጥቀስ በአሁኑ ሰኣት ምንም ዓይነት አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡
Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment