Friday, August 28, 2015

በቃሉ ወረዳ አንድ ሰው በታጣቂዎች ተገደለ


ነኅሴ ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ወሎ ዞን በቃሉ ወራዳ ጅጋ ቀበሌ ላይ ጀማል ሙሼ የተባለ የ22 ዓመት ወጣት፣ ሃምሌ 27 ቀን 2007 ዓም በሚሊሺያዎች ተገድሏል። ወጣት ጀማል ሙሼ በዩ፣ ሰይድ ሙሄ ጌሮና እንድሪስ ኡመር በተባሉ ታጣቂዎች ተገድሎ ከአካባቢው 24 ኪሎሜትር ርቆ ሊቀበር ሲል መረጃ የደረሳቸው ዘመዶቹ ቦታው ድረስ በመሄድ አስከሬኑን ወስደዋል።
ወጣቱ ግንባሩ አካባቢ በጥይት የተመታ ሲሆን፣ ሁለቱ ኩላሊቶቹም ወጥተዋል። ታጣቂዎቹ ወጣቱን ብረታብረት እንሸጥልሃለንና 40 ሺ ብር ይዘህ ና ብለው እንዳስመጡት፣ ነገር ግን ቦታው ደርሶ በዋጋ ለመስማማት አለመቻሉን ዘመዶቹ ለኢሳት ተናግረዋል። ሌሎች ጉደኞቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ታጣቂዎቹ ጀማልን መንገድ ላይ በማስቆም በጥይት ገድለው ገንዘቡንና የእጅ ስልኩን ይዘው በመሄድ ለመቅበር ሲሞክሩ ዘመዶቹ ደርሰዋል።
ታጣቂዎቹ እንዲያዙ ዘመዶቹ ለመንግስት አቤት ቢሉም የሚሰማቸው ማጣታቸውንና ገዳዮቹ አሁንም ድረስ ስራቸውን እየሰሩ መሆኑን አለም ይወቅልን ሲሉ ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን ባለስልጣናት ለማናገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment