Friday, May 29, 2015

በሃመር ወረዳ ከፍተኛ እልቂት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ


ግንቦት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በሃመር ወረዳ በዲመካ ከተማ እና አካባቢዋ የሚኖሩ አርብቶአደሮች ” እኛ ድምጽ ሳንሰጥ” እንዴት ኢህአዴግ አሸነፈ ይባላል በሚል ካለፈው
ሰኞ ጀምሮ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ሲታኮሱ መቆየታቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አንድ ሻለቃ ጦር እና የፌደራል አባላት ወደ አካባቢው በመንቀሳቀስ በወሰዱት እርምጃ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር በመቶዎች ያደርሱታል።
የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት አርብቶ አደሮች 5 የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ያቆሰሉ ሲሆን፣ ቁስለኞችም በሄሊኮፕተር ተወስደዋል። በአርብቶ አደሮች በኩል የተገደሉትን ሰዎች በትክክል ለማወቅ እንደማይቻል የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች
አስከሬን በየቦታው ወደቆ እንደሚታይ እየገለጹ ነው።
በዞኑ የሚኖሩ አንድ ታዋቂ ግለሰብ እንደተናገሩት ደግሞ ትናንት አርብቶ አደሮች ዲመካን በሌሊት ለመያዝ ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት የመንግስት ወታደሮች ከባድ መሳሪያ በመተኮስ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች
እንደተገደሉ መረጃው እንደደረሳቸው ገልጸዋል። በሶስት ፒካፕ መኪኖች የተጫኑ ቁስለኛ ወታደሮች ጂንካ ሆስፒታል መግባታቸውንም አክለው ገልጸዋል። ሁለቱም ወገኖች ለወራት የጦርነት ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ፣
የችግሩ ምንጭ ከምርጫ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመሬት ጋር የተያያዘ መሆኑም ይገልጻሉ።
ሌላ የአካባቢው ነዋሪም እንዲሁ በተወሰደው እርምጃ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል ። የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በርጤ ዢላ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢሳት በሁለቱም ወገን የሞቱትን ሰዎች ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት ያደረገው መኩራ አልተሳካለትም።
ኢሳት ከሶስት ቀናት በፊት አርብቶአደሮች 3 ፖሊሶች ማቁሳለቸውን ዘግቦ የነበረ ሲሆን፣ ሆቴል ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሁንም ድረስ እንደተዘጉ ነው።
ለወራት የዘለቀው ውጥረት ምርጫውን ሰበብ አድርጎ መጀመሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ሰመጉ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው ልዩ መግለጫ ከጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተ ግጭት 7 ሰዎች መገደላቸውንና 9 ሰዎች መቁሳለቸውን
በጥናት አረጋግጦ ይፋ አድርጓል።
ሰመጉ በሪፖርቱ ህዳር 7 ቀን 2007 ዓም አቶ ዑልዴ ሃይሳ በሐመር ወረዳ ሸንቆ ወልፎ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የነበረ አርብቶ አደር ሲሆን፣ በድንገት በተነሣ አለመግባባት ምክንያት ባሌ ኢልዴ በተባለ የፖሊስ አባል ኩላሊቱ ላይ በከባድ
እርግጫ በመመታቱ የአቶ ዑልዴ ህይወት በእለቱ ህዳር 7 አልፏል። የሐመር ብሔረሰብ አባላት አቶ ዑልዴን የገደለው የፖሊስ አባል ሕግ ፊት ቀርቦ ባለመጠየቁ ከፍተኛ ቅሬታ አድሮባቸውና የመበደል ስሜት ውስጥ ገብተው እንደነበር
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ አስታውቃል።
ማንጐ ተብሎ በሚጠራው ፓርክ ጎሽ የገደሉ የሐመር ብሔረሰብ አባላትን ለመያዝ ከደቡብ ኦሞ ዞን ፓሊስና ልዩ ኃይል የተውጣጡ አባላት ጥር 7/ 2007 ሥፍራው ሲደርሱ ለሽምግልና የተቀመጡ የአካባቢውን ሽማግሌዎች ጎሽ ገዳዮችን እንዲያወጡ በጠየቁዋቸው ጊዜ “በቅርቡ የተፈጸመውን የአቶ ዑልዴን ግድያ ሳታጣሩና ገዳዩን ይዛችሁ ለፍርድ ሳታቀርቡ፣ ከረዥም ጊዜ በፊት ጎሽ ገደለ የምትሉትን ሰው ለመያዝ እንዴት መጣችሁ?” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ይሁን እንጅ ” የፖሊስና ልዩ ኃይል አባላቱ በወቅቱ የተሰጣቸው ግዳጅ ጎሽ የገደለን ሰው መያዝ ብቻ መሆኑን በመግለጽ፣ ፖሊስ የተላክሁበትን ግዳጅ እፈጽማለሁ በማለቱ የሐመር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰቡ አባላት ደግሞ የአቶ ዑልዴ ሃይሳን ገዳይ ሳትይዙ
የጎሽ ገዳይ ልትይዙ አትችሉም በሚል አለመግባባት መፈጠሩን ሪፖርቱ ያስረዳል።
አለመግባባቱ እየተካረረ ሄዶ በዚያው ቀን ጥር 7 ቀን 2007 በሐመር ማኅበረሰብ አባላትና በፖሊሶች መካከል ተኩስ ተጀምሮ፣ ሰፋ ወዳለ ግጭት ያመራ ሲሆን በግጭቱም 7 ሰዎች ሲሞቱ 9 ሰዎች መቁሰላቸውን ማረጋገጡን የሰመጉ 134ኛ
ሪፖርት ያስረዳል።
ሰመጉ ባወጣው የሟቾች ስም ዝርዝር አብዛኞቹ የሞቱትና የቆሰሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስና የልዩ ሃይል አባላት ናቸው።
ሰመጉ በግጭቱ ተሳታፊ ከነበሩት የሐመር ብሔረሰብ አባላት በኩል ምን ያህል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰ ለማወቅ አለመቻሉን በመግለጫው አስታውቋል።
በሃመር ወረዳ ከ45 ሺ በላይ ነዋሪዎች ይኖራሉ። ዲመካ የወረዳው ዋና ከተማ ናት።

No comments:

Post a Comment