Friday, August 28, 2015

ለምርጫ ተብለው የተቀየሩ ትራንስፎርመሮች ተቃጥለው በርካታ ሰዎች ተጎዶ


ነኅሴ ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ኦሞ ዞን ከምርጫ 2007 ጋር በተያያዘ የተቀየሩ በርካታ ትራንስፎርመሮች በአንድ ቀንና ሰአት በመቃጠላቸው ሰዎች ተጎድተዋል።
በነ ጸማይ ወረዳ ቃቆ ቀበሌ ትራንስፎርመሩ ሲቃጠል አንድ ነርስ ወዲያውኑ ህይወቱን ሲያጣ፣ 11 ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል።
በዚሁ ወረዳ ቀይ አፈር ከተማ ላይ ተጨማሪ 3 ትራንስፎርመሮች ሲፈነዱ፣ በሀመር ወረዳ በዲመካ ከተማ አንድ ትራንስፎርም፣ በጂንካ ከተማም እንዲሁ ሌላ ትራንስፎርመር ተቃጥሎአል።ሁሉም ትራንስፎርመሮች በተመሳሳይ ሰአት ነው የተቃጠሉት። ነዋሪዎች ፍንዳታው ከጥራት ችግር ጋር በተያያዘ የተከሰተ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁን ለተጎጂዎች እርዳታ አለመድረሱንም ተናግረዋል።
የተቃጠሉት ትራንስፎርመሮች በቅርቡ ከቻይና የገቡት ይሁኑ ወይም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ የገጣጠማቸውና ለመብራት ሃይል ያስረከባቸው በውል አልታወቀም። ይሁን እንጅ ሁሉም ትራንስፎርመሮች ምርጫ ሊካሄድ አንድ ወር ሲቀረው መቀየራቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የዞኑን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment