ነኅሴ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በማላዊ እስር ቤቶች ከ300 በላይ ስደተኞች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው አሁንም በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ እስረኞች ውስጥ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ታውቋል። የተፈረደባቸውን የእስር ጊዜ ያጠናቀቁትን ወደ አገራቸው እንደሚላኩ የአገሪቱ ባለስልጣናት ቢያስታውቁም እስካሁን ድረስ በእስር ቤት ውስጥ መቆየታቸውን በመጥቀስ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጊቱን እየኮነኑ ነው።
የስደተኞች ጉዳይ ቃል አቀባይ ጆሴፍ ቻዋ፣ ስደተኞቹ በታንዛኒያ አድርገው በሕገወጥ መንገድ ማላዊ የገቡ ሲሆን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ፍላጎት ነበራቸው ብለዋል። በተለያዩ እስርቤቶች 385 እስረኞች መኖራቸውንና አብዛሃኞቹ የኢትዮጵያ እና የኮንጎ ዜጎች ሲሆኑ ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተጠባበቁ ይገኛሉ ብለዋል።
የእስረኞች መብት ተሟጋች ቪክቶር ሞሃንጎ ድርጊቱን አውግዘው ይህ ሕገወጥ አሰራር ነው መንግስት ሕግን እየጣሰ ነው ንፁሃን የሆኑትን የሕግ ጊዜያቸውን የጨረሱትን አስሮ ማቆየት ሕገወጥነት ነው ይላሉ። “ፍርዳቸውን የጨረሱትን በእንደዚህ ዓይነት እስርቤት ማቆየት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትና ኢሰብዓዊነት ነው” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።
የማላዊ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ምክትል ሃላፊ ዶክተር ኒኮሌት ጃክሰን አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እስረኞች በፕሮቲን እጥረት መጠቃታቸውን ተናግረዋል።
የማላዊ መንግስት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በአውሮፕላን አሳፍሮ ለመላክ ገንዘብ እንደሌለው ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዜጎቹ በየአገሩ እስርቤቶች ሲማቅቁ ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰዱ በተደጋጋሚ ይተቻል። በማላዊ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ የጀመረው ጥረት ስለመኖሩም የተናገረው ነገር የለም።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment