Friday, September 18, 2015

አይካ አዲስ ከሁለት ባንኮች የተበደረው 3.3 ቢሊዮን ብር መክፈል አልቻለም ተባለ።


ኢሳት ዜና (መስከረም 7, 2008)
የኢትዮጵያን ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግራል የተባለውና በቱርክ ባለሃብቶች የተቋቋመው አይካ አዲስ የተባለው የጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተበደረውን ሶስት ቢሊዮን ብር መክልፈል እንደተሳነው ታወቀ። የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት ኩባንያው ብድር መክፈሉን በማቋረጡ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማኔጅመት በኩል ከፍተኛ መደናገጥ መፍጠሩ ተመልክቷል።
የሃገሪቱን ኢንዱስትሪ ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል የተባለውና በኦሮሚያ ክልል አለምገና ወረዳ የተቋቋመው አይካ አዲስ የተባለው ይኸው የቱርክ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ከስምንት አመት በፊት ወደኢትዮጵያ የገባ ሲሆን፣ በ 10ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ስራ መጀመሩን ሲግለፅ ቆይቷል።
የቀድሞ ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የልማታዊ መንግስት ኢንዱስትሪ ፖሊሲን ውጤታማነት ያሳያል በሚል መሬት በርካሽ የሊዝ ዋጋ በማቅረብ እንዲሁም ከፍተኛ ብድር በመፍቀድ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የተደረገው ይኸው የቱርክ ኩባንያ ለብድር መያዣነት ያስመዘገባቸው አሮጌ ማሽኖች በአዲስ ማሽን ሂሳብ ተሰልተው ብድሩ እንደተፈቀደ የልማት ባንክ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የልማት ባንክ ለአሮጌ ማሽኖች በአዳዲስ ማሽኖች ሂሳብ ብድሩ እንዲፈቀድ ግፊት ያደረጉ የወቅቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ ግርማ ብሩ መሆናቸው ተመልክቷል።
በብድሩ ሂደት ውስጥ ተዋናይ የሆኑትና ይኸው የቱርክ ኩባንያ በሚያቀርብላቸው ግብዣ በተደጋጋሚ ወደኢስታንቡል የተጓዙት የልማት ባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ከሟቹ መለስ ዜናዊና ከአቶ ግርማ ብሩ ጋር በመሆኑ በባንክ ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ መሆናቸውም እየተገለጸ ይገኛል። ለዚህ የቱርክ ባለሃብት በቅድሚያ ከተፈቀደው ብድር በተጨማሪ ለስራ ማስኬጃ ወይንም ዎርኪንግ ካፒታል እየተባለ የሚለቀቀው ገንዘብ ለብድሩ መናር አስተዋጽዖ እንዳደረገ የባንክ ምንጮች ገልጸዋል።
ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድርን የተሸከመውና ብድር መከፈሉን በማቆሙ በልማት ባንክ አካባቢ መደናገጥን ያስከተለው የቱርክ አይካ አዲስ ኩባንያ የሚያመርታቸው ምርቶች በቀጥታ ለአለም ገበያ ከማቅረብ ይልቅ ቱርክ ለሚገኘው አይካ ኢስታንቡል ሲያቀርብ ቆይቷል። ለአይካ ኢስታንቡል በዝቅተና ዋጋ የሚቀርበውን ምርት አይካ ኢስታንቡል በከፍተኛ ዋጋ ለአውሮፓ ገበያ በመሸጥ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ሲያሳጣት መቆየቱ ተመልክቷል።
አይካ አዲስ ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ለእህት ኩባንያ በማቅረብ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ከማሳጣት ባሻገር በከፍተኛ ደሞዝ የሚያሰራቸው ሰራተኞች ደሞዛቸው ወደቱርክ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ሲያሸሹ መቆየታቸው ተመልክቷል። አይካ አዲስ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለተበደረው ሶስት ቢሊዮን ብር በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 300 ሚሊዮን ብር መበደሩም ታውቋል።
አይካ አዲስ ወደኢትዮጵያ ሲገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን የሚያገለግሉት አቶ ግርማ ብሩ በአይካ አዲስ ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ እንዳላቸው የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ ግርማ ብሩ ከዚህም በተጨማሪ አዳማ ቴክስታይልን ከቀደም ጓደኞቻቸው ጋር በጋራ የከፈቱት መሆኑን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች፣ አይካ አዲስን በስራ አስኪያጅነት የሚመሩት የኦህዴድ አባል አቶ አማረ ተ/ማሪያም በ አቶ ግርማ አማካኘነት ቦታውን እንዳገኙ ይገልጻሉ።

source:esat

No comments:

Post a Comment