Thursday, September 3, 2015

በአፋር ክልል በልማት ስም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቴምር ዛፍ መጨፍጨፉን ሰመጉ አስታወቀ


ነኅሴ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአፋር ክልል፣ ዞን አንድ፣ አሳይታ ወረዳ ዋሙሌ ቀበሌ፤ በአፋምቦ ወረዳ በአላሳቦሎና ሁመዱይታ ቀበሌ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቴምር ዛፍ በልማት ስም ተጨፍጭፏል። በዚህም በዜጎች ላይ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ሲል ሰመጉ በ138 ኛ መግለጫው አስታውቋል።
የአፋር ክልል ከእንስሳት እርባታ በተጨማሪ ሌላው ትልቅ የገቢ ምንጩ የሆነው የቴምር ዛፍ ሲሆን፣ ድርቅን ተቋቁሞ ከምግብነት ጀምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጠውን ተክል መንግስት ያለ ያለምንም ህጋዊ አግባብነት እንደጨፈጨፈባቸውና በአሳይታ ወረዳ ዋሙሌ ቀበሌ ነዋሪዎች በክልሉ መንግስት መሬታቸውን ለቀው እንዲወጡ ተጠይቀው እምቢ በማለታቸው በፌዴራል ፖሊስ ተገድደው እንዲወጡ መደረጉን ሰመጉ ገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው መሰደድ እንደማይፈልጉ የገለጹ ቢሆንም፣ “የክልሉ መንግሥትና የስኳር ኮርፖሬሽኑ ግን፣ የነዋሪዎቹን ቴምር ቆርጠው በቦታው ላይ የስኳር ፕሮጀክቱን የማስፋፋት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ፣ የአካባቢው ነዋሪ ንብረት ወደሆነው የቴምር እርሻ ሎደርና ግሬደር በማስገባት፣ ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ፣ የካሣ ክፍያም ሳይፈጽሙ፣ የፌዴራል ፖሊስ በማምጣት በኃይል በርካታ የቴምር ዛፎች እንዲጨፈጨፉና ወደ ቴምር እርሻቸው ይፈስ የነበረውን የአዋሽ ወንዝ በመገደብ የውሃውን የመፍሰሻ አቅጣጫ እንደቀየሩባቸው አስታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የተፈጸመባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በክልሉና በፌዴራል ደረጃ ለሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት አካላት ያመለከቱ ቢሆንም እስካሁን ድረስ መፍትሄ አላገኙም።
የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የጥናት ቡድን ሪፖርት መሰረትም 127 ከፊል አርብቶ አደርና አርሶ አደሮች በድምሩ 8 ሺህ 527 የቴምር ዛፍ ወይም በገንዘብ 596 ሚሊዮን 890 ሺህ ብር ንብረት ወድሟል።
የጥናት ቡድኑ የጥናት ጊዜውን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ ደግሞ በአፋምቦ ወረዳ በአለሳቦሎና ሁሙዱይታ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 30 ሰዎች 7 ሺህ 950 የቴምር ዛፍ መጨፍጨፉን አስታውቀዋል። በሁለቱ ወረዳዎችም በድምሩ 16 ሺህ 477 የቴምር ዛፎች ከህግ ውጭ እንደተጨፈጨፉና በገንዘብ ሲለካም አንድ ቢሊዮን 153 ሚሊዮን 390 ሺህ ብር እንደሚሆን ገልጿል።
ሰመጉ “መንግሥት ተለዋጭ ቦታ እና ተመጣጣኝ የቁሳቁስና የሞራል ካሣ የሚከፈልበትን መንገድ እንዲያመቻች፣ ከፊል አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች የመሬት ዋስትናቸው ተረጋግጦ ያለሥጋት የሚሠሩበትና የሚኖሩበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ በተለይም ከሕግ ውጭ የቴምር ዛፋቸው ለወደመባቸው የአፋር ከፊል አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደሮች ተገቢው ካሣ እንዲከፈል፣ የቴምር ዛፎቻቸውን እንዲጨፈጨፉ ባደረጉ አመራሮች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና ለወደፊቱም ለዜጎች የመሬት፣ የንብረትና ሠርቶ የመኖር ዋስትና እንዲሰጣቸው አጥብቆ ይጠይቃል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment