Wednesday, July 1, 2015

በድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት ላይ የሚሰጠው ፍርድ ለነገ ተራዘመ


ሰኔ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት በድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት ላይ ሊሰጥ የነበረውን ፍርድ ያራዘመ ሲሆን፣ ፍርዱ ለምን እንደተራዘመ ግን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
በአቶ አቡበከር አህመድ መዝገብ 18 የኮሚቴው አባላት በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው የመጨረሻውን ፍርድ ለመስማት ችሎት የተገኙ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ የክሱን ጭብጥና የምስክሮችን ቃል በማጠቃለያ መልክ ካቀረበ በሁዋላ ውሳኔውን ሳይጨርስ ለነገ አስተላልፎታል።
አቃቢ ህግ 102 ምስክሮችን ያቀረበ ሲሆን፣ተከሳሾች ደግሞ 220 የመከላከያ ምስክሮችን አቅርበዋል። አብዛኛው ሰው ፍርድ ቤቱ የሙስሊሙን መሪዎች በነጻ ያሰናብታቸዋል ብሎ አያስብም። አንድ አስተያየት ሰጪ ” ምን ያክል አመት ተፈረደባቸው የሚለውን ለመስማት እንጅ፣ ቅጣቱማ አስቀድሞ የታወቀ ነው” ብሎአል።
በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ወደ ሲኤም ሲ በማምራት የፍርድ ሂደቱን ለመከታታል ሲጠባባቁ ነበር። የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው በብዛት ታይቷል። አካባቢውን በማጣር እግረኞችና ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ ሲከላከል መታየቱን ዘጋቢያችን ገልጿል።
ከዚሁ የፍርድ ቤት ዜና ሳንወጣ የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በዘመነ ካሴ መዝገብ በሽብርተኝነት ለተከሰሱት ምስክር ሆነው መቅረብ የለባቸውም ሲል መቃወሚያ አቅርቧል። ተከሳሾቹ ‹‹አንዳርጋቸው ፅጌ አሰልጥኗችኋል ከተባለ አቶ አንዳርጋቸው ሀገር ውስጥ ባለ እስር ቤት ስለሚገኙ እሳቸውን በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡልኝ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጥልን›› ማለታቸው ይታወቃል፡፡
ዳኛው ‹‹ሌላ መከላከያ ምስክር ብትጠሩ ምን አለበት? አቶ አንዳርጋቸውን መጥራታችሁ ምን ይፈይድላችኋል?›› ቢሉም፣ ተከሳሾች በአቋማቸው በመጽናታቸው ፣ አቃቢ ህግ ‹‹በህይወት መኖሩ፣ አለመኖሩ የማይታወቅ ሰው በመከላከያ ምስክርነት ይቅረብ መባሉ አግባብ አይደለም፡፡›› ሲል ተቃውሞ አሰምቷል።
ተከሳሾቹ ‹‹በዶክመንተሪ ሀገር ውስጥ የሚገኝ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ለመረዳት ችለናል፡፡ በመሆኑም እሳቸውን በተከላካይ ምስክርነት ለማቅረብ የሚከብድ ነገር አይኖርም፡፡ እሱ ነው አስልጥኖ ያሰማራችሁ በሚል የተከሰስን በመሆኑ ለእኛ ዋነኛው የመከላከያ ምስክራችን አቶ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡›› በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ሰኔ 25/2007 ዓ.ም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መከላከያ ምስክር መሆን እንደሚችሉና እንደማይችሉ ለመወሰን ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡
በልደታ 19ኛው ምድብ ችሎት አቶ አንዳርጋቸው ምስክር መሆን እንደማይችሉ ቅሬታ ያቀረበው የፌደራል አቃቤ ህግ፣ ለፍርድ ቤቱ በጸሁፍ ቅሬታ ማቅረብ የነበረበት ቢሆንም፣ በመብራት መጥፋትና በፀሃፊ ችግር ምክንያት ቅሬታውን ማቅረብ አልቻልኩም ብሏል፡፡ በመሆኑም ቅሬታውን በጽሑፍ ለማቅረብ ለሐምሌ 6/2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
አቃቢ ህግ አቶ አንዳርጋቸው በህይወት መኖሩና አለመኖሩ ሳይታወቅ በማለት የሰጠው መልስ ችለቶዩን የታደሙ ሰዎችን አስገርሟል። አቶ አንዳርጋቸው ባለፈው ሚያዚያ ወር በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ተጎብኝተው ነበር።

No comments:

Post a Comment