Monday, October 5, 2015

ከ8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለረሃብ ተጋልጧል


መስከረም ፳፬ (ኅያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት እና አለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን 500 ሺ ህዝብ በረሃብ መጠቃታቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ በከተሞች የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎች ቁጥር ሲጨመር አጠቃላይ የተረጅዎችን ቁጥር ከ8 ሚሊዮን በላይ ሊያደርሰው እንደሚችል መረጃዎች አመልክተዋል።
በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሪፖርት ሲደረግ የቆየው በገጠሩ የሚታየው ችግር ብቻ ነው። ይሁን እንጅ የከተማና የኮንስትራክሽን ልማት ሚኒስትር መኩሪያ ሃይሌ ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል በአንድ ስብሰባ ላይ በሰጡት መረጃ፣ ከድህነትና ስራ አጥነት ጋር ተያይዞ በከተሞች ብቻ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ 4 ሚሊዮን 700 ሺ ዜጎች መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል።
የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ 11 ናቸው። መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን እንዲሁም ምግብ ከማቅረብ ባሻገር የሚሰሩና የማይሰሩትን በመለየት ስልጠና ለመስጠት መታቀዱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተሞች አካባቢ ከዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ወጣቶች ጭምር ለስራአጥነት እየተዳረጉ መምጣት ማህበራዊ ችግሩን ያባባሰ ሲሆን፣ ገዥውን ፓርቲም ድንጋጤ ላይ ጥሎታል።
በአገሪቱ የተከሰተውን ረሃብ ለመታደግ አንዳንድ አገሮች እርዳታ መስጠት ቢጀምሩም በቂ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እስካሁን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምግብ ፕሮግራም፣ ኖርዌይና እስራኤል እርዳታ ለግሰዋል። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ እርዳታ በማቅረብ የሚታወቁት አሜሪካና ካናዳ እስካሁን በይፋ የሰጡት እርዳታ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።
ድርቁ አስከፊ በሆነባቸው በኦሮምያ ፣ አፋርና ደቡብ እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም አካባቢዎች እንስሳት በመግብ እጥረት እየሞቱ ሲሆን፣ በትግራይ ደግሞ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ በሽታ ተከስቷል።
መንግስት የአለማቀፍ እርዳታ እየጠየቀ ባለበት ወቅት፣ አሁንም ከፍተኛ ወጪ እያወጣ በአላትን እያከበረ ነው። ባለፈው አመት ለብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ ለባንዲራ ቀን፣ ለመከላከያ ሰራዊት ቀን፣ ለህወሃት 40ኛ አመት ምስረታ፣ ለኦህዴድ 25ኛ አመት በአል እና ለሌሎችም የፖለቲካ ስልጠናዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ አድርጓል። በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም የገጠር ቀበሌዎች ዜጎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሞአቸው እርዳታ በሚጠይቁበት ወቅት፣ ክልሉን አስተዳድረዋለሁ የሚለው ብአዴን፣ 35ኛ አመት በአሉን ለማክበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መመደቡንና ጋዜጠኞችንና አርቲስቶችን ወጪያቸውን በመሸፈን የተለያዩ ቦታዎችን በማስጎብኘት ላይ መገኘቱ የክልሉ መነጋገሪያ ሆኗል።
ገዢው ፓርቲ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ረሃብ እንዳይታወቅበት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አረና ፓርቲ አስታውቋል። ድርጅቱ የአገራችንና የክልላችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚመለከት በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ “በ40ኛው የህወሓት ምስረታ በአል ከአጠቃላይ ታራሹ መሬት ግማሹ በመስኖ እየለማ ነው እንዳልተባለ በትግራይ ክልልና በብዙዎች ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተጋርጦ ያለው የድርቅ ችግር መንግስት ችግሩ ለማሳነስና ለመደበቅ እየሞከረ ቢሆንም ችግሩ ተገቢውን አትኩሮት እንዲሰጠው የድርቁ ተጠቂዎች በረሃብ እየተጠቁ ሰለሆኑ ከብቶቻቹሁን ሽጡ ከማለት ከብቶቻቸውን የሚያድኑበት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግ የእንስሶቹ ምግብ እንዲቀርብላቸው በትግራይ ህዝብ ደም የተገኘው የትእምት ሃብትም ግዜ ሳይጠፋ የህዝቡን ችግር በመፍታት የራሱን ሚና በወቅቱ እንዲጫወት ” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
አረና አያይዞም “አገራችን ኢትዮጵያ ትሁን ትግራይ በአሁኑ ግዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ፣ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ችግር፣ የፍትህ እጦት፣ የስራ እጦት፣ የወጣቶች ስደት፣ ሙስና ፣ የሚድያ አፈና፣ የፖለቲከኞች፣ የጋዜጠኞችና ፀሓፊዎች አፈና፣ እስራት፣ ሰፊ አገሪቱን አካባቢ የሚሸፍን የዝናብ እጥረት፣ ድርቅና ርሃብ ተደማምረው የአገራችን ህዝቦች ቀውስ ውስጥ ” ገብተዋል ብሎአል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment