Thursday, September 10, 2015

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በቃሊቲ እስር ቤት በፍትሃዊ መንግድ ተይዘዋል ብለው እንደማያምኑ አንድ የእንግሊዝ ባለስልጣን ተናገሩ


ጷግሜን ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቫይስ ኒውስ የተባለው ድረገጽ የግንቦት7 ዋና ጸሃፊ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ወቅታዊ ሁኔታ ይዞ በወጣው ዘገባ እንደገለጸው፣ የእንግሊዝ ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ታስረው ከነበሩበት ስውር ቦታ ወደ ቃሊቲ መዛወራቸው በጎ ነገር ቢሆንም፣ በቃሊቲ በጥሩ ሁኔታ ተይዘዋል ብለው አያምኑም።
የእንግሊዝ የውጭና የጋራ ብልጽግና አገራት ቃል አቀባይ ” ኢትዮጵያና ዩናይትድ ኪንግደም የቆየና ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው አገራት በመሆኑ ፣ ጉዳዩ ይህን ግንኙነት እንዲያበላሽ አንፈልግም” ብለዋል።
ይሁን እንጅ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጉዳዩን ለ17ኛ ጊዜ ለኢህአዴግ ባለስልጣናት አቅርበዋል። ቃል አቀባዩ፣ አቶ አንዳርጋቸው እንግሊዝ ባሉ ቤተሰቦቻቸው በተደጋጋሚ እንዲጎበኙ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያን እስር ቤት “ጉላግ” በሚል በቀድሞው የራሽያ እስር ቤት ስም እንደሚጠራው የገለጸው ዘገባው፣ አቶ አንዳርጋቸውም በዚህ እስር ቤት በስቃይ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
የሪፕሪቭ ሃላፊ ማያ ፎ እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸው ተፈተው ወደ እንግሊዝ እንዲመለሱ ጥረት አለማድረጓ የእንግሊዝንና ዝና የሚጎዳና ፍትህን የሚደፈጥጥ ነው ብለዋል። የእንግሊዝ መንግስት አቋሙን ቀይሮ አቶ አንዳርጋቸው በአስቸኳይ ተፈተው ወደ እንግሊዝ የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ዳይሬክተሩዋ ጠይቀዋል።
የአቶ አንዳርጋቸው የትዳር ጓደኛ ወ/ሮ የምስራች ሃይለማርያምም የእንግሊዝ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምሃ ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ወ/ሮ የምስራች ፣ ቶቢያስ ኤልውድ የተባሉ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይና የጋራ ብልጽግና አገራት ሚኒስትር የደቡብ ሱዳንን የሰላም ድርድር ለማየት ወደ አዲስ አበባ ባመሩበት ወቅት፣ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ ባለማንሳታቸው ማዘናቸውን ለጋዜጣው ተናግረዋል። ባለስልጣኑ የኢትዮጵያን ባለስልጣናት ለማግኘት እድሉን አላገኘሁም በማለት ለወ/ሮ የምስራች መጻፉም በዘገባው ተጠቅሷል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment