ሚያዝያ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ” የኢንዱስትሪውን ልማት በተሳለጠ መንገድ ይዘን በመጓዝ የአምስት አመቱን ዕቅድ ለማጠናቀቅ በስኬት ጎዳና ላይ ነኝ ” በሚል የገዢው መንግስት ቢናገርም፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በርካታ ችግር
እየገጠማቸው መሆኑን ተናገሩ፡፡
ሰሞኑን በተካሄደው የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ከከፍተኛ ባለሃብቶች ጋር ባደረጉት የውይይት መድረክ ላይ ፣ ባለሃብቶች እንደገለጹት በባለስልጣናት ላይ የሚታየው የፍርሃት መንፈስ ስራዎች በታሰበላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ አድርጓል፡፡
ችግሮች በየደረጃው እንዲፈቱ በማሰብ የገዥው መንግስት የቀየሰውን የአሰራር ፖሊሲ እንዲያስፈጽሙ የተቀመጡት አመራሮች በራሳቸው ተማምነው ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ ሌሎችን የመጠበቅ እና ውሳኔ በቶሎ አለመስጠት በዘርፉ በመታየቱ ተገቢውን አገልግሎት
ማግኘት አለመቻላቸውን ባለሃብቶቹ ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢ ባለሃብቶች በየጊዜው የሚደረጉ የአመራሮች ከቦታ በመነሳት በየጊዜው መቀያየር ከፍተኛ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡የስርአቱን ብልሹነት በሚያሳይ መልኩ በሙስናና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ስድስት ወር ሳይሞላቸው የሚነሱ
አመራሮች ባሉበት ቢሮ ከውጭ ሃገር በመምጣት መዋእለ ነዋያቸውን የሚፈሱ የውጭ ሃገር ዜጎች ሃገራቸው ቆይተው በሚመጡ ጊዜ አመራሮች ተቀያይረው ማግኘታቸው ጉዳያቸውን እንደ አዲስ ለማስረዳት በየጊዜው መቸገራቸው አንዱ ሲሆን አዲስ የሚመደቡት
አመራሮችም ጉዳዩን እናጥናው በማለት ተጨማሪ ጊዜ መውሰዳቸው ትልቅ ድካም ከማስከተሉም በላይ የውጭ ሃገር ዜጎች በገዥው መንግስት አሰራር ላይ ሁልጊዜ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ክስተት መፈጠሩን ባለሃብቶቹ ተናግረዋል፡፡
‹‹ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ችግር በመሆን ላይ ያለው የምርት ጥራት ነው ፡፡ባለሃብቶች በክልሉ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ቢያመርቱም፤ጎን ለጎን ጥራታቸውን ያልጠበቁ ተመሳሳይ ምርቶችን በማስገባትና በማቅረብ ኢንቨስተሩን ለኪሳራ የሚዳርግ አሰራር
በጉልህ ይታያል፡፡ ›› በማለት የሚናገሩት ሌላው ቅሬታ አቅራቢ በተለይ ጉዳዩን እንዲቆጣጠር የተመደበው የደረጃ መዳቢዎች ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ሲሰራ የሚታየው ማህተም ማዘጋጀትና የዕውቅና ደብዳቤ መስጠት ብቻ መሆኑ ገልጸዋል፡፡ባለስልጣን መስሪያቤቱ
አሰራሩ አግባብ እንዳልሆነ ጥራት እና ቁጥጥር ላይ ሳያተኩር በግዴለሽነት እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሆቴል ንግድ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለአሰራራቸው ከፍተኛ ማነቆ በመሆን ያስቸገራቸውን አሰራር ሲገልጹ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች ህጋዊ የገቢ አሰባሰብ በመዘርጋት በዘመናዊ መልኩ እየሰሩ ቢሆንም ፤የገዢወው መንግስት ሹመኞች የሚጠይቋቸው የግብር መጠን
በግምት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ስራቸውን አደጋ ላይ መጣሉን ተናግረዋል፡፡በጎንደር የጃንተከል ሆቴል ባለቤት አቶ ተመስገን ሰጥአድርገው ሲናገሩ የሽያጭ ማሽን ተገጥሞ በሚሰራባቸው ታላላቅ ሆቴሎች ከደንበኞች የሚሰበሰበውን ገቢ በአግባቡ ቢይዙም መንግስት
ባለሃብቶችን ባለማመን በግምት በሚጥለው ግብር በመማረር ስራውን ለመተው ጫፍ መድረሳቸውን በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
በምእራብ አርማጮሆና መተማ አካባቢ በጥጥ ምርት ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ባቀረቡት ቅሬታ በአካባቢው የሚመረተው ምርት ጥራቱን የጠበቀ ሆኖ እያለ በዘርፉ የተሰማሩ የውጭ ሃገር ባለሃብቶች በሃገራችን ለተከሉት ፋብሪካ ምርታቸውን ከውጭ ለማስገባት የሚያደርጉትን የተንኮል አሰራር የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚያግዙዋቸው ሲናገሩ፤
የጥጥ ምርት በኢትዮጵያ በሚደርስበት ጊዜ በመጋዝናቸው ምርት እንዲኖር ፣በሃገር ውስጥ የነበረው ምርት ከባከነና በርካሽ ከተሸጠ በኋላ ‘ምርት እንፈልጋለን ‘ በማለት ከውጭ ሃገር የራሳቸውን ምርት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገቡ በማድረግ ሀገሪቱ የምታገኘውን
ጥቅም በማባከን ላይ መሆናቸውን በምሬት ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡ያመረቱትን ከፍተኛ ምርት በርካሽ እንዲሸጡ የተገደዱት ባለሃብቶች እንባ አውጥተው በየስብሰባው የሚያለቅሱበት ጊዜ ላይ የደረሱ ቢሆንም ከፍተኛ ባለስልጣናት ምንም አይነት እርምጃ ባለመውሰዳቸው የባለሃብቶች ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በሰሊጥ ምርት የጥራት ደረጃ ማውጣትና ማወዳደር የሚገባው የምርት ገበያ ድርጅት ባለሃብቶች ያለሙያቸው ለምርታቸውን ደረጃ በማውጣት ምርታቸውን እንዲያቀርቡ በማስገደድ ያለአግባብ በመቅጣት እየበደለን ነው፡፡
” የሚሉት ባለሃብቶች፤ይህንንም ለከፍተኛ አመራሮች አቤት ቢሉም ቅጣቱን እንዳጸደቁባቸው ተናግረዋል፡፡መፍትሄ በማጣታቸውም ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደተገደዱ ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡በሰሊጥ ምርት ለተሰማሩ ባለሃብቶችም ሆነ ለዘርፉ
የገዥው መንግስት ምንም ዓይነት ማበረታቻ ባለማድረጉ ዘርፉ በጥቂት ሰዎች እጅ መያዙን ተናግረዋል፡፡
‹‹ጉዳይ ለማስፈጸም በክልል ደረጃም ብቃት ያለው ባለስልጣን የለም፡፡›› የሚሉት ባለ ሃብቶች ‘አንድ ደብዳቤ ጽፎ ይህ ይፈጸም! ‘ለማለት የሚችል አመራር በክልል ደረጃ አለመኖሩ በብድር አገልግሎት ለመጠቀም እንዳይችሉ ማድረጉን ገልጸው፤የውሳኔ አሰጣጥ ከጊዜ
ወደ ጊዜ እየባሰበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለሃብቶቹ በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ የቢሮክራሲ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸው ፤ስርዓቱ የተለመደ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የሚናገረውን እውነታ በተግባር በማዋል ያለበትን ችግር ባለማስተካከሉ በዘርፉ ለመሰማራት አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
Source:http://ethsat.com
No comments:
Post a Comment