ኢሳት ዜና (ነሐሴ 12 ፣ 2007)
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የዞኑ አስተዳደር ህገ ወጥ ግንባታ ናቸው ያላቸውን መኖሪያ ቤቶች ለማፍረስ መሞከሩን ተከተሎ ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውና መደብደባቸው ተገለጠ።
በሳምንቱ መገባደጃ በዞኑ በምትገኘው የቦሎሶሶሬ ወረዳ በተቀሰቀሰ በዚሁ ግጭት ከ20 በላይ ነዋሪዎች በላይ ነዋሪዎችና ህገ-ወጥ ናቸው የተባሉትን ግንባታዎች ለማፍረስ የተሰማሩ ከ10 በላይ አፍራሽ ግብረ ሀይሎች ጉዳይ እንደደረሰባቸው ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የከተማዋ አስተዳደር በህገ ወጥ መንገድ ተገንብተዋል ያላቸውን ከ940 በላይ ቤቶች ለማፍረስ እንቅስቃሴ ባደረገ ግጭት መፈጠሩን የተናገሩት ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶቹን በከተማዋ ማካለል ይቻል እንደነበር ገልጸዋል ።
ይሁንና የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ ስድስቱ ቀበሌዎች ወደ ከተማ እንደሚካለሉ እያወቁ ነዋሪዎቹ ህገ-ወጥ ግንባታን አካሂደዋል ሲል ለግጭቱ ነዋሪዎችን ተጠያቂ አድርጓል።
በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት ተከትሎም በርካታ ነዋሪዎች ለእስር እንደተዳረጉና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የታወቀ ሲሆን እስከ 40 የሚደርሱ ሰዎች መታሰራቸውን በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሀኖች ዘግበዋል።
ፖሊስ በበኩሉ ለእስር የዳረገውን ነዋሪ ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቦ በታሳሪዎች ላይ ምርመራን እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ እዮብ ዋቴ በፖሊስ በኩል ሁለት አባላቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው ብዛት ያላቸው ሰዎች መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል።
በከተማው ዙሪያ የሚገኙ ስድስት የቀበሌ ማህበሮችን ወደ ከተማዋ ለማካለል እቅድ ተይዞ እየተሰራ ቢሆንም ድርጊቱ ለግጭቱ ምክኒያት መሆኑን ታውቋል።
ዱቦ ፤ አቹራ፤ ዶላና ኡቶ በተባሉ አራት ቀበሌዎች የተቀሰቀሰው ግጭት በነዋሪዎች ዘንድ ውጥረትን አስፍኖ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
Source : https://m.facebook.com/ESATtv/posts/1011255722239843
No comments:
Post a Comment