Thursday, January 28, 2016

ኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮችን ከስልጣን ሊያነሳ እንደሆነ ተገለጸ


ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2008)
የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በስራ አስፈጻሚ ደረጃ አስቸኳይ ስብሰባ መቀመጡ ታወቀ።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሙክታር ከድር እየተገመገሙ እንደሆነና ስልጣናቸውን ሊለቁ እንደሚችሉ ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ከጨፌ ኦሮሚያ የውስጥ ምንጮች ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኦህዴድ በመላው የኦሮሚያ አካባቢ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ቁልፍ አመራር እየገመገመ መሆኑ ታውቋል።
የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴና ስራ አስፈጻሚው ግምገማውን በአቶ ሙክታር ላይ በማተኮር ግምገማ እያደረገ እንደሆነ ከስፍራው የደረሰው ዜና ያስረዳል። የግምገማው ውጤትም አቶ ሙክታር ከድርን ከፕሬዚደንትነት በማንሳት ሊጠናቀቅ እንደሚችል የውስጥ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። በአቶ ሙክታር ከድር ምትክ የገቢዎችና ጉምሩክ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በክር ሻሌ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለማወቅ ተችሏል።
ግምገማው ከአቶ ሙክታር ከድር በተጨማሪ የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ከስልጣናቸው ሊነሱ እንደሚችሉ የኢሳት የጨፌ ኦሮሚያ የውስጥ ምንጮች ግምታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ ነጋዴዎችን ለይቶ ለማወያየት ውሳኔ ማሳለፉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በክልል ደረጃ የኦሮሞ ባለሃብቶችን በመሰብሰብ በወቅታዊ የህዝብ ንቅናቄ ላይ ለማወያየት የታቀደው በየአካባቢው የተደረገው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ውጤት አልባ መሆኑን ተከትሎ ነው። በቅርቡ በአቶ ዱላ ገመዳና በሌሎቹ የኦህዴድ አመራሮች ተጠርቶ በነበረው የኦሮሞ ባለሃብቶች ስብሰባ ላይ ባለሃብቶቹ ጥቁር ለብሰው በመምጣት የመንግስት የግድያ ዕርምጃ መቃወማቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment