Tuesday, October 27, 2015

“በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አለ” የሚለው ተረት ተረት ነው ሲሉ ዶ/ር መረራ ጉዲና ገለጹ


ጥቅምት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊቀመንበር እና የመድረክ የአመራር አባል የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ይህን ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበውን የውይይት ግብዣ ተቃዋሚዎች ውድቅ ማድረጋቸውን ለፓርላማ አባላት መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
መንግስት በጠራው የአምስት ኣመታት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይት ላይ ያልተሳተፉ እንደመድረክ፣ ሰማያዊ እና መኢአድ ያሉ ፓርቲዎች ያቀረቡት ምክንያተ ውሃ ያማያነሳ ነው ያሉት አቶ ሃይለማርያም ፣ ፓርቲዎቹ ያልተሳተፉት በሕጋዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት አይደለም በማለት መሆኑን ጠቅሰው ወደፊት ከየትኛው መንግስት ጋር እንደሚወያዩ እናያለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ሲናገሩ፣ “በቅድሚያ አንነጋገርም አላልንም፣ ቅድሚያ መሰረታዊ በሆኑት የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ ነጻ ምርጫን ፣ ነጻ ሚዲያን፣ በነጻነት መንቀሳቀስንንና በመሳሰሉት መሰረታዊ መብቶች ጉዳይ እንነጋገር ” ነው ያለው ካሉ በሁዋላ፣ እነሱ በሚሉት ጉዳይ ላይ ለመነጋገርም ፣ በር ዘግቶ ሳይሆን፣ በነጻ ሜዳ፣ ለህዝብ በቀጥታ በሚተላለፍ መልኩ መሆን አለበት በማለት በጽሁፍ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
መድረኩን ተጠቅማችሁ ለምን ሃሳባችሁን ለማስተላለፍ አልቻላችሁም በሚል ለተጠየቁት ዶ/ር መረራ፣ የኢህአዴግ ፖሊሲ ስልጣን ወይም ሞት በመሆኑ፣ የልጅ ስራ መጫወቱ ትርጉም የለውም ብለዋል።
አገሪቱ አደጋ ውስጥ ናት ያሉት ዶ/ር መረራ ዲሞክራሲው የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ መግባቱን፣ አገሪቱ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እያመራች መሆኑዋንና የሚባለው ዲሞክራሲ፣ ሰላምና መረጋጋት አለመኖሩን እንዲሁም ረሃብና ድህነት ታሪክ ሆኗል የሚባለውም ተረት ነው በማለት ገልጸዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ የብድር አወሳሰዳችን የተለየ በመሆኑ ለጫና አልተዳረግንም ብለዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በፓርላማ ተገኝተው ከምክርቤቱ አባላት የብድር ዕዳ ክምችት አለ ስለመባሉ የተጠየቁ ሲሆን መንግስታቸውን የብድር አወሳሰድ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በማነጻጸር እኛ የተሻልን ስለሆነ ለዕዳ ጫና አልተዳረግንም ብለዋል፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለዕለት ተዕለት ሥራ ማስኬጃና ደመወዝ ክፍያ ብድር ይወስዳሉ፣
እኛ ግን ለትርፍ የሚሰሩ ተቋማት ማለትም እንደቴሌ፣ አሌክትሪክ፣ ስኳር፣ ባቡር ወዘተ ስንል ብድር እንወስዳለን፣ ኩባንያዎቹ ሰርተው ብድራቸውን የሚከፍሉ በመሆኑ ያን ያህል ስጋት እንደሌለው በመግለጽ ለማጣጣል ሞክረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተወሰደው የኢትዮጽያ የኤክስፖርት ዘርፍ አፈጻጸም ባለፉት ሶስት ኣመታት የተዳከመ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ክስተት በዕዳ ጫና አለካክ ላይ የራሱ ተጽዕኖ እንዳለው አምነዋል፡፡
ለልማት ስራዎች ብድር የምንወስደው የመክፈል አቅም ስላለን ነው የሚሉት አቶ ሃይለማርም መክፈል እስከቻልን ድረስ ብንወስድ ችግር የለውም ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ መድረኩን ተጠቅመውበታል፡፡
የኣለም ባንክ በቅርቡ ኢትዮጽያ ከፍተኛ ዕዳ ጫና ካለባቸው የአፍሪካ አገራት አንዱዋ መሆንዋን በመጥቀስ መንግስት ጥንቃቄ እንዲደርግ መምከሩ የሚታወስ ነው፡፡
Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment