Friday, September 25, 2015

ኢህአዴግ ከድርጅት የሚለቁትን እያገደ ነው


መስከረም ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ኢህአዴግ በመቀሌ ላይ ባደረገው ጉባኤ ግንባሩን ጥለው የሚወጡ ሰዎች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨመሩን የገለጸ ቢሆንም፣ አሁንም ድርጅቱን ጥለው የሚወጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ፣ ግንባሩ የመልቀቂያ ጥያቄን እንደማያስተናግድ አስታውቋል። ድርጅቱን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡ አባላት አርፈው እንዲቀመጡ ተነግሯቸዋል። ለኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የመልቀቂያ ጥያቄ የሚያቀርቡ አባላት፣ የተቃዋሚ አባላት ሆናችሁዋል በሚል ማስፈራሪያ እየደረሳቸው ነው።
በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አማኑኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ድላችን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ 10 የህወሃትና ኦህዴድ አባላት ፣ ከደሞዛቸው እየተቆረጠ ለድርጅታቸው የሚላከው ገንዘብ እንዲቆም ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም አልተሳካላቸውም። መምህራኑ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ” እናንተ የአረና ፓርቲ አባላት ናችሁ” በሚል እንዲሸማቀቁና እንዲፈሩ የተደረገ ሲሆን፣ ድርጅቱን ለመልቀቅ የሚጠይቅ ማንም ሰው፣ ጥያቄው ተቀባይነት እንደማያገኝ እንደተነገረ ምንጮች ገልጸዋል።
አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላት ግንባሩን የሚቀላቀሉት የስራ፣ የትምህርት እድልና እድገት ለማግኘት መሆኑን ኢህአዴግ በይፋ በሪፖርቱ ያስታወቀ ሲሆን፣ የግንባሩን አላማ ተሸክሞ እስከመጨረሻው የሚጓዝ ወጣት ሃይል ማጣቱንም ገልጿል።
አሁን ባለው አዲስ አመራርና በነባሩ አመራር መካከል የመናበብ ችግር መኖሩም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment