Saturday, April 18, 2015

‹‹አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት ያለምርጫ ሥርዓት በኃይል ለመጣል የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ ትቃወማለች››

‹‹አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት ያለምርጫ ሥርዓት በኃይል ለመጣል የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ ትቃወማለች››
ዌንዲ ሼርማን፣ የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

የአሜሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዌንዲ ሼርማን ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነውን ግንቦት ሰባትን ጨምሮ፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) የመሳሰሉ

በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን የአሜሪካ መንግሥት እንደማይደግፍ አስታወቁ፡፡

ባለፈው ሳምንት ለሁለት ቀናት ጉብኝት አዲስ አበባ የተገኙት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከአራት ዓመታት በፊት አሸባሪ የተባሉትን ድርጅቶች፣ በሚመለከት ‹‹አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት ያለምርጫ ሥርዓት በኃይል ለመጣል የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ ትቃወማለች፤›› በማለት ለባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡

በአሜሪካ ኤምባሲ በተለይ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ መንግሥታቸው ግንቦት ሰባትን፣ ኦነግንና አብነግን በሚመከለት የኢትዮጵያን መንግሥት ሥጋት እንደሚጋራና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም መረጃ እንደሚለዋወጥ አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥታቸው እነዚህን ድርጅቶች በአሸባሪነት እንዳልፈረጀ ገልጸዋል፡፡

‹‹ድርጅቶቹን በአሸባሪነት ለመፈረጅ የሚያበቃ ማስረጃ አላገኘንም፡፡ እንደማስበው የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ድርጅቶች በሚለከት የያዘውን አቋም እንድንገነዘብ ይፈልጋል፡፡ እኛም እንዲሁ፡፡ በሕግ ማስከበር፣ በደኅንነት ጉዳዮችና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ መረጃ እየሰጠናቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይሻሉ፡፡ እኛም የኢትዮጵያን አመለካከት እንረዳለን፤›› በማለት ለሪፖተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች በአሜሪካ እንደሚኖሩ እናውቃለን፡፡ መንግሥት ያቀረባቸውን ሥጋቶች ተገቢነት ባላቸው መንገዶች እንደምንፈታቸው እናረጋግጣለን፤›› በማለት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሼርማን ተናግረው፣ የተጠቀሱትን ሥጋቶች አሜሪካ በራሷ መንገድና አካሄድ መፍትሔ እንደምትሰጣቸው፣ እንደምትገነዘባቸውና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም እንደምትጋራቸው አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ አቶ በረከት ስምዖን ጋር በፀጥታ፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም በመጪው ምርጫ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው ታውቋል፡፡

‹‹በ1997ቱ ምርጫ በርካቶች አዲስ ቀን መምጣቱንና ይህም ይበልጥ እየተሻሻለ እንደሚቀጥል ማሰባቸው ይሰማኛል፡፡ እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ በምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ላይ ሥጋቶች አሉ፤›› ያሉት ምክትል ሚኒስትሯ፣ ‹‹ተስፋ የምናደርገው ግን ምርጫው የሚፈለገውን እንደሚያሟላ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሼርማን በኢትዮጵያ ስለታሰሩት ጋዜጠኞችም ያላቸውን ሥጋቶች ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ‹‹ሁሉም አገር የራሱ የፍትሕ ሥርዓት ስላለው ያንን እናከብራለን፡፡ ሆኖም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ከታሰሩት ጋዜጠኞች በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩት በርካታ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች እውነተኛ ተቃዋሚ ለመሆን የሚያስችላቸውን ምኅዳር ስለማግኘታቸውም ሥጋት መኖሩን አውስተዋል፡፡

‹‹ሰባ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖራቸው ማወቃችን ያስደስተናል፤›› ያሉት ሼርማን፣ ጠንካራና ቁርጠኛ ፓርቲ ስለመኖሩም ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ረገድ ገና አፍላ በመሆኗ በጊዜ ሒደት ይህ እየበሰለ ሄዶ የፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓቱም እውነተኛ ምርጫ ለሕዝቡ እንደሚያመጣ እምነታቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሲቪል ማኅበረሰቡ በኩል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ያወደሱት ሼርማን፣ መንግሥትን በማስገደድ ረገድ፣ ችግሮችን በመፍታትና ድምፅ ለሌላቸው ሰዎች ተሟጋች በመሆን የሲቪል ማኅበራት የሚወጧቸውን ተግባራት የሚያስመሰግኑ ናቸው ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድን በሚመለከት ሼርማን እንዳብራሩት፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የአካባቢው አጋርነት ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ቀውስ በማስመልከት ሲናገሩም፣ የአሜሪካ መንግሥት የትኛውንም ዘዴ በመጠቀም ተፋላሚዎቹን ወገኖች ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት እንደሚጥር አስታውቀዋል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment