Tuesday, June 30, 2015

ፍርድ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በምስክርነት ይቅረቡ አይቅረቡ በሚለው ላይ ብይን ይሰጣል


ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ወንጀል አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ለመኢአድ አባላት መከላከያ ምስክር መሆን መቻል አለመቻላቸው ላይ ነገ ሰኔ 24፣ 2007 ዓ.ም ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ በግንቦት ሰባት አባልነት የተከሰሱት 5 የመኢአድ አባላት ‹‹በአንዳርጋቸው ፅጌ አሰልጣኝነት የሽብር ተግባር ለመፈፀም ተንቀሳቅሳችኋል፡፡›› በሚል ክስ የቀረበባቸው በመሆኑ እነሱም ‹‹አንዳርጋቸው ፅጌ የሚባል ሰው አናውቅም፡፡ አሰልጥኛቸዋለሁ ካለ እሱ ቀርቦ ያስረዳልን፡፡›› ብለው በመከላከያ ምስክርነት ቀርበው እንዲመሰክሩ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ዳኛው በበኩላቸው ‹‹የት እንደሚገኙ የማይታወቁ ሰውን በመከላከያ ምስክርነት ማቅረብ ይከብዳል›› ያሉ ሲሆን፣ ተከሳሾቹም ‹‹በኢቲቪ ዶክመንተሪ ላይ እንዳየነው አቶ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት እንደሚገኙ ተረድተናል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ማረሚያ ቤት ውስጥ ያለን ሰው በምስክርነት ለማቅረብ ስለማይከብድ በመከላከያነት ሊቀርቡልን ይገባል›› ሲሉ ተከራክረዋል።
ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ደጋግመው መከራከራቸውን ተከትሎ ዳኛው ‹‹ሌላ መከላከያ ምስክር ብትጠሩ ምን አለበት? አቶ አንዳርጋቸውን መጥራታችሁ ምን ይፈይድላችኋል?›› በሚል ለማባበል ቢሞክሩም፣ ተከሳሾቹ በአቋማቸው ፀንተዋል።
ይህንን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ለተከሳሾች በምስክርነት መቅረብ እንደሚችሉና እንደማይችሉ ነገ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment