August 20, 2015
ዛሬ በአገራችን ውስጥ በፖለቲካ አቋም ልዩነት ሣቢያ እንዲሁም የሃይማኖት ነጻነት እንዲከበር በጠየቁ ወገኖቻችን ላይ የወያኔ አምባገነን መንግሥት እያደረሰ ያለው ኢሰብአዊ ድርጊት በእጅጉ ተባብሦ ይገኛል::Ethiopian Muslims protest continue July 21, 2012
የወያኔ አገዛዝ ሠለባ የሆኑ የፖለቲካ መሪዎች፣ የሙስሊም ሃይማኖት መሪዎች፣ ከየቀዬያቸው እየተፈናቀሉ የሚገኙ ወገኖቻችንን በተመለከተ በተደጋጋሚ እና በማያቋርጥ መልኩ በዚህ ሰው በላ ሥርዐት እየተደረገ ያለው ጭቆና ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደደረሰ እንረዳለን::
አዎ ዛሬ በአገራችን በዴሞክራሲ እጦት ምክንያት በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ ውድ ዜጎች ያሉባት፣ በእምነትና በዲሞክራሲ ነጻነት እጦት ሣቢያ ህብረተሰባችን አፉ ተሸብቦ የሚገኝባት፣ ህፃን አዋቂ ሳይባል በልማት ስም የሚፈናቀልባት፣ ለዘመናት በጽናት የቆዩ የእምነት ቦታዎች የሚደፈርባትና በህዝብ መካከል ጸንቶ የቆየውን አብሮነት ለመናድ ከፍተኛ ውንብር የሚፈጸምባት፣ የዘር ማጥራት የሚካድባትና በዝርዝር ቢገለፁ ቦታና ጊዜ የማይበቃቸው የአፈናና የጭቆና ተግባራት የሚከናወንባት ሀገር ሆናለች::
በህግ የተደነገጉ የሃይማኖት ነጻነታቸውን ለማስከበር ሠላማዊ ትግል ሲያደርጉ በነበሩ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በርካታ የሃይማኖትና የህብረተሰብ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች እና አክቲቪስቶች ላይ ሲካሄድ የነበረው ለ3 አመታት የቆየ የችሎት ድራማ ሐምሌ 27 ቀን 2007 መንግስት ራሱ አሳሪ፣ ከሳሽ፣ መስካሪ፣ ፈራጅ ግልጽ በሆነበት ክስ የቅጣት ፍርድ ያስተላለፈ ሲሆን ንጹህ ወንድሞቻችን ላይ ከ 7 እስከ 22 አመታት የሚደርስ እስራት መበየኑ ይታወቃል:: በወንድሞቻችን ላይ የተሰጠው ኢፍትሐዊ ውሳኔ አገራችን ምን ያህል ከፍትህ የራቀች መሆኗን በድጋሚ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው::
የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ላለፉት አራት አመታት የመንግስትን አሰቃቂ ግፎች ሲያስተናግድ ቆይቷል:: “እኔ ለክቼ የሰራሁልህን እንጂ በነጻነት የመረጥከውን እምነት ማራመድ አትችልም” በሚል አምባገነናዊ ስርአቱ የከፈተበትን ዘመቻ እጅግ በሰለጠነና ሰላማዊ መልኩ ሲያስተናግድ ቆይቷል::
ሙስሊሙ ማህበረሰብ እነዚህን ግፎች በሰላምና በትእግስት ሲያስተናግድ የቆየው ድል ያለመስዋትነት እንደማይገኝ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው:: ዛሬም በማንአለብኝነት በሙስሊሙ ውድ ኮሚቴዎችና ረዳቶቻቸው ላይ የፈጸመው የግፍ ውሳኔ የስርአቱን የተባ የፍርድ ስርአትና ለሙስሊሙ ማህበረሰብ በአጠቃላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያለውን ንቀት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው::
እኛም በኦክላንድ ኒውዚላንድ የምንገኝ ኢትዮጵያን ከዚህ በፊት የተላለፈውን ጥፋተኝነት ብይን እንደተቃወምነው ሁሉ ዛሬም ይህንን ፍርድ በጽኑ እናወግዛለን:: ምንም እንኳን የሙስሊም መሪዎች ላይ የተሰጠው የፍርድ ውሳኔ አሳዛኝ ቢሆንም የተጀመረውን ትግል ይበልጥ እንዲቀጣጠል እንደሚያደርገው ቅንጣት ያህል አንጠራጠርም::
በተለያየ ጊዜያት እየተፈጸመ እንደሚገኘው በፖለቲካ እምነታቸው ለአገራቸው ቀናኢ ሆነው በግንባር ቀደምነት ትግሉን ሲመሩ የነበሩትን የፓርቲ መሪዎችና አባሎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በሽብርተኝነት ስም የረዥም ጊዜ እስራት በመወሰን ከህዝብ እይታ በመሰወር በመግደል እንዲሁም በሞትና በህይወት እንዲኖሩ የተወሰነባቸውን ሁል ግዜም እናስባቸዋለን::
በአገራችን እየደረሰ ያለውን የግፍ አገዛዝ በማስመልከት በተባ ብእራቸው ሃሳባቸውን በጽሁፍ በማቅረባቸው እንደ ሽብርተኛ ተቆጥረው ለረዥም አመታት የእስር ሰለባ የሆኑትን ነጻ ጋዜጠኞችን አብረን እናስባችዋለን::
በመሆኑም እኛ በኦክላንድ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ያሉንን ልዩነቶች በማቻቻል መብታችንን ለማስከበርና ነጻነታችንን ለማግኘት ከማንኛውም ጊዜ በተለየ መልኩ በሃገራዊ ስሜት ተነሳስተው በሁሉም አይነት የትግል ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወገኖቻችንን ለማገዝ የበኩላችንን ለመወጣት በጋራ የቆምን መሆናችንን እንገልጻለን::
የዜጎች ነጻነት ማጣት መሰቃየት መታሰር መሞት መሰደድ ግድ ብሎን አላማችንን ከእውነተኛ የነጻነት ትግል በመነሳት የወያኔን አረመኔያዊ ስርአት አስወግዶ ነጻነታችንን ለመቀዳጀት በኢትዮጵያዊነት ስሜትና ተነሳሽነት እስከሆነ ድልን የምንቀዳጅበት ቀን ሩቅ መስሎ አይሰማንም:: ለዚህም ፈጣሪያችንን ከልብ እንማጸነዋለን::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!!!
በኦክላንድ የኢትዮጵያውያን ነፃ የውይይት መድረክ
ነሐሴ 3 ቀን 2007 (ኦገስት 9 ቀን 2015
Source : http://ecadforum.com/Amharic/archives/15513/
No comments:
Post a Comment