Tuesday, November 15, 2016

በደቡብ ኦሞ ዞን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ታሰሩ

በኮማንድ ፖስት ስም የደቡብ ኦሞን ዞን የሚመሩት የህወሃት የደህንነት ሰራተኞች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችንና ወጣቶችን እየያዙ በማሰር ላይ ናቸው። የኦሞ ህዝብ ዲሞክራሲ ህብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ተጠሪ መምህር አለማየሁ፣ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የዞን ተጠሪ የነበሩት አቶ ስለሺ ጌታቸው እንዲሁም የኦሞ ህዝብ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዳዊት ካብት ይመር ትናናት ከንጋቱ 12 ሰአት ላይ በ15 ታጣቂዎች ታጅበው እስር ቤት ተወስደዋል። ዛሬም ሌላ አንድ የድርጅቱ አባል ተወስዶ ታስሯል።
እነ አቶ አለማየሁ እስካሁን ፍርድ ቤት አልመቅረባቸውን የኦህዲህ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ገልጸዋል። ከፖለቲካ ድርጅት መሪዎች በተጨማሪ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በመታሰራቸው የዋና ከተማዋ ጅንካ እስር ቤት በአሰረኞች ተጨናንቋል።
አመራሮች “ አዋጁ እርምጃ እንድትወስዱ መብት ሰጥቷችሁዋል እና እስረኛ እያመጣችሁ እስር ቤት ከምታጨናንቁ እርምጃ ለምን አትወስዱም” እያሉ በአካባቢው ፖሊሶችና የልዩ ሃይል አባላት ለተዋቀረው የወታደራዊ እዙ አባላት መመሪያ እየሰጡ ቢሆንም፣ የእዙ አባላት ግን “ ጥፋታቸውን ባልተረዳንበት ሁኔታ ነገ አብረነው ከምንኖረው ህዝብ ጋር መጋጨት አንፈልግም፣ እርምጃም አንወስድም” የሚል መልስ የሰጡ ሲሆን፣ እስርቤቶች መጣበባቸውን ተከትሎ የተወሰኑ ወጣቶች በዋስ እንዲፈቱ ሲደረግ ሌሎች ወደ ውሀኒ ተልከዋል። በዞኑ የመንግሥት አመራር የነበሩና አሁንም በሥልጣን ላይ ያሉ የሃመር ተወላጆች እየታሰሩና እየታደኑ መሆኑም ታውቋል።
የቀድሞው የሃመር ወረዳ አስተዳዳሪ በቀጣይም የዞን ም/አስተዳዳሪ የነበሩት  አቶ በእምነት፣  አቶ ዲለማ ጎዴ፣ እንዲሁም የሃመር ወረዳ ፖሊስ አዛዥ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣  የቀድሞው የተወካዮች ም/ቤት አባል የነበሩት አቶ ሣሙኤል ገርሾም እየተፈለጉ ነው፡፡ አገዛዙ እየወሰደው ያለው እርምጃ  ከሃመርና በና ወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር የተገናኘ  እንጂ ሰዎቹ ወንጀል አልፈጸሙም በሚል በጂንካ ከተማ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የሃመር ወጣቶች እርምጃውን ተቃውመውታል።በዚህም የተነሳ በከተማው ውጥረት መንገሱን ምንጮች ገልጸዋል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ በበና ጸማይና ሃመር ወረዳዎች የወጣቶች ተቃውሞ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣  አንድ ፖሊስ ተገድሎ፣ ሁለት ፖሊሶች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ የጂንካ ሳላማጎ መደበኛ መንገድ መዘጋቱም ታውቋል። በእንግሊዝኛ ኮማንድ ፖስት እየተባለ የሚጠራው ወታደራዊ ማዘኛ ጣቢያ  አመራር የሚሰጠው በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ በተቀመጡ የህወሃት አባላት መሆኑ የዞኑን ተወላጆች እጅጉ ማስቆጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
Source: http://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%8B%B0%E1%89%A1%E1%89%A5-%E1%8A%A6%E1%88%9E-%E1%8B%9E%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%8D%96%E1%88%88%E1%89%B2%E1%8A%AB-%E1%8B%B5%E1%88%AD%E1%8C%85%E1%89%B5-%E1%88%98%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD/

No comments:

Post a Comment