ሐምሌ ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ም/ሰብሳቢ የነበረውና ከሶስት ሳምንት በፊት በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ፣ ‹‹ሰዎችን ለግንቦት ሰባት በመመልመል ወደ ኤርትራ ትልክ ነበር›› የተባለው አቶ ፍቃዱ በቀለ ከታሰረበት ካሳንችስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በዋስ ተፈቷል፡፡
በተመሳሳይ ክስ ተጠርጥሮ ከ25 ቀናቶች በላይ ካሳንችስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ የነበረው የቀድሞ አንድነትና በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው አቶ አበበ ቁምላቸውም በዋስ እንዲወጣ መታዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ዜናም፣ ‹‹የአልሸባብ ህዋስ ነህ፤ ባራክ ኦማባ በሚገኙበት ስብሰባ ወቅት የሽብር ወንጀል ለመፈፀም አሲረሃል›› ተብሎ ለ28 ቀናቶች፣መገናኛ አሚቼ አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ የነበረው የቀዳሚ ገጽ ጋዜጣ ሥራ አስኪያጅና የቀድሞ የሚሊየኖች ድምጽ ጋዜጣ ሪፖርተር ሀብታሙ ምናለ ከትናንት በስትያ ከምሽቱ 2፡30 ገደማ ከእስር ቤት መውጣቱን ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍርዋል።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment