Tuesday, September 8, 2015

አራት የተቃዋሚ ድርጅቶች ጥምረት መመስረታቸውን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ቀረቡ


ጷግሜን ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በስልጣን ላይ ያለውን የኢህአዴግ አገዛዝ በሃይል ለማስወገድ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ” አገር አድን ሰራዊት” ማቋቋማቸውን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየቀረቡ ነው።
የአፋር ድርጅት የጋራ ንቅናቄ፣ የትግራይ ህዝብ የጋራ ንቅናቄ፣ የአማራ ዲሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄ እና አርበኞች ገንቦት 7 ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ በጋራ የአገር አድን ንቅናቄ የሚባል ድርጅት መመስረታቸውን ጳጉሜ 3 ቀን 2007 ዓም ያስታወቁ ሲሆን፣ ንቅናቄው የራሱ ስራ አስፈጻሚና የተለያዩ መምሪያዎች ይኖሩታል ተብሎአል። አዲሱ ንቅናቄ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋን በሊቀመንበርነትና አቶ ሞላ አስገዶምን በምክትል ሊቀመንበርነት መርጧል። ከእነዚህ አባል ደርጅቶች የተውጣጣ አገር አድን ሰራዊት መቋቋሙም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይወድ በግድ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የሃይልን አማራጭ እንዲቀበል በመገደዱ፣ አገዛዙን ለማስወገድ የጋራ እንቅስቃሴው ተጀምሯል ሲል መግለጫው ያክላል።
ንቅናቄው ከሌሎች ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ከሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ጋር ተጣምሮ ለመስራት ጥረቱን እንደሚቀጥልም ገልጿል።
መግለጫውን ተክትሎ ጥምረቱን በአወንታዊ መልኩ የተቀበሉ በርካታ አስተያቶች ለኢሳት በኤሜል መልእክት ደርሰዋል። አንዳንድ ሰዎች ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችንም ልከዋል።
ዜናው አዲስ መነቃቃት የፈጠረና የገዢውን ፓርቲ እድሜ ለማሳጠር ወሳኝ ምእራፍ መሆኑን የሚገልጹ በርካታ አስተያየቶች ሲቀርቡ፣ ኦነግና አብነግ ለምን አልተካተቱም የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።
አንድ አስተያየት ሰጪ ” ወያኔ የተባለ ሃገርን ከፋፋይ የፖለቲካ ነቀርሳ ነቅሎ ለመጣልና ለማሸነፍ ለሚደረግ ትግል አቅም የተፈጠረበትን የፖለቲካ ድርጅቶች የአንድነት ዓላማ ትብብር ዜና ከመስማት የበለጠ የሚያስደስት የታሪክ አጋጣሚ ለማከፈል ከመታደል የበለጠ አስደሳች ነገር ሊኖር አይችልም!!! ብራቦቦቦቦቦቦ ለፕ/ር ብርሃኑ ነጋና ለሌሎች ሃገር ወዳድ ፖለቲከኞች!!!!! ቪቫ ለመረጃ ምንጫችን ኢሳት” የሚል መልእክት ሲልክ፣ ሌላው የስርዓቱ ደጋፊ ነኝ ያለ ሰው ደግሞ ” ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ እንዲሉ በገባችሁበት ገብተን እንደመስሳችሁዋለን” ብሎአል። “የኦሮሞ ፖለቲከኞች በጥምረቱ አለመካፈላቸው አሳዝኖኛል፣ ለወደፊቱም ተጣምረው ይታገላሉ” የሚል ተስፋ አለኝ ሲል ዱኪ የተባለ አስተያየት ሰጪ ጽፏል።
የህወሃት ደጋፊ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ገዢው ፓርቲ ” ሳይቀጠል በቅጠል” የሚል ብሂል በመጥቀስ ኢህአዴግ እርምጃ እንዲወስድ እየጠየቁ ነው።
ካለፉት ሶስት ወራት ጀምሮ አርበኞች ግንቦት7ትን ለመቀላቀል ጥያቄ የሚያቀርበው ወጣት ቁጥር እንዲሁም ድርጅቱን ለመርዳት የባንክ አካውንት የሚጠይቀው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የድርጅቱ አመራሮች ይናገራሉ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች ትግሉን በአካል እንቀላቀል የሚል ጥያቄ ከማቅረብ ውጭ፣ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መረጃዎችን እየጠየቁ በመሆኑ ድርጀቱ በቅርቡ መረጃ እንደሚሰጥ አመራሮች ይገልጻሉ።
ገዢው ፓርቲ ጥምረቱ ስላወጣው መግለጫ ምንም ያለው ነገር የለም። ይሁን እንጅ የኤርትራ መንግስት በህወሃት በኩል የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ አውጥቷል። በኤርትራ በኩል ይህ ነው የሚባል ወታደራዊ ዝግጅት ወይም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደማይታይ የኤርትራ ምንጮች ይገልጻሉ።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment