Thursday, May 19, 2016

ወደ ደቡብ ሱዳን ገብቶ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር አካባቢውን ለቆ መውጣቱ ተነገረ

ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2008)
በቅርቡ ከጋምቤላ ክልል ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ለማስለቀቅ ወደ ደቡብ ሱዳን ገብተው የነበሩ ወደ ሶስት ሺ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሃገሪቱ መውጣታቸውን የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት አስታወቁ።
ወታደሮቹ ከጋምቤላ ክልል በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው የፖቻላ ግዛት አካባቢ ሰፍረው የነበረ ሲሆን፣ በድርድር የተቀቁ ህጻናትን ሲቀበሉ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይሁንና፣ ወታደሮቹ ሰፍረው በነበረበት አካባቢ የታፈኑ ህጻናት ባለመኖራቸው ምክንያት ወታደሮቹ ከሰፈሩበት ቦታ ለቀው መውጣታቸውን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
እስከ ሃሙስ ድረስም ታፍነው ከተወሰዱት ከ100 በላይ ህጻናት መካከል 53ቱ በድርድር የተለቀቁ ሲሆን፣ የቀሪዎቹ ህጻናት ሁኔታ ግን አልታወቀም።
የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ህጻናቱን ለማስለቀቅ ከሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጋር ድርድር መካሄዱን ቢገልጹም ድርድሩ በምን ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ እንደሆነ ግን የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
የኢትዮጵያ መንግስት የታፈኑ ህጻናትን ለማስለቀቅ በሚል በርካታ ታንኮችና ወታደሮችን ወደ ደቡብ ሱዳን ቢያሰማራ ልጆቹን ለማስለቀቅ የወሰደው እርምጃ አለመኖሩን የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ሃላፊዎች ለሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ገልጸዋል።
የሃገሪቱ ጦር ሰራዊት ተወካይ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል አቲም ኦት ከሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጋር የሚካሄደው ድርድር እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በጋምቤላ ክልል በተፈጸመው ጥቃት ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከ100 የሚበልጡ ህጻናትም ታፍነው ተወስደዋል።
በዚሁ ጥቃት ከ20ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎችም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።

Source: http://amharic.ethsat.com/%e1%8b%88%e1%8b%b0-%e1%8b%b0%e1%89%a1%e1%89%a5-%e1%88%b1%e1%8b%b3%e1%8a%95-%e1%8c%88%e1%89%a5%e1%89%b6-%e1%8b%a8%e1%8a%90%e1%89%a0%e1%88%a8%e1%8b%8d-%e1%8b%a8%e1%8a%a2%e1%89%b5%e1%8b%ae%e1%8c%b5/

No comments:

Post a Comment