Tuesday, September 8, 2015

አቃቢ ህግ በአርበኞች ግንቦት7 ስም በተከሰሱት ላይ ምስክሮችን አሰማ


ጷግሜን ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አቃቢ ህግ ምስክሮችን ያሰማው በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ችሎት ላይ ሲሆን፣ በተከሳሾች ወርቅዬ ምስጋናው፣ አማረ መስፍን፣ ቢሆኝ አለናና አትርሳው አስቻለው ላይ 6 ምስክሮች ቀርበው መስክረዋል።
ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው አቃቢ ህግ ያቀረባቸው 13 ምስክሮች ማን ላይ እንደሚመሰክሩ ግልጽ አድርጎ ባለማቅረቡ ጠበቆች ተቃውሞ አስምተዋል።
አንደኛው ምስክር በ12ኛው ተከሳሽ አትርሳው አስቻለው ላይ በመሰከረበት ወቅት፣ “ለየትኛው ድርጅት ተመለመለክ ?” ተብሎ ሲጠየቅ፣ ለአርበኛው ግንባር፣ ለአርበኛው ግንባር ግንቦት7፣ ለግንቦት7፣ አርበኛው ግንባር ለግንቦት7″ የሚሉ የተለያዩ ስሞችን መናገሩን ጋዜጣው ዘግቧል።
ኤርትራ ምን ትስራለህ ተብለህ ነው እንደትሄድ የተጠየከው ተብሎ ሲጠየቅ ደግሞ ” ኤርትራ ውስጥ የተሻሻለ ዲሞክራሲያዊ መንግስት አለ ተብለንና ተመልሰን ይህን መንግስት እንድንወጋ ነው” ብሏል። ምስክሮቹ ተመለመልን ያሉበትን ቀን፣ ተደዋወልን ያሉባቸውን ስልኮች እንደማያስታውሱ ገልጸዋል።
ሶስተኛው ምስክር 12ኛው ተከሳሽ ያልምንም ጫና ቃሉን ሲሰጥ አይቻለሁ ብሎ የመሰከረ ሲሆን፣ ግለሰቡን አሳይ ሲባል ” ሁለት ተከሳሾችን በመጠቆም ከሁለቱ አንዱ ብሎ መልሷል። መርማሪ ፖሊሶች ተከሳሾች የተቀመጡበትን ቦታ ለመስካሪዎች ማሳየታቸው ያልተዋጠላቸው ተከሳሾች፣ ቦታ ቀይረው በመቀመጥ ምስክሮችን አደናብረዋቸዋል። 4ኛው ምስክር ወደ ችሎት ገብቶ 12ኛ ተከሳሽን እንዲያሳይ ሲጠየቅ፣ ቦታውን ቀይሮ የተቀመጠውን 10ኛውን ተከሳሽ ጠቁሟል።
5ኛ ምስክር 9ኛ ተከሳሽ አቶ ቢሆነኝ አለነ ለኮንስትራክሽን የስራ ልምድ እንዲፅፍለት ሲጠይቃቸው ኤርትራው ውስጥ የተሻለ እንድል እንዳለ በመግለፅ ወደ ኤርትራ ለመላክ መልምሎኛል ብሎአል።
በ2005 ዓ.ም በማያውቀው ወንጀል ታስሮ እንደነበር የገለፀው 6ኛ ምስክር ይህንን በደሉን ለ6ኛ ተከሳሽ ወርቅዬ ምስጋናው እንዲሁም ለ7ኛ ተከሳሽ አማረ መስፍን አማክሯቸው ሁለቱ ተከሳሾች ኤርትራ ከሚገኝ ሰው ጋር በስልክ እንዳገኙት የተናገረ ሲሆን፣ የተከሳሾቹ ጠበቃ ምስክሩ በእስር ላይ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት በግዳጅ ለምስክርነት ቀርበው እንደሆነ ጥያቄ ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአቃቤ ህግና በጠበቃዎች መካከል በነበረው ክርክር ለአቃቤ ህግ በተደጋጋሚ በመበየኑ፣ ጠበቃዎች ለአቃቤ ህግ የተለየ መብት ተሰጥቶታል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
አቃቤ ህግ ነገ ጳግሜ 4/2007 ዓ.ም በቀሩት ተከሳሾች ላይ 14ት ምስክሮችን ያሰማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment