Monday, July 20, 2015

አመት በዓሉን ከህወሃትና ከኦህዴድ በአል ባላነሰ ለማክበር ከፍተኛ ዝግጅት ጀመረ


ሐምሌ ፲፫ (አስራሶስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህውሃት 40ኛ ዓመቱንና ኦህዴድ 25ተኛ አመቱን ባከበሩበት ማግስት፣ ብአዴንም 35ተኛ አመቱን ከሁለቱ ድርጅቶች ባላነሰ ለማክበር በብዙ መቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ መመደቡን የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ባደረጉት ዝግ ስብሰባ መነጋገራቸውን ምንጮች ጠቅሰዋል።
ከሀምሌ ወር, 2007 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ጋዜጠኛ የብአዴንን ታሪክ ለማወቅ የሚረዱትን መጽሃፍት በማሰባሰብ እንዲያነብና የተለያዩ ዶክሜንታሪ፣የጉዞ ማስታወሻዎችንና የመሳሰሉትን መሳጭ ፕሮግራሞች በሁሉም ሚዲየሞች በማዘጋጀት ብአዴን በኢትዮጵያ የሰራውን ተጋድሎ በጉልህ ለማሳየት መዘጋጀት እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፡፡
ጋዜጠኞች በተሰጡት የስራ መመሪያ የተመረጡ ጋዜጠኞች ትግል የተካሄደባቸውን ቦታዎች በአካል በመጎብኘት የተለያዩ ከአሁን በፊት ያልተነገሩ ታሪኮችን በመስራት ህብረተሰቡን እንዲያስደምሙ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
በመስከረም ወር ውስጥ ከመላው ኢትዮጵያ የሚሰባሰቡ የገዢው መንግስት ደጋፊ የሆኑ የግልና የመንግስት ጋዜጠኞችን ሙሉ ወጪ በመቻል የትግል ቦታዎችን እንዲጎበኙ ለማድረግ እና ብአዴን በመላው ሃገሪቱ ያለውን ተቀባይነት ለመጨመር የሚያስችል ዝግጅት በማዘጋጀት ልዩ ልዩ ዘገባዎችን በመስራት ውለታ እንዲሰሩ ለማግባባት የሚችሉ የብአዴን አባላትም ልዩ ተልዕኮ በመያዝ እንደሚሰሩ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ለዝግጅቱ የሚያስፈልገው ወጪ ከብአዴን ማእከላዊ ጽህፈት ቤት በዋናነት ሲሆን ከነጋዴው ማህበረሰብ፣ከመንግስት ሰራተኛው፣ ከድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመሰብሰብ እንዲያስችል ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች በየደረጃው ተዋቅረዋል፡፡የገዢው መንግስት ካድሬዎች በየአንዳንዱ ዜጋ ድርጅትና መኖሪያ ቤት በመዘዋወር ህብረተሰቡን አስገድደው ገንዘብ እንዲያስከፍሉ መመሪያ ወርዶላቸዋል።
ብአዴን እመራዋለሁ የሚለው ክልል ህዝብ በአብዛኛው በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ይሰቃያል። ሞጣ፣ቻግኒ፣ባቲ፤ከሚሴ፤ወልዲያ፣ጎንደርና የመሳሰሉት ከተሞች ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር አለ። በርካታ የሆስፒታል ግንባታዎች ያልተጠናቀቁበት ፣ አብዛኛው ህዝብ በቂ ህክምና ያላገኙበት፣የኑሮ ውድነት ጣራ በደረሰበት ጊዜ የህዝቡን ችግር ከመፍታት ይልቅ ለሌላ ተጨማሪ ዓመታት በችግር ለማቆየት የሚደረገውን ሽር ጉድ ህብረተሰቡ ሊቃወመው እንደሚገባ የመረጃ ምንጮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment