ኀዳር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በስፋት በመሰማራት የአነስተኛ ነዋሪውን ህይወት ለመቀየር ትልቅ መፍትሔ አለው በማለት የገዢው መንግስት በስፋት እየሰራበት ያለው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ ከሌሎች የባንክ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለየ ከፍተኛ ወለድ በማስከፈል ህብረተሰቡን እየበዘበዘ መሆኑን ደንበኞች በተለይ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡ የብድር ተቋሙ በየአካባቢው በሚከፍታቸው ቅርንጫፎች ሌሎችን የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የተለያየ ምክንያቶችን በመፍጠር እንዳይሰሩ በማድረግ በተለይ ለአርሶ አደሩ በሚያቀርበው ብድር በብቸኝነት ለመጠቀሙ ምክንያት መሆኑን አስተየየታቸውን የሰጡት ነዋሪዎች፣ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የሚቀጠሩት ሰራተኞች እርስ በርስ የተመራረጡና በዝምድና የተሳሰሩ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት በፍትሃዊነት ለማግኘት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡
የብድር አገልግሎት ተቋሙ በተለይ ከገጠር ረዥም መንገድ ተጉዘው የሚመጡትን ተበዳሪ አርሶ አደሮችን ጉዳያቸውን ጨርሰው ቶሎ ለመመለስ እንዲችሉ ከማመቻቸት ይልቅ በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዲያስተናግዱ ማስገደዱን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ በደቂቃዎች ይፈጸማሉ ተብለው የጊዜ ገደብ የተቀመጠላቸው ስራዎች ለቀናት ግፋ ሲልም ለሳምንታት እንደሚፈጁባቸው መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች ኑሯቸውን ለመለወጥ በማሰብ የብድሩ ተጠቃሚ ቢሆኑም በአሰቡት መንገድ ችግራቸውን ሊቀርፍላቸው አለመቻሉን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች ፣ አርሶ አደሩ ጊዜውን በከንቱ አባክኖ በብድር የሚያገኘውን ገንዘብ ከገዥው መንግስት በከፍተኛ ትርፍ በዱቤ ለሚወስዱት ማዳበሪያ ክፍያ እንደሚያውሉት ገልጸዋል፡፡የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአሁኑ ሰዓት በርካታ ህንጻዎችን በየከተሞች በመገንባት ከፍተኛ ትርፍ በማካበት ላይ መሆኑ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ኮንትራክቶችና ባለሃብቶች 5 ሺ ብር በነፍስ ወከፍ እንዲከፍሉ የከተማዋ አመራሮች ስልክ እየደወሉ በማስገደድ ላይ ናቸው፡፡ገንዘቡ ህዳር 11 ለሚከበረው የብአዴን-ኢህአዲግ በዓል አከባበር ለማዋል የታሰበ ነው፡፡ገንዘቡን እዲሰጡ የሚገደዱት ባለ ሃብቶች በሃገር ባይኖሩም ገንዘቡን እንዲከፍሉ በሁለትና ሶስት አመራሮች እንዲሁም በጓደኞቻቸው በስልክ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሆነ እየተናገሩ ነው፡፡
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment