Tuesday, May 12, 2015

የሰሞኑ አጀንዳ አቶ ብርሃኑ ተረፈ የነዳጅ ፍጆታ ቆጣቢ መሳሪያ ፈጣሪው ‹የሚያግዘኝ አጣሁ› ይላል

ቁም ነገር መፅሔት 14ኛ ዓመት ቁጥር 203 ዕትም
ሀገራችን የከርሰ ምድር ነዳጅ የላትም፤በየጊዜው ለነዳጅ የሚወጣው የውጪ ምንዛሪ የሀገሪቱን ሀብት እየተፈታተነ ስለመሆኑ የመንግስት የበጀት ሪፖርቶች ይናገራሉ፡፡ ታዲያ ይህንን ከውጪ ሀገር የሚገባ ነዳጅን የሚቆጥብ በመኪና ጎማ ላይ የሚገጠም መሳሪያ የሰራው የፈጠራ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ተረፈ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽ//ቤት መሳሪያው በመንገድ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ በመሆኑ የግልጋሎት ሞዴል ሰርተፍኬት ቢያገኝም ወደ ተግባር ለመቀየር ከሦስት ዓመታት በላይ እንደፈጀበት ይናገራል፡፡ ‹በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል› እየተባለ በየእለቱ በሚነገርበት ሀገር የፈጠራ ባለሙያው የደረሰበትን ውጣ ውረድ ለቁም ነገር መፅሔት እንዲህ ይገልጻል፡፡
ቁም ነገር፡- ይህንን የነዳጅ ፍጆታ ቆጣቢ የፈጠራ ሥራ እንዴት ልትሰራ ቻልክ?
አቶ ብርሃኑ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን እሞካክር ነበር፤ በተፈጥሮ የፈጠራ ሰው ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ለምን ችግር ፈቺ መሳሪያ አልሰራም በሚል የጀመርኩትን ስራ ነው አሳድጌ እዚህ ደረጃ የደረሰው፡፡
ቁም ነገር፡- ምን ያህል ጊዜ ወሰደብህ?
አቶ ብርሃኑ፡- ወደ 18 ዓመት ነው ይህንን ስራ ከጀመርኩት፤ደህና ነገር ሲገኝ እሰራዋለሁ፤ ደጋፊ ሲጠፋ ደግሞ ይቆማል፡፡ በመጀመሪያ ግን የራሴ መኪና ስለነበረኝ በራሴ መኪና ላይ ነበር ገጥሜ የሞከርኩት፡፡ በችግር ምክንያት መኪናዬን ከሸጥኩ በኋላ ደግሞ ለሁለት መኪናዎች ገጥሜ አሁንም ድረስ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የፈጠራ ስራው በአንድ ሊትር ከ70 እስከ 80 ኪሎ ሜትር ድረስ ነው የሚሄደው፡፡
ቁም ነገር፡- ምን ያህል ውጤታማ ነው? ሙከራውስ ምን ውጤት አስገኘ?
አቶ ብርሃኑ፡- መጀመሪያ ያሳየሁት ለማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ነው፡፡
ቁም ነገር፡- መቼ ማለት ነው?
አቶ ብርሃኑ፡- በ2002 ዓ.ም በደብዳቤ ነው የጠየቅሁት፤ ነዳጅ ቆጣቢ መሳሪያ ስለሰራሁ እንዲሞከርልኝ እፈልጋለሁ ብዬ ማለት ነው፡፡ እነሱም መሳሪያውን ከተመለከቱ በኋላ ባለሙያ መድበው ከአዲስ አበባ ናዝሬት ደርሶ መልስ ላይ ተሞከረ፡፡
ቁም ነገር፡- በማን መኪና?
አቶ ብርሃኑ፡- በእነሱ መኪና ነው የተሞከረው፡፡ የ2006 ሞዴል ቶዮታ ኤክስኪዩቲቨ መኪና ላይ፡፡ በዚህ መሰረት የኢነርጂ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ባዘጋጁት መኪና ላይ መሳሪያውን ገጥሜ ከአዲስ አበባ ናዝሬት ደርሰን ስንመጣ የተነሳነው ከቃሊቲ ስለነበር 143 ኪሎ ሜትር መኪናዋ ተጉዛ የፈጀችው 1.8 ሊትር ነዳጅ ብቻ ነው፡፡ ሁለት ሊትር እንኳ አልሞላም፡፡ ይህም የሚያሳየው በአንድ ሊትር 80 ኪሎሜትር ነው የሄደችው ማለት ነው፡፡ በማግስቱ ደግሞ ራሷኑ መኪና ላይ የኔን ማሽን ሳንገጥም ናዝሬት ደርሳ እንድትመጣ ተደርጎ በሊትር 22 ኪሎ ሜትር ነው የተጓዘችው፡፡ መሳሪያው የአየር ብክለትን ይቀንሳል፤የውጪ ምንዛሪም ያመጣል፤ ሀገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪም ይቀንሳል፡፡
ቁም ነገር፡- መሳሪያው ምድንው የሚያደርገው? የት ላይ ነው የሚገጠመው?
አቶ ብርሃኑ፡-መሳሪያው የመኪናው የኋላ ጎማ ቸርኬው ላይ ነው የሚገጠመው፡፡ የመሳሪያው ስራ የመኪናውን ጎማ በፍጥነት እንዲሽከረከር ማድረግ ነው፡፡ ለወትሮው መኪናው ከሚጓዝበት በሁለት እጥፍ ያሽከረክረዋል፡ ፡በመኪናው ላይ ምንም የሚያመጣው ጉዳት የለም፡ ፡ነዳጅን ግን በከፍተኛ ደረጃ ይቆጥባል፡፡
ቁም ነገር፡- ኢነርጂ ሚኒስቴር ምን አደረገልህ?
አቶ ብርሃኑ፡- ያው መሳሪያው በተግባር ተፈትሾ ውጤታማ መሆኑን በተመለከተ ለአዕምሮአዊ ፅ/ ቤትና ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ደብዳቤ ፃፉ፡ ፡አዕምሮአዊ ፅ/ቤት ሁኔታውን ገምግሞ የግልጋሎት ሞዴል ሰርተፍኬት ሰጥቶኛል፡፡
ቁም ነገር፡- አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲስ?
አቶ ብርሃኑ፡- በጀት የለንም ይህንን ስራ ለመስራት ነው ያሉኝ፡፡
ቁም ነገር፡- በቃል ነው በደብዳቤ?
አቶ ብህረሃኑ ፡- በቃል ነው ያሉኝ፤ቀድሞውኑ ኢነርጂ ሚኒስቴር ስለሆነ ደብዳቤውን የላከላቸው ለእኔ በቃል ነው ምላሽ የሰጡኝ፡፡
ቁም ነገር፡- የአዕምሮአዊ ንብረት ፅ/ቤትን ሰርተፍኬት ካገኘህ በኋላስ የት ሄድክ?
አቶ ብርሃኑ፡- ያልሄድኩበት ቦታ የለም ልልህ እችላለሁ፡፡ የሁሉም ምላሽ ግን ተስፋ የሚሰጥ አይደለም፡፡
ቁም ነገር፡- ለምሳሌ የት የት ሄድክ?
አቶ ብርሃኑ፡- ሊፋኖች ጋር ዶክመንቶቼን አስገብቼ ነበር፤ እንደውልልሃለን ካሉ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል፡፡ ሚድሮክም ሄጄ ነበር፡፡ መቻሬ ሜዳ ያለው ዋናው መ/ቤት ሄጄ ያው እንደውልልሃለን ነው ያሉኝ፡፡
ቁም ነገር፡- የመንግስት ተቋማትንስ ለማነጋገር አልሞከርክም?
አቶ ብርሃኑ፡- የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ደብዳቤ አስገብቼ ነበር፡፡ እነሱም ሁኔታውን አይተው ፕሮፖዛል ይሰራለት ተብሎ ከተሰራና ሙከራ ለማድረግ መኪና ከተጠየቀ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡ ደብዳቤውን መልክት ትችላለህ፡፡
ቁም ነገር፡- አዕምሮአዊ ጽ/ቤትና ኢነርጂ ሚኒስቴርስ የድጋፍ ደብዳቤ ከመፃፍ ውጪ ያደረጉልህ ድጋፍ አለ?
አቶ ብርሃኑ፡- ምንም የለም፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ የኢነርጂ ሚኒስቴር በኢነርጂ ቁጠባ ዙሪያና ኃይል ሰጪ መሳሪያ ዙሪያ የተለያዩ የፈጠራ ስራ ያላችሁ ሰዎች ተመዝገቡና ተወዳደሩ የሚል ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር፡፡ እኔም ፕሮፖዛሉን አሰርቼ አስገብቼ ነበር ፤ ምላሽ የለም፡፡
ቁም ነገር፡- የአዕምሯዊ ጽ/ቤት የሰጠህ የግልጋሎት ሰርተፍኬት ቆሻሻ ውስጥ ላይ ተጥሎ መገኘቱን የሚገልጽ አንድ ፅሑፍ በፌስ ቡክ ላይ ተመለክቼ ነበር፤ ማነው የጣለው?
አቶ ብርሃኑ፡- እኔ እንግዲህ ስራውን ወደ ተግባር ለመቀየር ይረዱሃል ለተባሉ ሰዎች ሁሉ ዶክመንቶቼን ስሰጥ ነበር፡፡ እንግዲህ ማን መሬት ላይ እንደጣለውን አላውቅም፤ እኔም ፌስ ቡክ ላይ እንደዚህ አይነት ነገር አለ ሲሉኝ ነው ያየሁት፡፡
ቁም ነገር፡- በምን ስራ ነው የምትተዳደረው?
አቶ ብርሃኑ፡ -በኮንስትራክሽን ስራ ላይ ነው ያለሁት፤በዚህ ስራ ምክንያት ደግሞ ስራዬንም መስራት አልቻልኩም፤ስራውን ትኩረት ሰጥቶ በባለቤትነት የሚሰራ አካል ማን እንደሆነ ባለማወቅ እየተንከራተትኩ ነው፡፡ይህንን ስራ ወደ ተግባር ለመቀየር በሚል ሙሉ ንብረቴን ነው የሸጥኩት፡፡
ውስጥ መኪናዎች አልፎ ወደ ውጪ ሀገር ተልኮ የውጪ ምንዛሪ ያመጣል የምንል ከሆነ በእጅ በመስራት የሚሆን አይደለም፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ስራው ራሱ ፐርፌክሽን ይፈልጋል፡፡ትንሽ መዛባት ካለ በትክክል ነዳጅ ላይቆጥብ ይችላል፡፡ ስለዚህ በትንሽ ጎጆ ኢንዱስትሪ ሳይሆን በትክክል በማሽን እየተለካ ብረቱ መቆረጥ አለበት፡፡
ቁም ነገር፡- ምን ያህል ወጪ ይፈልጋል ይህንን መሳሪያ የሚያመርት ፋብሪካ ለማቋቋም ?
አቶ ብርሃኑ፡- እኔ ባስጠናሁት ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ይፈልጋል፡፡
ቁም ነገር፡- እንግዲህ ሰሞኑን የተገናኘነው በወገኖቻችን ላይ አስከፊ ግድያ በተፈፀመበት የሀዘን ሳምንት ነው፤ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የሚነገረው ‹በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል› እየተባለ ነው፤ የህ ነገር ላንተ ምን ትርጉም ይሰጥሃል?
አቶ ብርሃኑ፡-የወገኖቻችን ሀዘን አጥንት ዘልቆ የሚሰማ ከባድ ሀዘን ነው፤ኢትዮጵያ የዚህ አይነት ስራ መስራት የሚችሉ ወጣቶች እያሏት ነው በበረሃ ላይ ወጥተው ብዙዎች እያለቁ ያሉት፡፡በበኩሌ ይህ የእኔ ስራ ተግባራዊ ሆኖ ወደ ውጪ ሀገር ተልኮ የውጪ ምንዛሪ የሚያመጣ ከሆነ ፕሮጀክቱን በእነዚህ በበረሃ ላይ ባለቁ ሰማእታት ስም መሰየም ነው ሀሳቤ፡፡ ተዳፍኖ መቅረት የሌለበት ነገር ነው፡፡እነዚህ ወጣቶች ከሀገራቸው የወጡት ለምንድነው? እውቀት ስላነሳቸው ችሎታ ስላነሳቸው አይመስለኝም፡፡ የመስራት እድሉን ፤ድጋፍ በማጣታቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ መሳሪያን የሚያመርት ፋብሪካ ቢከፈት ራሱ ከ200 እስከ 300 የሚደርስ ሰው ቀጠራል፡፡ የስራ እድልን ፈጥራል፡ ፡ ይህንን መሳሪያ ይዜ ከሀገር ብወጣና ሌላ ሀገር ተመርቶ ቢመጣ ሀገሪቱ በውጪ ምንዛሪ እየገዛች ነው የምታስገባው፡፡ እውቀቱም ፈጠራውም መጀመሪያ በሀገር ቤት ቢሰራ ይሻላል በሚል ነው የተቀመጥኩት፡፡
ቁም ነገር፡- በመጨረሻስ?
አቶ ብርሃኑ፡- እንግዲህ ይህንን ሀሳቤን ወደ ተግባር ለመቀየር ስንቀሳቀስ ከጎኔ ባለመለየት ወርክ ሾፑን ሳይቀር እየለቀቀልኝ ውጤታማ እንድሆን ያደረገኝ ጎፋ አካባቢ የሚገኘውን ወዳጄ የግሩም ኢንጂነሪንግ ባለቤት በጣም አመሰግናለሁ፡ ፡ ተስፋ ባጣህበት ጊዜ ተስፋ የሚሆኑህ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ በተረፈ የግል ባለሃብቶችም ሆኑ መንግስት ይህንን ፕሮጀክት ወደተግባር ለመቀየር ፍላጎቱ ያለው ካለ በማንኛውም መልክ አብሬ ለመስራትና የሀገሬን ስም ለማስጠራት ዝግጁ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ አገልፃለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡































No comments:

Post a Comment