Friday, September 4, 2015

በአርባምንጭ የአንድ ቤተሰብ አባላት በስቃይ ላይ ናቸው


ነኅሴ ፳፰ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ የአንድ ቤተሰብ አባላት ልጆቻችሁ የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ናቸው በሚል ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ለኢሳት ገለጹ።
ፈቃዱ አበበ የተባለው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ወንድምህ አርበኞች ግንቦትን እንዲቀላቀል አድርገኸዋል በሚል ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ በማእከላዊ እስር ቤት ታስሮ እየተሰቃየ ሲሆን፣ የእርሱ ታናሽ ወንድም ደግሞ በፖሊሶች ከፉኛ ተደብድቧል።
ይህም አልበቃ ብሎ፣ አባትየው አቶ አበበ አስፋውና ሴት ልጃቸው ከታሰሩ በሁዋላ፣ ፍርድ ቤት በዋስ ለቋቸዋል። ፖሊሶች በቤታቸው ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ሳይኖር የጦር መሳሪያ ደብቀዋል የሚል ክስ እንደከፈቱባቸው የሚናገሩት ቤተሰቦች፣ መሳሪያ ተፈትሾ አግኝተናል የሚል ምስክር በመጥፋቱ ፖሊሶች ራሳቸው ምስክር ሆነው ሊቀርቡ መሆኑን ይገልጻሉ።
ምንም በማናወቀው ጉዳይ እንሰቃያለን የሚሉት ቤተሰቦች፣ የቀበሌ መታወቂያ ሳይቀር እንዳይሰጣቸው መከልከላቸውን ይናገራሉ
በሌላ በኩል ደግሞ
አቶ ሀብታሙ አያሌው ቂሊንጦ እስር ቤት ላይ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ አቶ ሀብታሙ አያሌው ነሀሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከተከሰሰበት የሽብር ወንጀል ነጻ ነው በማለት ከእስር እንዲፈታ የሰጠው ትዕዛዝ ተከብሮ እንዲፈታ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ዛሬ ነሀሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው እና መልስ እንዲሰጥ የተጠራው የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ተወካዮች ሲሆኑ፣ የእስር ቤቱ የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊ ጣዕመ ደምሴ አቶ ሀብታሙ አያሌውን ለምን ከእስር እንዳልለቀቁ አስረድተዋል፡፡ ኃላፊው እንደሚሉት አቶ ሀብታሙ ከቂሊንጦ እስር ቤት ያልተፈታበት ምክንያት እስር ቤቱ ከአቃቤ ህግ ይግባኝ እንደተጠየቀበት እና ይህን ተከትሎ ተያይዞ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጻፈ የእግድ ትዕዛዝ ስለደረሳቸው ነው፡፡
ኃላፊው እንደገለጹት የመፈቻ ደብዳቤው እና የእግድ ትዕዛዙ የደረሳቸው ነሀሴ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሆን አቶ ሀብታሙ ግን ከእስር መፈቻ ትዕዛዙ የተጻፈለት ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ነጻ ናችሁ የሚል ብይን በተሰጠበት ዕለት፣ ማለትም ነሀሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመሆኑም አቶ ሀብታሙ የማስፈቻ ደብዳቤው እንደተጻፈለት ከእስር ሊለቀቅ ይገባ ነበር፡፡
በሌላ በኩል አቶ ሀብታሙ አያሌው ይግባኝ እንደተጠየቀበትና የእግድ ትዕዛዝ ለቂሊንጦ እንደተጻፈ በወቅቱ በደብዳቤ ጭምር መረጃ የጠየቀ ቢሆንም እንዳልተነገረው ለተረኛ ችሎቱ አስረድቷል፡፡ በዚህም ቤተሰቦቹ ለእንግልት፣ አቶ ሀብታሙ ደግሞ ለሞራል ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግሯል፡፡ ቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ግን ይህን ባለመቀበል በጊዜው መረጃ መስጠቱን ይከራከራል፡፡
ተረኛ ችሎቱ የቀረበለትን አቤቱታ እና የአስተዳደሩን መልስ ከሰማ በኋላ ቂሊንጦ እስር ቤት ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሰውን ትዕዛዝ እንዳስፈጸመ በመጥቀስ ትክክለኛ ነው ሲል በይኗል፡፡ በመሆኑም አቶ ሀብታሙ አያሌው በእስር ቆይቶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ብይን እንዲጠብቅ ታዝዟል፡፡ አቶ ሀብታሙ የተረኛ ችሎቱን ብይን ከሰማ በኋላ ‹‹ይህ ችሎት ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ነው፤ የውሳኔ ግልባጩ ይሰጠኝና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው አደርጋለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡
አቶ ሀብታሙ አያሌው ከሌሎች አራት ተከሳሾች ጋር መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment