ሐምሌ ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከማእከላዊ እስታትስቲክስ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በተለይ በአዲስ አበባ እና በኦሮምያ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የምግብ ኢንዴክስ 13 ነጥብ 9 በመቶ ሲጨምር፣ በአዲስ አበባ 26 በመቶ፣ አፋር 16 በመቶ፣ አማራ 6.7 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 13.9 በመቶ፣ ኦሮምያ 21.2 በመተ እንዲሁም በትግራይ 5.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ከፍተኛ ጭማሪ የታየባቸው የምግብ ክፍሎች እህል፣ ስጋ፣ ወተትና አይብ፣ እንቁላል፣ ዘይትና ቅባቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ በተለይም ምስር፣ እንዲሁም ቅመማቅመም በተለይ ያልተፈጨ በርበሬ ናቸው።
ዳቦና እህል 1.8 በመቶ ጭማሪ ሲያሳዪ፣ ስጋ 10.6 በመቶ፣ ወተት፣ የወተት ዘርና እንቁላል 19.6 በመቶ ፣ ዘይትና ቅባቶች 18.4 በመቶ እንዲሁም አትክልት 23 በመቶ፣ ፍራፍሬ ደግሞ 12 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የሌሎች ሸቀጦች ዋጋም እንደዚሁ ጭማሪ አሳይቷል።
እንደማእከላዊ እስታትስቲክስ መረጃ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 11.9 በመቶ ደርሷል። ገዢው ፓርቲ የዋጋ ግሽበቱ በአንድ አሀዝ እንዲቀንስ አድርጌዋለሁ በማለት በተደጋጋሚ ቢናገርም፣ ግሽበቱ ከወር ወር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። በመላ አገሪቱ የሚታየው የዝናብ እጥረት በዚህ ከቀጠለ፣ የዋጋ ንረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment