ጷግሜን ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚመራው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ2005 ዓ.ም በአዲስአበባ ከተማ
አስተዳደር የራራ መኖሪያ ቤቶችን ለማግኘት በድጋሚ የተካሄደውም ምዝገባ ዳግም እከልሳለሁ ማለቱ አብዛኛዎችን ነዋሪዎች አስቆጣ፡፡
ሚኒስቴሩ በመጋቢት 2007 ዓ.ም የወጣው 10ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ ነዋሪው ከአቅሙ በላይ መሆኑን መግለጹን መነሻ በማድረግ ተመዝጋቢዎች አቅማቸውን የፈቀደውን እንደሚዘገቡ ዳግም ዕድል ለመስጠት ያለመ መሆኑን ሰሞኑን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቆአል፡፡ አስተዳደሩ 20 በ80 ወይንም ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ባለፉት
12 ኣመታት ሲገነባ የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ 10 በ90 የሚባል ፕሮግራም እንዲሁም መካከለኛ አቅም ያላቸውንና ዲያስፖራውን ለመያዝ ሲባል 40 በ60 የሚባለውን የቤቶች ግንባታ መርሃግብር መዘርጋቱ የሚታወስ ነው፡፡
አስተዳደሩ በ1997 ዓ.ም ባካሄደው የመጀመሪያ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ከ350ሺህ በላይ ሕዝብ የተመዘገበ ቢሆንም ከእነዚህ ቤት ፈላጊዎች መካከል ከ10 ዓመት በኃላ ቤት ገንብቶ ከ1 አስከ 9ኛ ዙር ማስረከብ የቻለው 100ሺህ እንኩዋን እንደማይሞላ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በ2005 ዓ.ም በድጋሚ በተካሄደው ምዝገባ አዲስ ቤት ፈላጊዎችን ጨምሮ 994 ሺህ 788 ሕዝብ የተመዘገበ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ነባር ተመዝጋቢዎች ብቻ 135 ሺህ ገደማ መሆናቸው ታውቆአል፡፡ ከእነዚህ ነባር ተመዝጋቢዎች መካከል በ10ኛው ዙር 32 ሺህ ነዋሪዎች ዕጣ የወጣላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ በ11ኛው ዙር እንደሚወጣላቸው ቃል ተግብቶላቸው በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡
የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ10ኛው ዙር በአዲስአበባ ዕጣ የወጣላቸው ነዋሪዎች በመንግስት ከፍተኛ ድጎማ ለሚሰሩ ቤቶች የተቀመጠላቸው የግዥ ግምት ካለፉት ጊዜያት ሲነጻጸር ለስቱዲዮ ቤቶች በካሬሜትር 2ሺ483፣ ለባለሶስት መኝታ ቤት 4ሺ 776 ብር መሆኑ እጅግ ከፍተኛና የተጋነነ ዋጋ ነው በሚል ተቃውሞ አስክትሎአል፡፡
በርካታ ህዝብም በቤቶቹ ግንብታ ወቅት በሙስናና ብልሹ አሰራር በሚፈጠር ክፍተት፣ በወቅቱ ግንባታውን ባለማጠናቀቅ አለአግባብ የሚባክን ገንዘብ ወደሕዝቡ በዕዳ መልክ መተላለፍ የለበትም በሚል ጉዳዩ ተጠንቶ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድም ሕዝብ በተገኘው መድረክ ሁሉ ሲወተውት ከርሞአል፡፡
ሆኖም ሚኒስቴሩ ለምን የቤቶቹ ዋጋ ሊጋነን ቻለ የሚለውን መልስ ከመስጠት ይልቅ መሰረተ ልማት ዝርጋታና ለመሬት የሊዝ ክፍያና ግዥ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ያለአንዳች ድጎማ የሚያለሙ ነጋዴ የሪልስቴቶች አልሚዎች የቤቶች ዋጋ ጋር በማነጻጸር “የእኛ ዋጋ ርካሽ ነው» ወደሚል ያልተገባ ንጽጽር ውስጥ በመግባት ችግሩን ለመሸፋፈን ሲጥር መቆየቱን ለጉዳዩ
ቅርበት ያላቸው አስታውሰው፣ አሁን ደግሞ ሕዝቡ ከዛሬ ነገ ዕጣ ይወጣልኛል ብሎ በሚጠብቅበት ሰዓት ዳግም የክለሳ ምዝገባ አደርጋለሁ የሚል ነገር መምጣቱ መንግስት ለገባው ቃል እንኳን የቱን ያህል ታማኝ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ከግንቦቱ 2007 ምርጫ ቀደም ባሉት ጊዜያት 11 ዙር ዕጣ እና 40 በ60 ቤቶች ዕጣ በሰኔ ወር 2007 እንደሚወጣ፣ በመጋቢት ወር 2007 በ10ኛው ዙር ዕጣ የወጣላቸው ነዋሪዎች በሁለት ሳምንታት ጊዜያት ቤታቸውን እንደሚረከቡ ለሕዝብ ቃል ተግብቶ የነበረ ቢሆንም አንዳቸውም አለመፈጸማቸው ሕዝብ በመንግስት ላይ ያለውን አመኔታ የጎዳ መሆኑን ምንጫችን አስታውሶ አል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሕዝቡ በዋጋ ላይ ሊያማርር የቻለው ከአቅሙ በላይ ቤት በመመዝገቡ ነው በሚል የክለሳ ምዝገባ እንዲካሄድ በእነአቶ መኩሪያ መወሰኑ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር ከመክፈት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው፣ ውሳኔውም ተጨባጩን እውነታ ያላገናዘበና ሕዝብንም የናቀ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ሚኒስቴሩ በድጎማ የሚሰሩ ቤቶች ለምን ዋጋቸው ሊጋነን ቻለ በሚል በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ጥናት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ሲጠበቅ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ወደማድበስበስ መግባቱ አሳፋሪና አሳዛኝ መሆኑንም በአዲስአበባ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አስተያየት ጠቁሟል፡፡
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment